Wednesday, December 6, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንግድ ምክር ቤቱ ኤግዚቢሽን ማዕከልን ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ ለማልማት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከልና መስቀል አደባባይን እንዲያስተዳድር ተሰጥቶት የነበረው ውለታ የተቋረጠበት አዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ማዕከሉን ከአስተዳደሩ ጋር ለማልማት የቀረበለትን ጥያቄ መቀበሉን አስታውቀ፡፡ 

ንግድ ምክር ቤቱ ከ20 ዓመታት በላይ ሲያስተዳድር የነበረው ማዕከል ላይ ምንም ዓይነት ኢንቨስትመንት ሳይካሄድ በመቆየቱና የከተማ አስተዳደሩ ቦታውን በራሱ ለማልማት በመፈለጉ ከንግድ ምክር ቤቱ ጋር የነበረውን ውል ማቋረጡ ይታወሳል፡፡ 

ንግድ ምክር ቤቱ በኤግዚቢሽን ማዕከል ላይ የነበረው የማኔጅመንት ውል ስለመቋረጡና ማዕከሉን በጋራ ለማልማት ስለቀረበው ጥሪ በሚል ርዕስ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ፣ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመሆኑ ማዕከሉን ለማልማት ፍላጎት እንዳለው ገልጿል።

ምክር ቤቱ በመግለጫው በኤግዚቢሽን ማዕከል ላይ የነበረውን የማኔጅመንት ውል የተከማ አስተዳደሩ ማቋረጡን የተቸ ቢሆንም፣ በመግለጫ የመደምደሚያ ሐሳብ ላይ ግን ማዕከሉ የሚገኝበትን ቦታ በጋራ ለማልማት ከአስተዳደሩ የቀረበውን ጥሪ መቀበሉን ጠቅሷል፡፡ 

‹‹የከተማ አስተዳደሩ ማዕከሉን በጋራ እንድናለማው ያቀረበልንን ጥሪ በመላ የምክር ቤታችን አባላትና በንግዱ ኅብረተሰብ ስም መቀበላችንን እናረጋጋጣለን፤›› በማለት በቦታው ላይ ከአስተዳደሩ ጋር ለማልማትና ዝግጁ መሆኑን አሳውቋል፡፡ 

አያይዞም በቀጣይም በቂ ምክክር ተደርጎበት ለጋራ ጠቀሜታና ለከተማዋ ልማት ዘላቂ ፋይዳ ያለው መሆኑን በማሳመንና ንቅናቄ በመፍጠር ተፈጻሚ ለማድረግ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ማሳወቅ እንደሚፈልግ ምክር ቤቱ ገልጿል።

አስተዳደሩ የሰየመው የኤግዚቢሽን ማዕከሉ ሥራ አመራር ቦርድ፣ ንግድ ምክር ቤቱ ማዕከሉን በጋራ ለማልማት በሰጠው አዎንታዊ ምላሽ ላይ በዚህ ሳምንት ተወያይቶ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ታውቋል፡፡ የቦርድ ሊቀመንበሩና የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክረ ለሪፖርተር እንደገለጹት ንግድ ምክር ቤቱ በቦታው ላይ በጋራ ለማልማት መወሰኑ የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡ 

ቢሆንም ግን በጉዳዩ ላይ ንግድ ምክር ቤቱ የሰጠውን ዝርዝር ምላሽ የከተማ አስተዳደሩ በጥልቀት እንዳልተመለከተው ጠቅሰው፣ አስተዳደሩ ሰሞኑን በሚያደርገው ስብሰባ ተመልክቶ ውሳኔ የሚሰጥበት መሆኑን አቶ ቢኒያም ገልጸዋል፡፡ 

ንግድ ምክር ቤቱ ቦታውን በጋራ ለማልማት ፈቃደኛ ባይሆን ኖሮ ከሌላ ባለሀብት ጋር ለማልማት የሚገደድ መሆኑን አስተዳደሩ ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡ 

ምንጮች እንደገለጹት፣ የተለያዩ ባለሀብቶች ቦታውን ከአስተዳደሩ ጋር በጋራ ለማልማት ጥያቄ እያቀረቡ በመሆናቸው፣ አስተዳደሩ የኤግዚቢሽን ማዕከሉን በጋራ ለማልማት ከንግድ ምክር ቤቱ ማዕከሉን በጋራ ለማልማት ያሳየውን ፍላጎት የከተማ አስተዳደሩ ላይቀበለው እንደሚችል ጠቁመዋል።

ለዚህም በዋናነት የሚጠቅሱት አስተዳደሩ ለንግድ ምክር ቤቱ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ እንዲውል በሰጠው ቦታ ላይ ግንባታ ማካሄድ አቅቶት አስተደደሩ የሰጠውን ቦታ መልሶ ለመውሰድ መገደዱን ነው። 

እንደ ምንጮች ገለጻ ከሆነ የንግድ ምክር ቤቱ የቀድሞ አመራር ለአዲሱ አመራር ኃላፊነቱን ሲያስረክብ የሕንፃ ማስጀመርያ ሊሆን የሚችል በጀት መድቦ የነበረ ቢሆንም ኃላፊነት የተረከበው አመራር ግን ግንባታውን ማስጀመር ተስኖት ቦታው ሊነጠቅ ችሏል።

በሌላ በኩልም የቀድሞ የንግድ ምክር ቤቱ አመራሮች የኤግዚቢሽንና የኮንቬንሽን ማዕከል እንዲገነባ በንግድ ምክር ቤቱ ስም ሲኤምሲ አካባቢ የወሰዱት ቦታ ላይ የተጀመረው ግንባታ በአሁኑ ጊዜ እየተጠናቀቀ ቢሆንም እዚህ ፕሮጀክት ላይ ንግድ ምክር ቤቱ የባለቤትነት ድርሻው በእጅጉ የቀነሰ ሆኖ መገኘቱም ተጨማሪ ግንባታ ለማካሄድ ይችላል ወይ የሚል ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ 

ንግድ ምክር ቤቱ ዋነኛ ባለድርሻ ይሆንበታል ተብሎ የታመነው የሲኤምሲው ኮንቬንሽን ማዕከል በአሁኑ ሰዓት ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያለው ቢሆንም ከዚህ ውስጥ የንግድ ምክር ቤቱ ድርሻ አሥር ሚሊዮን ብር ብቻ ነው፡፡ ይህ የሆነው ኢንቨስት ማድረግ ስላቃተው በመሆኑ አሁንም ከአስተዳደሩ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ግንባታ ለማድረግ አይችልም የሚል ሥጋታቸውንም ያንፀባርቃሉ፡፡ በዚህ የኮንቬንሽን ማዕከል የአዲስ አበባ አስተዳደር ተጨማሪ አክሲዮኖችን እየገዛ የባለቤትነት ድርሻውን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ መቻሉንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች