የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውን ከተቀላቀለ አራተኛ ዓመቱን የያዘው ዘመን ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር፣ ባለፈው ዓመት አግኝቶ የነበረውን 2.5 ሚሊዮን ብር በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ወደ 45.9 ሚሊዮን ብር በማሳደግ ከፍተኛ ዕድገት አስመዘገበ። ኩባንያው በተጠናቀወው የሒሳብ ዓመት ያገኘው የዓረቦን ገቢም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ316 በመቶ ብልጫ ያለው ሆኖ ተመዝግቧል።
ኢንሹራንስ ኩባንያው ቅዳሜ ጥቅምት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንዳስታወቀው፣ በ2015 የሒሳብ ዓመት በኢንዱስትሪው ላይ ከፍተኛ ጫና የነበረ ቢሆንም፣ ይህንን ጫና በመቋቋም ከፍተኛ ዕድገት የታየበት ውጤት ማስመዝገቡን አመላክቷል፡፡
የዘመን ኢንሹራንስ ኩባንያው ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ግርማ ሰይፉ ለጠቅላላ ጉባዔው ባቀረቡት ሪፖርት፣ ኩባንያው በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት 325.58 ሚሊዮን ብር ገቢ ከዓረቦን አሰባስቧል፡፡ ይህ ገቢ ከቀዳሚው ዓመት በ316 በመቶ ዕድገት ከማሳየቱም ባለፈ ኩባንያው በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት አገኛለው ብሎ ካቀደው የዓረቦን ገቢ በ104 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ተናግረዋል። ኩባንያው በ2015 የሒሳብ ዓመት 165.6 ሚሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ ነበር ለመሰብሰብ ያቀደው፡፡ አፈጻጸሙ ግን 325.5 ሚሊዮን ብር ሆኗል። ዘመን ኢንሹራንስ በ2014 የሒሳብ ዓመት ከዓረቦን ያገኘው ገቢ 78.26 ሚሊዮን ብር ብቻ እንደነበር የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ያቀረቡት ሪፖርት ያመለክታል፡፡ በ2015 የሒሳብ ዓመት ከተሰባሰበው አጠቃላይ የዓረቦን መጠን ውስጥ 126.02 ሚሊዮን የተጣራ ገቢ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ388.3 በመቶ ወይም የ100.2 ሚሊዮን ብር ጭማሪ ያሳየ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በ2014 የሒሳብ ዓመት ኩባንያው የተጣራ የዓረቦን መጠኑ 25.8 ሚሊዮን የነበረ በመሆኑ የተጣራ ዓረቦን ገቢው በከፍተኛ ደረጃ ማደጉን ሪፖርቱ ያሳያል።
ዘመን ኢንሹራንስ በሒሳብ ዓመቱ ያገኘው ከፍተኛ የዓረቦን ገቢ የኩባንያውን ዓመታዊ ትርፍና የባለአክስዮኖች የትርፍ ድርሻ መጠንንም በዚያው ልክ አሳድጎለታል። የኩባንያው ሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ባቀረቡት ሪፖርት መሠረት፣ ዘመን ኢንሹራንስ በ2015 የሒሳብ ዓመት 45.9 ሚሊዮን ብር ትርፍ አስመዝግቧል። ይህ የትርፍ መጠን በቀዳሚው ዓመት ከተመዘገበው 2.53 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር 18 እጥፍ ብልጫ ያለው ነው።
ኩባንያው በተጠናቀቀው ሒሳብ ዓመት ያገኘው ትርፍ በባለአክሳዮኖች የትርፍ ድርሻ በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር አድርጓል። በዚህም መሠረት አምስት መቶ ብር ዋጋ ያለው የኩባንያው አንድ አክሲዮን በተጠናቀቀው የሐሲብ ዓመት 1,587 ብር የትርፍ ድርሻ ያገኛል። ከዚህም ባለፈ ኩባንያው በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ያስመዘገበው ውጤታማ የሥራ አፈጻጸም በኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን የገበያ ድርሻ እንዳሳደገለትም ለማወቅ ተችሏል፡፡
አቶ ግርማ ባቀረቡት ሪፖርት እንደለጹትም፣ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት የተገኘው ከፍተኛ የዓረቦን ገቢ የኩባንያውን የገበያ ድርሻ በ2014 ከነበረበት የ0.5 በመቶ፣ ወደ 1.53 በመቶ ከፍ አድርጎታል፡፡ ዘመን ኢንሹራንስ ከቀዳሚዎቹ ዓመታት በተለየ ዘንድሮ ያስመዘገበውን ውጤታማ የሥራ አፈጻጸም በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ እንዳልካቸው ዘለቀው፣ ‹‹በብዙ ጥረት የመጣ ውጤት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ከኩባንያው ከሌሎች ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በተለየ እስከ 12፡30 ሰዓት አገልግሎት መስጠቱም የራሱ አስተዋጽኦ እንደነበረው አመልክተዋል፡፡
በተለይ ግን ኩባንያው በኢንዱስትሪው ያልተለመዱ አዳዲስ አገልግሎቶችን መጀመሩ፣ እንዲሁም በሒሳብ ዓመቱ አካባቢ በተለይ የተሽከርካሪ ኢንሹራንስ ሽፋን ዓረቦን መጠነኛ ዕድገት ማሳየቱ ለአፈጻጸሙ አስተዋጽኦ እንደነበረውም ጠቅሰዋል፡፡ በተለይ የተሽከርካሪ ጉዳት ካሳ ክፍያ ጋር በተያያዘ ኩባንያው ይዞት የመጣው አዲስ አሠራር በተሽከርካሪ የመድን ሽፋን ከፍተኛ ዓረቦን ለመሰብሰብ እንዳስቻለው አቶ እንዳልካቸው ገልጸዋል፡፡
አዲስ ያሉት ይህ አሠራር ደንበኞች ጉዳት የደረሰበትን ተሽከርከሪዎቻቸውን መልሰው እስኪያገኙ ወይም ጥገና እስኪያደረግለት ድረስ ለደንበኞቻቸው ከአንድ ሳምንት እስከ 30 ቀናት የሚገለገሉበት ተሽከርካሪ ኪራይ ወጪ የሚሸፍን መሆኑ አንዱ ሲሆን፣ እንዲህ ባለው አገልግሎት ብዙ ደንበኞችን ለመሳብ ያስቻላቸው ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡
ከኢንሹራንስ ኩባንያው ዓመታዊ ሪፖርት መረዳት እንደተቻለውም፣ በሒሳብ ዓመቱ ከተገኘው አጠቃላይ የዓረቦን ገቢ ውስጥ 77.5 በመቶ የሚሆነው የመነጨው ከተሽከርካሪ የመድን ዋስትና ሽፋን ነው። የተቀረው 22.5 በመቶ ደግሞ ከሌሎች የመድን ሽፋን ዓይነቶች ነው፡፡ በመሆኑም ፣ የኢንሹራንስ ኩባንያው ገቢ በተሽከርካሪ የመድን ሽፋን ላይ የተንጠለጠለ መሆኑን ያሳያል። ይህ መሆኑ በኩባንያው ትርፍ ዘላቂነት ላይ እክል የሚፈጥር ነው። ነገር ግን ኩባንያውም ይህንን ስጋት በመገንዘብ የዓረቦን ገቢ ስብጥሩን በማስፋት ለማመጣጠን እንደሚሠራ አስታውቋል።
አቶ ግርማ ሰይፉም በሪፖርታቸው የኩባንያው የዋስትና ዓይነቶች ስብጥር ከጀማሪነቱ አንፃር ጥሩ የሚባል ቢሆንም፣ በቀጣይ የገቢ ስብጥሩን ለማመጣጠን በከፍተኛ ጥረት መሠራት እንዳለበት የሥራ አመራር ቦርዱ አቅጣጫ ማስቀመጡን አመልክተዋል፡፡
ኩባንያው በአብዛኛው የተሽከርካሪ ኢንሹራንስ ሽፋን እንደመስጠቱ፣ በሒሳብ ዓመቱ ለካሳ ክፍያ ወጪ ካደረገው ውስጥ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆነው ለዚሁ የተሽከርካሪ መድን ሽፋን ነው፡፡
በሪፖርቱ እንደተጠቀሰው በሒሳብ ዓመቱ 39.00 ሚሊዮን ብር ያልተጣራ የካሳ ክፍያ ተፈጽሟል፡፡ በተጨማሪም በሒደት ላይ ለሚገኙ የጉዳት ካሳ ጥያቄዎች 40.2 ሚሊዮን ብር መጠባበቂያ የተያዘ መሆኑንም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ በአጠቃላይ የተጣራ የ68.25 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ የተመዘገበ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ52.78 ሚሊዮን ብር ወይም የ341.3 በመቶ ዕድገት ጭማሪ እንዳለው ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡ በቀዳሚው ዓመት የተጣራ የካሳ ክፍያ መጠኑ 15.47 ሚሊዮን ነበር፡፡
የኢንሹራንስ ኩባንያው በዓረቦን ገቢም ሆነ በትርፍ ደረጃ ያስመዘገበው ውጤት በቀጣይም ዕድገቱን ጠብቆ የሚሄድ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ እንዳልካቸው፣ ኩባንያቸው በአጠቃላይ አፈጻጸሙ ዕድገት እያሳየ የሚሄድ መሆኑን እርግጠኛነት ተናግረዋል፡፡ ለዚህም በ2016 የሒሳብ ዓመት የመጀመርያዎቹ ወሮች ያስመዘገበው ውጤት ምስክር መሆኑን ይጠቅሳሉ። ኩባንያው በዘንድሮው የሒሳብ ዓመት የመጀመሪያ ሦስት ወራት ውስጥ ያሰባሰበው የዓረቦን ገቢ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከእጥፍ በላይ የጨመረ በመሆኑ በ2015 ዓ.ም. የተመዘገበው ውጤት በአዲሱ ዓመትም ቀጣይነት እንደሚኖረው ያመላክታል ብለዋል። በተጠናቀቀው ዓመት የተገኘው ከፍተኛ ውጤት በአጋጣሚ የመጣ ሳይሆን ኩባንያው በተገበራቸው አሠራሮች የመነጨ ስለመሆኑም አቶ እንዳልካቸው ተናግረዋል፡፡
የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አሁን እየታየ ባለው ከፍተኛ የሆነ ዋጋ ንረት ጉዳት እየደረሰባቸው ስለመሆኑ የሚገልጹት አቶ እንዳልካቸው፣ በአጠቃላይ አፈጻጸሙን እያሳደጉ መሄድ ከብዙ አኳያ የግድ ነው፡፡ በተለይ ወደፊት ኩባንያዎች ወደ ውህደት ቢገቡ ራስን አጠንክሮ መገኘት ያስፈልጋል፡፡
ኩባንያው የራሱ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ እንዲኖረው ለማድረግ ሕንፃ ለመግዛት ባወጣው ጨረታ መሠረት፣ አሸናፊ ከተባለው የሕንፃ ባለቤት ጋር የግዥውን ሒደት የማጠናቀቅ ሥራ በመሥራት ላይ እንደሚገኝም በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
ዘመን ኢንሹራንስ በአሁኑ ጊዜ ካፒታሉ 207.6 ደርሷል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ካፒታል ወደ 500 ሚሊዮን ብር ማደግ እንዳለበት በወሰነው መሠረተ፣ ዘመን ኢንሹራንስም ባለፈው ዓመት ካፒታሉን ወደ 500 ሚሊዮን ብር ለማሳደግ በመወሰን፣ ለባለአክሲዮኖች የአክሲዮን ሽያጭ ጀምሯል፡፡
ከየካቲት 2016 ዓ.ም. በኋላ ግን ከባለአክሲዮኖች ሌላ ለሌሎች አክሲዮን ገዥዎች ሽያጩን ክፍት የማድረግ እንደሆነ ታውቋል፡፡ ኩባንያው የራሱ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ እንዲኖረው፣ በአዲስ አበባ ከተማ ሕንፃ ለመግዛት ባወጣው ጨረታ አሸናፊውን የለየ ሲሆን፣ የሕንፃ ግዥ ስምምነቶችን በማካሄድ ሒደት ላይ መሆኑንም አሳውቋል፡፡
ዘመን ኢንሹራንስ በአሁኑ ወቅት በ23 ቅርንጫፎች አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፣ በ2016 የቅርንጫፎችን ቁጥር 30 ለማድረስ የሚሠራ ይሆናል ተብሏል፡፡ እንደ ኩባንያው መረጃ ኢንሹራንስ ኩባንያው አጠቃላይ የሀብት መጠኑ 526 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ዘመን ኢንሹራንስ ከአራት ዓመት በፊት የተቋቋመ ሲሆን፣ አሁን ላይ 954 ባለአክሲዮኖች አሉት፡፡