ንብ ኢንሹራንስ ኩባንያ ‹‹ሲሲሲሲ›› ከተሰኘው የቻይና ሥራ ተቋራጭ ኩባንያ ጋር ባለመግባባት፣ ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ ተቋርጦ የነበረው የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ እንደገና መጀመሩን አስታወቀ፡፡
የኢንሹራንስ ኩባንያው 18 ወለሎች ያሉት የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ እንደገና ሊጀመር የቻለው፣ ግንባታውን ለማስቀጠል ከኮንትራክተሩ ጋር በተደረገ ድርድር ስምምነት ላይ በመድረሱ ነው ተብሏል፡፡
ቦሌ ዋናው መንገድ ሜጋ ሕንፃ አካባቢ እየተገነባ የነበረው የንብ ኢንሹራንስ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ ዘጠነኛ ወለል ላይ ከደረሰ በኋላ መቋረጡ ይታወሳል፡፡
ኮንትራክተሩ የሕንፃ ግንባታ ሥራውን ያቋረጠው በዋጋ ንረት ጋር ምክንያት ማስተካከያ እንዲደረግለት ያቀረበው ጥያቄ በወቅቱ አዎንታዊ ምላሽ ባለማግኘቱ እንደነበር መገለጹ አይዘነጋም፡፡
ከተደጋጋሚ ድርድር በኋላ በተደረሰው ስምምነት ኮንትራክተሩ ግንባታውን ለማካሄድ፣ ቀድሞ ሙሉውን የሕንፃ ግንባታ አጠናቅቆ አሸናፊ ከነበረበት ዋጋ 2.5 በመቶ ጭማሪ እንዲደረግለት ተወስኖ ሥራው መጀመሩ ታውቋል፡፡ የማጠናቀቂያ (ፊኒሺንግ) ሥራውን በሌላ ስምምነት እንዲያከናውን የሚደረግ መሆኑን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የንብ ኢንሹራንስ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ዙፋን አበበ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የተቋረጠው የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ በሁለት በመክፈል እንዲጀመር ተወስኗል፡፡ በውሳኔው መሠረት የስትራክቸሩንና የማጠናቀቂያ ሥራው ለየብቻው በሚደረግ ውል ተፈጻሚ ይሆናል ብለዋል፡፡ በመጀመሪያው ዙር የስትራክቸር ግንባታው በስድስት ወራት እንዲያልቅ በተገባው ውል መሠረት መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡ ይህ ከተጠናቀቀ በኋላ የማጠናቀቂያ ሥራው ደግሞ እንደገና ከኮንትራክተሩ ጋር በመደራደር በስምምነት እንዲቀጥል የሚደረግ መሆኑን ወ/ሮ ዙፋን አስረድተዋል፡፡
በአዲሱ ስምምነት መሠረት ግንባታ ከተጀመረ በኋላ ዘጠነኛ ወለል ላይ ቆሞ የነበረው የግንባታ ሒደት አሁን 13ኛ ወለል ላይ መድረሱንም ወ/ሮ ዙፋን ገልጸዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ንብ ኢንሹራንስ ኩባንያ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓመታዊ የዓረቦን ገቢውን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ መቻሉ ታውቋል፡፡ ይህም ዓመታዊ የዓረቦን ገቢያቸውን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ ከቻሉ ጥቂት የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች መካከል አንዱ አድርጎታል፡፡
ንብ ኢንሹራንስ ኩባንያ በሒሳብ ዓመቱ ያሰባሰበው የ1.1 ቢሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ55.8 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ከአጠቃላይ የዓረቦን ገቢ ውስጥ 90.5 በመቶ የሚሆነው ሕይወት ነክ ካልሆነው የኢንሹራንስ ዘርፍ የተገኘ ሲሆን፣ 9.5 በመቶ ደግሞ ከሕይወት ነክ የኢንሹራንስ ዘርፍ እንደሆነ የኩባንያው መረጃ ያመለክታል፡፡
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ኩባንያው በአጠቃላይ 472.8 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ የፈጸመ መሆኑን፣ ለተሽከርካሪ ዋስትናና ለሕክምና የተከፈለው የካሳ መጠን ትልቁን ድርሻ እንደያዘም ተመልክቷል፡፡
ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ካስመዘገበው ውጤት አንፃር የትርፍ መጠኑንም ማሳደግ የቻለ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ የተመዘገበውም የትርፍ ምጣኔ በታሪኩ ከፍተኛ የተባለ ሲሆን፣ ይህም ከታክስ በፊት 291.2 ሚሊዮን ብር ማትረፍ መቻሉን ከኩባንያው መረጃ መገንዘብ ተችሏል፡፡
ንብ ኢንሹራንስ ኩባንያ ከተመሠረተ 21 ዓመታት የሞሉት ሲሆን፣ ጠቅላላ የሀብት መጠኑ 2.8 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የተከፈለ ካፒታሉም 735.4 ሚሊዮን ብር ማድረጉንም አስታውቋል፡፡ በተለያየ የአገሪቱ ክፍሎች 52 ቅርንጫፎችና አገናኝ ቢሮዎች ሲኖሩት፣ የኩባንያው ሠራተኞች ቁጥርም 420 ደርሷል ተብሏል፡፡