በንጥረ ነገሮች ያልበለፀጉ የምግብ ዘይትና የስንዴ ዱቄት የሚያስመጡ ድርጅቶች ወደ አገር ውስጥ እንዳያስገቡ ቁጥጥር መጀመሩን የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
ለኅብረተሰቡ በንጥረ ነገሮች የበለፀጉ የስንዴ ዱቄትና የምግብ ዘይት ላይ መጨመር ከአንድ ዓመት በፊት በአስገዳጅ ደረጃ መውጣቱ ይታወሳል፡፡
አስገዳጅ ደረጃው ከወጣ በኋላ ከውጭ አገሮች የዘይትና የስንዴ ዱቄት ምርቶችን በንጥረ ነገሮች የበለፀጉትን ብቻ እንዲገቡ ግዴታ መጣሉን የባለሥልጣኑ የምግብ ተቋማት ኃላፊ አቶ በትረ ጌታሁን ተናግረዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በመነጋገር ከውጭ ለማስገባት የምንዛሪ መጠይቅ (ኤልሲ) የሚከፈቱ ድርጅቶች፣ በንጥረ ነገሮች የበለፀጉ ብቻ እንዲያስገቡ ለማድረግና ያላሟሉ ድርጅቶችን ደግሞ ባንኩ ፈቃድ እንዳይሰጣቸው መደረጉን አስረድተዋል፡፡
በዚህ መሠረት በተለያዩ በአገሪቱ በሚገኙ 17 የመግቢያ በሮች ቁጥጥር መደረግ መጀመሩን፣ ይሁን እንጂ ገበያ ላይ የሚገኙት የስንዴ ዱቄትና የምግብ ዘይት ምርቶች ከባንኩ ጋር ስምምነት ሳይደረግ በፊት የገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ከሦስትና ከአራት ወራት በፊት ከባንኩ ጋር ስምምነት የተደረገ መሆኑን፣ ከዚህ በኋላ የባንክ የውጭ ምንዛሪ መጠየቅ ከፍቱው የሚያመጡ ድርጅቶች በንጥረ ነገሮች ያልበለፀጉ ምርቶችን ይዘው ቢገቡ ወደ መጡበት እንዲመለሱ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
ከስምምነቱ በኋላ በንጥረ ነገሮች ያልበለፀጉ ምርቶች ወደ መጡበት ተመላሽ መደረጋቸውንና ለዕርዳታ የገቡትን ግን በማስጠንቀቂያ እንዲያልፉ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
የአገር ውስጥ የስንዴ ዱቄትና የምግብ ዘይት አምራቾች ቁጥጥር ለመጀመር የዝግጅት የአንድ ዓመት ጊዜ የሚያስፈልጋቸው በመሆናቸው፣ እስካሁን ድረስ አስገዳጅ ሕጉ ተግባራዊ አልተደረገባቸውም ብለዋል፡፡
ባለሥልጣኑ የአገር ውስጥ የስንዴ ዱቄትና የምግብ ዘይት አምራቾች በንጥረ ነገሮች የማበለፅግ ግዴታ ቁጥጥር ለመጀመር ለሚመለከተው አካል ደብዳቤ ቢጽፉም፣ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት እስካሁን ወደ ሥራ መግባት አለመቻላቸው ምላሽ መስጠታቸውን እንደሚያሳይ አቶ በትረ ገልጸዋል፡፡
ደረጃው አስገዳጅ በመሆኑ ድርጅቶቹ የሚጨምሩት ንጥረ ነገሮች እጃቸው ላይ መኖሩን፣ ማደባለቂያ መሣሪያውንም ማሟላታቸውንና በሰው ኃይል ዝግጁ እንዲሆኑ ግልጽ ደብዳቤ መጻፋቸውን አስረድተዋል፡፡
ይሁን እንጂ የስንዴ ዱቄት ፋብሪካዎቹ ግን ንጥረ ነገሮቹን ማግኘት አለመቻላቸውና በቂ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው ሪፖርት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ምክንያት ችግሩን በጋራ ለመፍታት ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር ኮሚቴ እስከማዋቀር መድረሳቸውን፣ ኮሚቴው የሚያመጣው ውጤት ታይቶ ወደ አስገዳጅ ትግበራው እንደሚገቡ አስረድተዋል፡፡
በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪ ምርምር ማዕከል የባዮቴክኖሎጂና የምግብ ማበልፀግ ምርምር ልማት ዴስክ አስተባባሪ አቶ ሶፎንያስ ምንደሲል፣ በሦስት የምግብ ግብዓቶች ላይ በንጥረ ነገሮች የማበልፀግ ሒደት አስገዳጅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የስንዴ ዱቄትና የምግብ ጨው በአስገዳጅ ደረጃ የንጥረ ነገሮች የማበልፀግ ግዴታ መሆኑን፣ ከእነዚህ ውስጥ 97 በመቶ የምግብ ጨው ምርት የማበልፀግ ሒደት መከናወኑን አስረድተዋል፡፡
ይሁን እንጂ በሚፈለገው መጠን ጨውን በአዮዲን ማበልፀግ ሒደቱ በየጊዜው ቢዋዥቅም፣ በግዜ ሒደት እንደሚስተካከል አቶ ሶፎንያስ ገልጸዋል፡፡
የምግብ ዘይት ደረጃ ከሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ አስገዳጅ መሆኑን፣ 24 የሚሆኑ ድርጅቶች ምርቱን በንጥረ ነገሮች ለማበልፀግ በሒደት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
የአገር ውስጥ የዘይት ፍላጎት 82 በመቶ ከውጭ እንደሚገባ፣ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ደግሞ በንጥረ ነገሮች የበለፀጉ ምርት ብቻ እንዲገቡ ቁጥጥር መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
ማዕከሉ በዋናነት የሚሠራው 18 በመቶ የሆነው የአገር ውስጥ የዘይት አምራቾች ብቻ የማብቃት ሥራ እንደሚያከናውኑ ጠቁመዋል፡፡
ከእነዚያ ውስጥ 1.5 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛ ዘይት ጨማቂዎች በመሆናቸው፣ ድርጅቶቹ አስገዳጅ ደረጃው እንደማይመለከታቸውና ራሱን የቻለ ስትራቴጂ እንደተዘጋጀላቸው ጠቁመዋል፡፡
16.5 በመቶዎቹን የምግብ ዘይት አምራቾች በሁለት ወራት ውስጥ ሥራ እንደሚጀምሩና አራት ድርጅቶች በአሁኑ ጊዜ በንጥረ ነገሮች የበለፀገ ዘይት ወደ ማምረት መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡
ዘይት ላይ የሚጨመሩት ቫይታሚን ኤ እና ዲ መሆናቸውን፣ ለማስጀመሪያ የሚሆን ግብዓት ወደ አገር ውስጥ መግባቱን ጠቁመዋል፡፡
የስንዴ ዱቄት የሚያመርቱ 359 ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውን፣ እነዚህን ድርጅቶች በንጥረ ነገሮች የበለፀገ ምርት እንዲቀርቡ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች መሠራቱን ተናግረዋል፡፡
ከእነዚህ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ 40 የሚሆኑት የማበልፀጊያውን ዶዚንግ ማሽን ማሟላታቸውን፣ ከእነዚህ ውጪ ያሉትም እንዲያሟሉ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገባቸው ይገኛል ብለዋል፡፡
በስንዴ ዱቄት ላይ የሚጨመሩት ንጥረ ነገሮች በተሠራው የወጪ ትንተና መሠረት በኪሎ ከ20 እስከ 80 ሳንቲም ተጨማሪ ወጪ ፋብሪካዎች እንደሚጨምሩ ገልጸዋል፡፡
የሚጨመረው ባይታሚንና ማዕድን (ዚንክና ቢ ኮምፕሌክስ) እንደሚባሉና በአንድ ሜትሪክ ቶን የስንዴ ዱቄት ላይ 600 ግራም ብቻ እንደሚጨመር ተናግረዋል፡፡
የዶዚንግ ማሽን ወጪ የአንድ ጊዜ ኢንቨስትመንት መሆኑን፣ ከ200 ሺሕ ብር እስከ 500 ሺሕ ብር እንደየ ጥራቱ ተጨማሪ ወጪ ሊያስወጣቸው እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
የኒድ ኒውትረሽን ፕሮዳክት ሰርቪስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መሥራችና የሥነ ምግብ ባለሙያ አብነት ተክሌ፣ ምግብን ማበልፀግ ማለት ቀድሞ ከነበረው የተሻለና ጠቃሚ ንጥረ ነገሮች እንዲሆን ማስቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከ100 ዓመት በፊት በተለያዩ የዓለም አገሮች የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች በተለያዩ ንጥረ ነገሮች ማበልፀግ እንደተጀመረ የገለጹት አቶ አብነት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ከተጀመረ ቅርብ ጊዜ ነው ይላሉ፡፡
የዘይትና የስንዴ ዱቄትና ጨው በኢትዮጵያ በሁሉም ቤት ከሚገቡ የምግብ ፍጆታዎች የሚጠቀሱ መሆናቸውን፣ መንግሥት እነዚህ የምግብ ፍጆታዎችን በንጥረ ነገሮች በማበልፀግ ሊደርስ ከሚችል የማኅበረሰብ ጤና እክል መታደግ እንደሚቻል ይገልጻሉ፡፡
የምግብ ዘይት ቫይታሚን ኤ እና ዲ፣ የስንዴ ዱቄት ፎሊክና ሌሎች ንጥረ ነገሮች እንዲጨመር በማድረግ የትውልድ የጤና ሁኔታ ቀድሞ ለማስተካከል እንደሚጠቅም አስረድተዋል፡፡