የፕላስቲክ ጠርሙስና የምግብ ማሸጊያ ግብዓቶችን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ረቂቅ መመርያ ሊዘጋጅ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪዎች ምርምር ልማት ማዕከልና የኢትዮጵያ የመጠጥ አምራቾች ማኅበር በጋራ አስታወቁ፡፡
መመርያው ከፀደቀ በኋላ በዋናነት የሚመራው የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን እንደሚሆን፣ መመርያውም በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ ተቋማቶች የተውጣቱ ባለሙያዎች ለተከታታይ ጊዜ ውይይት አድርገውበት ለፍትሕ ሚኒስቴር መቅረቡን፣ የኢትዮጵያ ምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪዎች ምርምር ልማት ማዕከል የመጠጥ ፕሮሰሲንግ ምርምርና ልማት ዴስክ ኃላፊ አቶ አብዱራቅ ታመነ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ጥቅም ላይ የዋሉ የፕላስቲክ ጠርሙስና የምግብ ማሸጊያ ግብዓቶችን መልሶ ለመጠቀም የሚያስፈልጉ ግብዓቶች በረቂቅ መመርያው ውስጥ መካተታቸውን ገልጸው፣ ግብዓቶቹን የመሰብሰብ ተግባር በተቋም ደረጃ ብቻ የሚከናወን መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በዚህ መሠረት ግብዓቶችን የሚሰበስቡ ተቋማት ሕጋዊ ፈቃድ ኖሯቸው እንደሚንቀሳቀሱ፣ መልሶ ለመጠቀም የሚውሉ ግብዓቶች ከየት እንደሚገኙ፣ ማን እንደሚያመጣቸው፣ እንዲሁም ማን መልሶ ሥራ ላይ ያውላቸዋል የሚሉትን ለመከታተል የተለያዩ ተቋማት በጋራ የሚሠሩ መሆናቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡
መልሶ ለመጠቀም የሚውሉ ግብዓቶች ከሆቴል ቤቶችና ከሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተሰብስበው በሥርዓት የተዘጋጁ መሆን እንዳለባቸው የተናገሩት ኃላፊው፣ መመርያ እንዲወጣና ውሳኔ ላይ እንዲደረስ የተደረገበት ምክንያት የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ በመውሰድ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ለፍትሕ ሚኒስቴር የቀረበው መመርያ ከአሥራ ሦስት ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች አስፈላጊውን ውይይት አድርገውና ያለበትን ችግር አጥንተው እንዲያቀርቡ የተደረገ መሆኑን፣ ረቂቅ መመርያውን የፍትሕ ሚኒስቴር ገምግሞ አስተያየት ከሰጠ በኋላ የሚመለከተው አካል እንዲያፀድቀው እንደሚደረግ አብራርተዋል፡፡
በዚህ መሠረት መመርያው ሲፀድቅ የፕላስቲከ ጠርሙሶችንም ሆነ የታሸጉ ምግቦችን የሚሸጡ ተቋማት ከከፍተኛ ወጪ ሊድኑ እንደሚችሉ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የመጠጥ አምራቾች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ መርዕድ እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ የፕላስቲከ ጠርሙስ አምራች ድርጅቶች በተገቢው መንገድ እንዲያመርቱ ረቂቅ መመርያው ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡
ረቂቅ መመርያው ከፀደቀ 40 በመቶ ያህል ወጪያቸውን ሊቀንስ እንደሚችል የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፣ ለፕላስቲክ ጠርሙሶችና ለታሸጉ ምግቦች የሚሆኑ ግብዓቶችን መልሶ መጠቀም ለማስቻል ሦስት ባለሀብቶች ፍላጎት ማሳየታቸውን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵም በአሁኑ ወቅት ሰባት ያህል በመልሶ መጠቀም ምርት የተሰማሩ ተቋማት እንዳሉ፣ እነሱም በቴክኖሎጂ የታገዘ ግብዓት ካላቸው በዚህ ሥራ መሰማራት እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡
ተቋማቱ በምርት ሒደት የሚጠቀሙት ግብዓት ጤናን በማይጎዳ መንገድ መሆን እንዳለበት፣ ይህንንም የሚከታተል ተቋም እንዳለ ገልጸዋል፡፡
በተለይ መልሶ ለመጠቀም በሚደረገው ርብርብ ተቋማት ምን ያህል ቶን ያመርታሉ የሚለው በውል እንደማይታወቅ ጠቅሰው፣ በፕላስቲክ ጠርሙሶች የተሰማሩ ተቋማት ከተለያዩ ወጪ ሊድኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡