Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹የጥበብ ውለታ ጉዞ›› ምንን ይዟል?

‹‹የጥበብ ውለታ ጉዞ›› ምንን ይዟል?

ቀን:

‹‹ጥበብ አክባሪዋን ታከብራለች›› ይባላል፡፡ ይሁን እንጂ ጥበብ በእነሱ ላይ አድራ፣ አብባና አፍርታ ነፍስ ዘርታ በታዳሚዎች ፊት ቀርባ ትበላና ትጠጣ እግር አውጥታ ተራምዳ የምትጠጋበት ዋርካ ክንፍ አውጥታ በራ ታርፍበት ዘንድ ማረፊያ ማማ ያስፈልጋታል።

ማረፊያዎቿ ደግሞ ጠቢባን መሆናቸው አይዘነጋም፡፡ ጥበብ መከሰቻዋ መምጫዋና መገኛዋ አይታወቅም፡፡ አንዱ ብሩሽ ከቀለም ጋር ተዋዶ በሸራ ተወጥሮ አጃኢብ የተባለለት ሥዕል ብራና ላይ ሲያሰፍር፣ ሌላው ፊደላትን ከቃላት አዋህዶ፣ ዜማን ከቅኔ አዋዶ ጥዑም ዜማን ለጆሮ ሲያደርስ፣ ገጣሚው ደግሞ ቃላትን በመሰደር ሲያሻው ፍቅርን ፍንትው አድርጎ በማሳየት፣ ሲፈልግ ወርቁን በሰም አከናንቦ ፖለቲካውን እንደ አመጣጡ ጎሸም ሲያደርግ ይስተዋላል፡፡ ጥበብ በጥበበኞች ላይ አድራ ትናገራለችና።

ጥበብ የማትደርስበት ጥግ የማትዳስሰው ርዕሰ ጉዳይ የለም፡፡ በፖለቲካው ቢሉ በኢኮኖሚው፣ የአገርን ወግና ባህል በማስተዋወቅ የራቀውን አቅርባ የረቀቀውን አጉልታ በማሳየት ረገድ ኪነ ጥበብ ወደር አይገኝላትም፡፡

ብዙ ታዋቂና ስመጥር የዓለማችን የኪነ ጠበብ ባለሙያዎች ሙሉ ዘመናቸውን ኪነ ጥበብን ሲዘሩ፣ ሲያጭዱ፣ ሲያቦኩና ሲጋግሩ ይኑሩ እንጂ ጥበብ በሠሩት ልክ ስትከፍላቸው አይስተዋሉም፡፡

ከአገራችን የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የአገር ባለውለታዎች ገጣሚዎች፣ ከያኒዎች፣ ደራሲዎች፣ ሠዓሊዎችና ሌሎችም የዘርፉ ባለሙያዎች በሠሩት መልካም ሥራ ጥቂት የማይባሉና ምሥጋናና ክብርን ከማግኘት ይልቅስ ለስደት፣ ለእስራትና ለሞት ሲዳረጉ ማየት የተለመደ ተግባር ነው፡፡

በኢኮኖሚያቸውም ቢሆን ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር ተስኗቸው ብዙ ውጣውረድ ሲገጥማቸው ይስተዋላሉ፡፡

በሠሩት ጥበብ ልክ ተከፍሏቸው ሕይወታቸውን በአግባቡ የኖሩ የጥበብ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ፣ ያበረከቱት ጥበብ ተረስቶ ሲታመሙ እንኳ መታከሚያ አጥተው ገንዘብ ከሕዝብ ሲሰባሰብላቸው ይስተዋላል፡፡

የሆነ ሆኖ ይህንን ችግር ይፈታል፣ የጥበብ ሰዎችም በሠሩት ልክ ይከፈላቸው ዘንድ እንዲሁም ተሰባስበው በአንድነት ስለጥበብ ያስቡና ያሰላስሉ ይወያዩና ይጠያየቁ ዘንድ፣ በአንድነት የሚያሰባስብ በኢትዮጵያ ‹‹የጥበብ ውለታ›› የተሰኘ ፕሮጀክት ይፋ ሆኗል፡፡

የጥበብ ውለታ ፕሮጀከት መንግሥትን፣ ባለሀብቶችንና ኅብረተሰቡን በማስተባበር ሦስት ዋና ዋና ተግባራትን ለመሥራት መታሰቡን ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተገልጿል፡፡

 ፕሮጀክቱን ዕውን ለማድረግ የተሰባሰቡት አርቲስቶች ለንደን ከተማ ላይ ሆነው በቪዲዮ በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ በእንግሊዝ ለሚገኙ ኢትጵያውያን ዳያስፖራዎች ለማስተዋወቅ  መሄዳቸውን ተናግረዋል፡፡

በስብስቡ ውስጥ ተካተው ወደ እንግሊዝ ከሄዱት አርስቲስቶች መካከል ሰለሞን ተካ፣ ማክዳ ኃይሌ፣ ፍቅርተ ጌታሁንና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

 ሦስቱ ዋና ዋና የጥበብ ውለታ ፕሮጀክት ዓላማዎች፣ የጥበብ ባለውለታዎች የጋራ መኖሪያ መንደር ግንባታ፣ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት፣ የመመገቢያና የመዝናኛ ማዕከል ግንባታዎችን ለመሥራት አቅደው መነሳታቸውን ባለሙያዎቹ ተናግረዋል፡፡

 በዚህም የጥበብ ቤተሰብ ከልመናና ከችግር የሚወጡበትን ሥራ ለመሥራት እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ከተጠቀሱት ዋና ዋና ዓላማዎች በተጨማሪ ጥበበኛውም ከአገሩ ማግኘት የሚገባውን እንዲያገኝ፣ አገርም ከጥበብ መጠቀም ያለባትን ሁሉ እንድትጠቀም ማስቻል የዲያስፖራውን ሚናና ተሳታፊነትን የማመቻቸት ሥራን እንደሚሠሩ አርቲስቶቹ ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር አንጋፋ የጥበብ ባለውለታዎች ከአገር ወጥተው የሚዝናኑበትን፣ ሁኔታዎች ማመቻቸት፣ እንዲሁም የአገርን ገጽታ በኪነ ጥበብ ሥራዎች በማስተዋወቅ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን ማሳደግ የሚቻልበትን ሁኔታ ዕውን ለማድረግ የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ደራስያን፣ ሙዚቀኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ሞዴሎች፣ ዲዛይነሮች፣ ሠዓሊያን፣ ዜማ ደራሲዎች፣ ድምፃውያንና የመሳሰሉት የጥበብ ውለታ ዓላማ ተጠቃሚ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ባለሙያዎችን ዋና ተጠቃሚ ያደርጋል የተባለው ፕሮጀክት   ስኬታማ ይሆን ዘንድ፣ ‹‹የጥበብ ውለታ ጉዞ›› ብለው ወደ እንግሊዝ የተጓዙ አርቲስቶች ብቻ የሚያሳኩት ጉዳይ ስላልሆነ ገጣሚው በግጥሙ፣ ዜማ ደራሲው በዜማ ድርሰቱ፣ ድምፃውያንም በድምፃቸው፣ ሠዓሊያን በቡርሻቸው፣ ዲዛይነሮችና ሞዴሎች በሥራዎቸው ዓላማው ዕውን ይሆን ዘንድ ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

የባህልና ቱሪዝም የበላይ ኃላፊዎችም፣ ፕሮጀክቱ ተሳክቶ አገር ከጥበብ ማግኘት የሚገባትን ሙሉ ጥቅም በሁሉም መልኩ እንድታገኝ፣ ጥበበኛውም ማግኘት የሚገባውን ጥቅም እንዲያገኝ፣ እንዲሁም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ለአገር የሚያደርጉትን አስተዋጽኦና የሚኖሩትን የሕይወት ደረጃ በመገምገም በጥበበኛው ኅብረትና በሕዝብ ተሳትፎ የሚሠሩ ሥራዎች ስኬታማ ይሆኑ ዘንድ ከጎናቸው እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

  ፕሮጀክቱ በአዲስ አበባ ባሉት በ11 ክፍለ ከተሞች ተግባራዊ እንደሚሆን ተጠቅሷል፡፡

ድምፃውያንን በማስተባበር ኮንሰርቶችን መሥራት፣ በኮንሰርቶች ላይ ታዋቂ ግለሰቦችን እንዲገኙ በማድረግ ገቢ ማሰባሰብ፣ በርካታ ሰዎች የሚሮጡበት ‹‹ለጥበብ እንሮጣለን›› የተሰኘ የሩጫ ዝግጅቶች በአዲስ አበባና በተለያዩ ዋና ዋና ከተሞች ይዘጋጃሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ገንዘብ ማሰባሰብ የሚያስችል ጎ ፈንድሚ አካውንት በመክፈት እንዲሁም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋርም በመነጋገር በአጭር የመልዕክት ቁጥር ገንዘብ በማሰባሰብ ፕሮጀክቱን ዕውን ለማድረግ የሚሠሩ ሥራዎች እንደሆኑም ተነግሯል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...