Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የእውነተኛ ፈራጅ ያለህ!

ከቦሌ ወደ ካዛንቺስ ልንጓዝ ነው። ሁሉም አካባቢ አቋራጭ እንጂ አገር አቋራጭ ባለመሆኑ፣ ከአንድ ራሱ በቀር ተጎታች ሳይኖረው ይሳፈራል። ወያላው ራቅ ብሎ ቆሟል። ‹‹የት ነው?›› እያለ እርስ በርሱ ተጠያይቆ የሚሳፈረው መንገደኛ ብዙ ነው። የጎዳናው አቀማመጥ የሕይወት ገጾችን የሚወክል ይመስላል። ለአንደኛው ቀላል የሆነው ለአንደኛው ደግሞ ከብዶ ተራራ ይሆናል፡፡ አስተዋይ ብቻ ይኼንን ይረዳል። ሁሉም በመሰለው መንገድ እንደ መሰለው ይሮጣል፡፡ መንገድ ነውና። የተሸወደው ወደ ኋላው ለመራመድ ዋጋ እየከፈለ፣ መስመሩን ያገኘው ደግሞ ወደ ፊት እየገሰገሰ ያመለጠውን ለመጨበጥ፣ የሌለው ለማግኘት፣ ያለው ደግሞ የበለጠ ለማካበት ሩጫ በሩጫ ሆኗል። ጎዳናው በገስጋሾች ታጭቋል። አልፎ አልፎ የቆመ አይጠፋም። አንዳንዱ ነዳጅ እንደ ጨረሰ መኪና አቅሙን አሟጦ ከመንገድ ቆሟል። በሞትና በሕይወት መካከል ውስጡን ማንም ሳያውቅለት። ሌላው በቸልታ ‘ለማን ብዬ?’ ብሎ የሰው አጥር ተደግፎ፣ አልያም የካፌ ወንበር አጣብቦ ጥርሱን እየፋቀ አቃቂር ያወጣል። ሳይታገል እየደከመው፣ እየሰለቸው። ይህም የሕይወት አንዱ አካል ይባላል!

‹‹የመረጃ እጥረት ብሎ ብሎ ታክሲ ተራ ገባ?›› ቢል አንድ ወጣት ተሳፋሪ፣ ‹‹ከላይ ከተጀመረ ወደ ታች መውረዱ መቼ ሊከብድ?›› ሲል አዋዝቶ መሀል መቀመጫ ላይ የተቀመጠ ጎልማሳ መለሰ። ‹‹ሰው ምን እንደሚታየው እንጃለት ታክሲ ሲሳፈር የአሜሪካን አፈር የረገጠ ይመስለዋል እኮ…›› ይለዋል አንድ ጎልማሳ አብሮት ለሚጓዘው ጓደኛው። ‹‹የዘንድሮዋን አሜሪካ እንዲህ እንደ ዋዛ መርገጥ አለ ብለህ ነው? አሁንማ እንኳን እኛ ወደ አሜሪካ ልናንጋጥጥ እዚያ ያላችሁትም ብትመጡ ይሻላችኋል እየተባለ እኮ ነው…›› ሲለው፣ ‹‹የአሜሪካን ጉዳይ ለአሜሪካና ለአሜሪካውያን ትተን የራሳችን ጊዜ የማይሰጡ ጉዳዮች ላይ ብንረባረብ የሚሻል መሰለኝ…›› አለው። የአሜሪካ ነገር ሲነሳ ጆሮአችን የተቀሰረ ሁሉ ነገሩ ወዴት እያመራ እንደሆነ ገባን መሰል ቀዝቀዝ ስንል እናስታውቅ ነበር፡፡ ‹‹አሜሪካማ በግብረ ሰዶማውያንና በፆታ ቀያሪዎች ተወራ የዲያቢሎስ መንደር መስላለች…›› እያሉ አንዲት እናት በለሆሳስ ሲናገሩ ሰማኋቸው፡፡ ሌሎች አልሰሙም መሰል ነገሩ በዚሁ ተቋጨ፡፡ መዓት ምኑ ያስደስታል ድሮስ!

‹‹በአስከፊ የኑሮ ውድነትና በሰላም ዕጦት ውስጥ እየኖርን ተመሥገን እያልን ውለን ከማደር ውጪ ሌላ ምን አማራጭ አለን ብለህ ነው?›› ከኋላ ጥጉን ይዞ የተቀመጠ ጎልማሳ በስልክ ሲያወራ እንሰማዋለን። ‹‹እውነትህን ነው ወንድሜ ዘንድሮ ከአምላካችን ዘንድ ካልሆነ ከሰው መጠበቅ የከንቱ ከንቱ ነው፡፡ የሰዎችን ከንቱ ሐሳብ ተከትለን መሰለኝ መከራ የምንበላው…?›› ትላለች ከጎኔ የተቀመጠች ወይዘሮ። ‹‹እኛ ልክ እንደ ሰዎቹ የራሳችን አጀንዳ ላይ ስለሆንን መስሚያ የለንም…›› ይላል ወያላው እያሾፈ። ‹‹አንተን ማን ጠየቀህ?›› ትላለች ወይዘሮዋ። ‹‹እኔ እኮ የሚገርመኝ ድህነትን ማሸነፍ የሚቻለው በመሥራት ነው ወይስ በየጥጋ ጥጉ ተወዝፎ ነገር ሲበሉ ውሎ በማደር ነው? አንዱ ሲሠራ ሌላው አላሠራ ካለ፣ ይኼኛው ቀና ሐሳብ ሲያቀርብ ያኛው ለማዳመጥ ፈቃደኛ ካልሆነ፣ ይህች እህቴ በረባ ባልረባው ከምንነታረክ እስቲ በወጉ እንነጋገር ሰትል እኔ ጀርባዬን ከሰጠኋት ስለየትኛው ዕድገት ነው ማውራት የምንችለው?›› ሲል፣ ‹‹ፉከራና ቀረርቶ እንጂ እሺ ባይነትና ቅንነት ስላለመደብን አይመስልህም?›› አለው ጎልማሳው። ‹ስንቱን አሳለፍኩት ስንቱን አየሁት…› ይላል የትዝታው ንጉሥ መሐሙድ አህመድ በዚያ በሚያምር ቅላፄው ከወደ ስፒከሩ፡፡ ያሰኛል!

አዛውንቱ ሾፌር እስከ ኋለኛው መቀመጫ ድረስ በሚሰማ ሳቃቸውና ድምፃቸው ጋቢና ከተቀመጡት ተሳፋሪዎች ጋር ጨዋታ ጀምረዋል። ‹‹አቤት ዘንድሮ ፀሐይዋ ገና ብቅ ከማለቷ አቅለጠለጠችን። እኔ ድሮ የከባድ መኪና ሾፌር ነበርኩ። የአገሬን በረሃ በሙሉ አውቀዋለሁ እል ነበር። ነገር ግን ውሸት ሆኖ አገኘሁት። ይኼ ዘመንማ ለእንደኛ ዓይነቶቹ ሽማግሌዎች ስንቱን መሰላችሁ ውሸት ያደረገብን? ሃ…ሃ…ሃ…›› እያሉ ይስቃሉ ለራሳቸው። ድንገት ደግሞ ኮስተር ብለው መሀል ላይ ያለውን ቀጭን ጎልማሳ አስተዋሉት። ፊታቸውን እንዴት እንዴት እንደሚያደርጉት እያየን በቀልዳቸው መገረም ከመጀመራችን፣ ‹‹አንተ እንዴት እስካሁን የራስህን መኪና ሳትገዛ ቀረህ?›› አሉት ልክ እንደሚያውቁት ሁሉ። አልፎ አልፎ መንገዱ ሲለቀቅ አንደኛ ማርሽ በጭንቅ ለማስገባት ካልሆነ በቀር ፊታቸውን ከሁለቱ ተሳፋሪዎች አይመልሱትም። ‹‹ፋዘር መኪና እንደሌለኝ እንዴት አወቁ?›› ሲላቸው፣ ‹‹ወይ ጉድ ይህቺ ይህቺ መቼ ትጠፋናለች? መኪና ቢኖርህ ኖሮ ይህች አሮጌ ታክሲ ላይ ለምን ትሳፈር ነበር?›› ሲሉት፣ ‹‹ፋዘር ገቢያችንን ከፔይሮል እስከ ካፌ ማኪያቶ ድረስ በግብር እያስመታን ኑሮ ከብዷል፡፡ እንኳንስ መኪና ልገዛ ለቤት ኪራይና ለቀለብ በመከራ ነው፡፡ እኛ የቅጥር ሠራተኞች ሲስተሙ ውስጥ ሆነን በተደራራቢ ግብር ስንመታ፣ ግብር ሰዋሪዎችና አጭበርባሪዎች በሽልማት የሚንበሻበሹበት አገር ውስጥ መኖር ራሱ ያስጠላል…›› ሲላቸው በንዴት መሪውን ጠለዙት፡፡ ወይ ምሬት!  

ሁለት ተሳፋሪዎች ወርደው በምትካቸው አራት ተጫኑ። ሾፌሩ በመስኮቱ አሻግረው በተቃራኒ አቅጣጫ የሚመጣ ባለታክሲ መንገድ ላይ የትራፊክ ፖሊስ መኖር አለመኖሩን ጠየቁት። ‹‹የለም…›› ብሎ መለሰላቸው። ‹‹በል ጫን በደንብ…›› ሲሉት ወያላውን፣ ‹‹ለማን አቤት ይባላል? ቢባልስ እስካሁን ያልነው አይበቃም ነበር?›› ይላል ጎልማሳው። ጠይሟ ቆንጆ ወጣት በበኩሏ፣ ‹‹ሹማምንቱ እንኳን ተነግሯቸው ላያቸው ላይ አስተዳደር ቢገነባባቸውም አይነቁ…›› ትላለች። የሚስቅ ይስቃል ሌላው ደግሞ፣ ‹‹ኧረ አሁንም በግምገማ ላይ ነን እህት?›› ይላታል። ‹‹ተስፋ መቁረጥ የለም…›› ብሎ አንድ ድምፅ ሲጮህ ሁላችንም ዞረን አየነው። ሙሉ ልብስ ነው የለበሰው። በእጁ የላፕቶፕ ቦርሳ ይዟል። ‹‹በሚቀጥለው ምርጫ እኔን ከመረጣችሁኝ ችግራችሁን ሁሉ ገደል ነው የምሰደው…›› ብሎ ከወዲሁ ቅስቀሳውን ጀመረ። ‹‹እሺ ፖለቲከኛው ለመሆኑ ለሚቀጥለው ምርጫ ተዘጋጅተሃል ወይስ እንደ ስመ ዴሞክራቶች ወይ በምርጫ ካልሆነም በዱላ እያልክ ይሆን…›› አንዱ አላጋጭ ነገር ወጋ ያደርጋል። ሊጀመር ነው!

ሰውዬው ወዲያው ለመጪው ምርጫ ዕጩ የግል ተወዳዳሪ ለመሆን ማሰቡን ነገረን። ‹‹ለመሆኑ…›› አለው አንድ ተሳፋሪ፣ ‹‹… ለመሆኑ እንዴት ብለህ ነው የታክሲ ሠልፍን ብሎም ዕጦትን እስከ እነ አካቴው ልታስረሳን የምትችለው? መቼም እንደ አሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ሠልፈኛው እንዳይታይ ግንብ እገነባለሁ እንደማትለን ተስፋ አደርጋለሁ…›› ሲለው ሙሉ ፈገግታ ፊቱን ወርሶት፣ ‹‹ይኼማ ቀላል ነው፣ አያችሁ ብዙዎቻችን ከእንቅስቃሴ ጋር ተቆራርጠናል። ጠንካራና ጤናማ ዜጋ ለአንድ አገር ህልውና ወሳኝ ነው። ጠንካራና ጤነኛ ኅብረተሰብ የአገሩን ዳር ድንበር ከማስከበር አልፎ በጥሩ ሁኔታ ሳይደክመው እየሠራ ጥሩ ግብር ከፋይ ይሆናል። ስለዚህ የታክሲ ችግርን መቅረፍ የሚቻለው በእግር ለመሄድ ስንወስን ነው። ጤናችሁንና ገንዘባችሁን ገና በብዙ ጉዳዮች ዙሪያ ስለማተርፍላችሁ ግድ የለም እኔን ብትመርጡ ታተርፋላችሁ፣ አመሠግናለሁ…›› ሲል ታክሲዋ ደም በለበሱ ዓይኖች በሚያፈጡ ንዴት በሚያቁነጠንጣቸው ተሳፋሪዎች ተሞላች። ‹‹አይ ምርጫና አልጫ…›› የሚሉት አዛውንቱ ነበሩ። እውነታቸውን ነው! 

ወደ መዳረሻችን ተጠግተናል። ወያላው አንገቱን ለረጅም ጊዜ ወደ ውጭ አስግጎ ከቆየ በኋላ ወደ ውስጥ መለስ ብሎ፣ ‹‹እኔምለው ሀቀኛ ግብር ከፋዮች ሲሸለሙ ዓይናችን ደም ለምን ይለብሳል? እነዚህን ዓይን የሚያጥበረብሩ ምርጥ ሕንፃዎች የገነቡልን እነሱ አይደሉም እንዴ?›› ከማለቱ፣ ‹‹ድንቄም ዓይን ማጥበርበር፣ ማጠናገር ብትል አይሻልህም እንዴ? ከዱባይ በሚያግበሰብሱት መናኛ መስታወትና አሉሚኒየም ዓይናችንን ማንሸዋረራቸው ሳያንስ በሙቀት አዲስ አበባን የመሰለች ነፋሻ ከተማ እያነደዱልን ነው፡፡ ሌብነቱንማ ተወው፡፡ በቀደም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው ከጥቂት ምሥጋና ቀጥሎ ባለሥልጣኖቻችንን አታባልጉ ሲሉ መቼም አልሰማንም አይባልም፡፡ ይህንን ለምን አሉ መሰላችሁ፣ የዘንድሮ ባለሥልጣንና ባለሀብት አንድ ላይ እንደሚነግድ ስለሚታወቅ ነው፡፡ የኮንትሮባንዱንና የግብር ማጭበርበሩማ አይነሳ…›› ስትል አዲስ አጀንዳ ዘርግታ እጃችንን አፋችን ላይ አስጫነችን፡፡ ‹‹እኛ ግን በሌሎች ኃጢያትና ክፋት እስከ መቼ ስንሳቀቅ እንኖራለን?›› የሚሉት እኛ እናት ናቸው፡፡ አሁንም በለሆሳስ ነው የተናገሩት፡፡ ምን ያድርጉ ታዲያ!

‹‹ይህንን ሁሉ ወግ ስትሰልቁ ምነው ስለፍልስጤምና ስለእስራኤል መነጋገር ፈራችሁ?›› ብሎ ያ ነገረኛ ወያላ አዲስ ሐሳብ ሲያነሳ፣ ‹‹እኛ የሁለቱንም ወገኖች ጉዳት በሰብዓዊ ርኅራኄ በመመልከት ሰላም እንዲሰፍን ነው ማሳሰቢያ መስጠት ያለብን፡፡ የውጭ እጅ ገብቶባቸው ዝንተ ዓለም ሲፋጁ ቢኖሩም ከሁለቱ በላይ የሚቀራረብ ማንም አይኖርም ነበር፡፡ የእኛ ሚና መሆን ያለበት ፖለቲከኞች በሰከነ መንገድ ንፁኃን የሚማገዱበትን የዕብደት ጦርነት እንዲያቆሙ ግፊት ማድረግ ይበጃል፡፡ ከዚያ ውጪ ያለው አጉል ወገንተኝነት ከፍጅትና ከውድመት የዘለለ ፋይዳ የለውም…›› እያለ አንድ ረጋ ያለ ወጣት ሲናገር ሁላችንም አገራችንን ያለችበትን መከራ እያሰብን ነው መሰል በዕርጋታ ነበር የሰማነው፡፡ ‹‹ልጄ መልካም ቁምነገር ተናገርክ…›› ብለው እኚያ እናት ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፃቸውን በጉልህ አሰሙ፡፡ ‹‹…ልጄ ተባረክ፣ ‹የዕብድ ገላጋይ ዱላ ያቀብላል እንደሚባለው› ነገረ ሠሪ በዝቶ ነው የአንድ አያት ልጆች ለብዙ ዓመታት የሚጋደሉት፡፡ አሁንማ ጭካኔው በዝቶ ሽብርተኝነት ነው የነገሠው፡፡ ለማንኛውም ለእኛም ሆነ ለሌሎች ፈጣሪ ሰላሙን ይስጠን፣ ከፈጣሪ በስተቀር ማንም እውነተኛ ፈራጅ የለም…›› እያሉ ‹‹መጨረሻ!›› ተብለን ተሸኘን፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት