(ክፍል አንድ)
በተሾመ ብርሃኑ ከማል
መንደርደሪያ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ዓርብ ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የቀይ ባህር ጉዳይን በሚመለከት 45 ደቂቃ ያህል የወሰደ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባህርና ህንድ ውቅያኖስ ለመውጣት የሚያስችላትን በር መጠየቋ አግባብነት እንዳለው ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ወደ ኤርትራና ሱዳን ተከዜ፣ ወደ ግብፅና ሱዳን ዓባይ፣ ወደ ደቡብ ሱዳን ባሮ፣ ወደ ኬንያ ኦሞ፣ ወደ ሶማሊያ ደግሞ ገናሌ፣ ዳዋና ዋቢ ሸበሌ ወንዞች ከኢትዮጵያ ተነስተው እንደሚጓዙ፣ ወደ ጂቡቲ የውኃ መስመር በኢትዮጵያ ወጪ መገንባቱን አውስተው ኢትዮጵያ ከእነዚህ አገሮች አንዳቸው እንኳን “ለኢትዮጵያ ንፁህ ውኃ የሚሰጥ የለም፣ ሁሉም ተቀባይ ነው፤›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ የእናንተን እንካፈል የእኛን አትጠይቁ ማለት ግን ትክክል አይደለም፤” በማለት ተናግረዋል።
መስከረም 10 ቀን 2016 ዓ.ም. ‹‹የቀይ ባህር የደኅንነት ሁኔታ ቀጣናዊ ምክክርና ትብብር መልከዓ ፖለቲካዊ መጠላለፍ በበዛበት ዓለም ወቅት›› በሚል ርዕስ በተዘጋጀ ጉባዔ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ካደረጉ የተመረጡ የውጭ ዲፕሎማቶች ተወካዮች፣ የዘርፉ ተዋንያን፣ የመንግሥት ተቋማት ተወካዮች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችና ሌሎች ተጋባዦች በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል፡፡ በውይይቱ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላትን አገር ወደብ አልባ ማድረግና በቀይ ባህር ቀጣና ላይ በሚከናወኑ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች ማግለልን በዝምታ ማለፍ ለመጪው ትውልድ ፈተና ጥሎ መሄድ ነው ያሉት እንድሪስ መሐመድ (ዶ/ር)ናቸው፡፡ ‹‹ከዚህ በፊት የነበረው የእኔ ትውልድ አገሪቱን ወደብ አልባ ያደረጋትን ስህተት ማናቸውም አማራጮች በመጠቀም መፍትሔ ሊያመጣ የሚችል ሥራ መሥራት ይገባዋል፤›› ብለዋል፡፡ ወደብ የማግኘት ጉዳይ አማራጭ የሌለው በመሆኑ በሰጥቶ በመቀበል፣ ከዚያም ካለፈ የኃይል አማራጮችን የመጨረሻ መንገድ ማድረግ እንደሚያስፈልግ እንድሪስ (ዶ/ር) አስረድተው ነበር፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መሳፍንት ተፈራ፣ ከቀይ ባህር ፖለቲካ ኢትዮጵያን አግልሎ መቆየት የማይቻል በመሆኑ ማናቸውም ቀይ ባህርን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ ሚና ልትጫወት ግድ ይላታል ብለዋል፡፡ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት አገር በፀጥታ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በደኅንነት ወይም በሌላ ጉዳይ እያደገ ከሚመጣው ፍላጎት ጋር ከቀይ ባህር ውጪ መንቀሳቀስ የማይቻላት በመሆኑ፣ በዚህ ቀጣና በማንኛውም ኢትዮጵያን ተሳታፊ ሊያደርግ የሚችል ጉዳይ ላይ ተሳታፊ መሆኗን ማረጋገጥ እንደሚገባት አብራርተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይም ሆኑ የውጭ ጉዳይ ባለሥልጣናት ስለቀይ ባህር ወደብ ተጠቃሚነት ሲነግሩን፣ ስለቀይ ባህር ጂኦ ፖሊቲክስ አደገኛ ሁኔታም እየጠቆሙን ነው የሚል ግምት አለኝ፡፡ ለመሆኑ የቀይ ባህር ጂኦ ፖሊቲክስ ማለት ምን ማለት ነው? በቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲክስ ዙሪያ የተሰባሰበው ኃይል ምን ያህል ነው? ለምን ስለቀይ ባህር ፖለቲካ እንናገራለን? ኢትዮጵያ ለምንና በምን ሕግ የቀይ ባህር መግቢያ በር ማግኘት ትችላለች? የቀይ ባህር ታሪካችን ምን ይመስላል? በዚህ አምስት ክፍል ያለው ጽሑፍ እነዚህና እነዚህን የመሳሰሉ ዓበይት ጉዳዮች ይቀርባሉ፡፡ በቅድሚያ ጂኦ ፖለቲካ ማለት ምን ማለት ነው?
ጂኦ ፖለቲካ ማለት ምን ማለት ነው?
በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም ከሚስተጋቡት ቃላት አንዱ ‹‹ጂኦ ፖለቲካ›› መሠረታዊ ወይም ዕሳቤያዊ ቃል ነው፡፡ ‹‹ጂኦ ፖለቲካ›› አንድ የተወሰነ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ያለው አካባቢ በሚገኝበት ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊና ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለው፣ የአካባቢው፣ የአውሮፓ፣ የእስያና የአሜሪካ አገሮች በባህር መስመሩ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ኃይላቸውን የሚያሠልፉበት፣ አንዱ የሌላው ሥጋት በመሆኑ በዓይነ ቁራኛ የሚተያይበት፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የጦር መሣሪያ የሚማዘዝበት፣ የፖለቲካዊ ውዝግብ አውድማ ሊባል የሚችል ነው፡፡ ቀደም ሲል ስለጂ ኦፖሊቲክስ ሲወሳ ‹‹ስትራቴጂካዊ የባህር መስመር›› የሚል ሐረግ ተጠቅሷል፡፡ ትርጉሙም አካባቢው ከአንድ የገበያ ቦታ ተነስቶ ሌላ የገበያ ቦታ ለመድረስ መስመር የሚያደርስ፣ አካባቢው ለቀጥታና እጅ አዙር ቅኝ ግዛት አመቺ ለመመሥረት ተፈላጊ የሆነ፣ አካባቢው ለንግድ ወይም ለጦር ሠራዊት መተላለፍ ባለው ጠቀሜታ ከመሆን ጋር ባለው ምክንያት መጠበቅ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ እንደማለት ነው፡፡
በሜዲትራንያን፣ በቀይ ባህርና በህንድ ውቅያኖስ አካባቢ የሚገኙ የንግድ መስመሮች ወደ ሀብት ምንጭ አገሮች ስለሚወስዱ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የዓለምን ትኩረት እንደሳቡ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ጥንታዊ ግሪኮችና ጥንታዊ ሮማውያንም ከሜዲትራንያን ባህር እስከ ህንድ ውቅያኖስ ድረስ የነበራቸውን ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ትስስር ጽፈዋል፡፡ ጥንታዊ ግብፆችና ሐበሾችም በቀይ ባህር የንገድ መስመር የበላይነት በታሪክ ማኅደራቸው አስፍረዋል፡፡ ጥንታዊ ህንዶችና ቻይናዎች ከህንድ ውቅያኖስ እስከ ሜዲትራንያን ባህር ድረስ የነበራቸውን የንገድ መስመር ዘግበዋል፡፡ በሁሉም አገሮች ኮስማስ ኢንደፕሊከስ፣ እንደ ኤርትራ ባህሩ ፐሪፕለስ ጸሐፊዎች፣ ቀራፂያን ስለጥንታዊው የንግድ መስመር መረጃዎችን ለዚህ ትውልድ አስተላልፈዋል፡፡ እንደ ታላቁ እስክንድር፣ እንደ አውጉስቶስ ቄሳር፣ ፕቶሎሚ፣ ንግሥት ሐትሸፐስት፣ ካሌብ፣ ያሉት መሪዎችም ስማቸው ከዚህ ስትራቴጂካዊ ሥፍራ ጋር ያነሳል፡፡
በዓለም ላይ በርካታ በከፍተኛ የወታደር ኃይል የሚጠበቁና እንደ ዓይን ብሌን የሚታዩ የባህር በሮች ሲገኙ ዓላማቸውም የንግድ፣ የሰውና የጦር መሣሪያ መርከብ መተላለፊያ መስመር ሆኖ ማገልገል ነው፡፡ ከማታውቁት የንግድ መስመሮች መካከል ውስጥ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡
- ጂብራተር መተላለፊያ አትላንቲክ ውቅይኖስንና ሜዲትራኒያን ባህርን ያገናኛል፣
- ሆርሙዝ ‹‹HORMUZ›› የባህር መተላለፊያ መስመር ፐርሺያ ባህረ ሰላጤንና ኦማን ባህረ ሰላጤን የሚያገናኝ ሲሆን፣ ሆርሙዝ በዓለም ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ካላቸው የባህር መስመሮች ግንባር ቀደሙ ነው፣
- ባብኤል መንደብ ‹‹BAB-EL-MANDAB›› ቀይ ባህርንና የኤደን ባህረ ሰላጤን እንዲሁም አፍሪካንና እስያን የሚያገናኝ፣
- ማላካ ‹‹MALACCA›› የባህር መተላለፊያ መስመር ህንድ ውቅያኖስንና ፓሲፊክ ውቅያኖስን የሚያገናኝ ረጅሙ የባህር መስመር ‹‹በር›› ማላካ ሲሆን ይህም 800 ኪሎ ሜትር ርቀት አለው፣
- ዳርዳነለስ ‹‹DARDANELLES›› የባህር መተላለፊያ መስመር ኢስያዊቷን ቱርክና አውሮፓዊቷን ቱርክ፣ እንዲሁም ጥቁር ባህርን ከሜዲትራንያን ባህር ጋር የሚያገናኝ፣
- ታርታር ‹‹TARTARY/TARTAR›› የባህር መተላለፊያ መስመር ሩሲያን ከእስያ የሚያገናኝ መስመር፣
- ታይዋን ወይም ፎርሞሳ ‹‹TAIWAN STRAIT OR FORMOSA STRAIT›› የባህር መተላለፊያ መስመር ታይዋንና ቻይናን የሚያገናኝ መስመር፣
- ሞዛምቢክ የባህር መተላለፊያ መስመር ‹‹MOZAMBIQUE STRAIT›› በሞዛምቢክና በማዳጋስካር መካከል የሚገኝ መስመር፣
- ዩካታን የባህር መተላለፊያ መስመር ‹‹YUCATAN STRAIT›› ሜክሲኮንና ኩባን የሚያገናኝ፣
- ፍሎሪዳ የባህር መተላለፊያ መስመር ‹‹FLORIDA STRAIT›› ኩባንና አሜሪካን የሚያገናኝ፣
- ሀድሰን የባህር መተላለፊያ መስመር ‹‹HUDSON STRAIT›› ሀድሰን ባህረ ሰላጤንና ላብራዶር ባህርን የሚያገናኝ፣
- ታረስ የባህር መስመር ‹‹TORRES STRAIT›› ፓስፊክ ውቅያኖስ የሚገኝ ሲሆን በኒውዮርክ ኬፕ ሰላጤና በአውስትራሊያና በፓፑዋ ኒው ጊኒ መሀል የሚገኝ፣
- ማጅላን የባህር መስመር ‹‹MAGELLAN STRAIT›› ደቡብ አሜሪካን ከበስተደቡብ ጫፍ በኩል የሚያስተላልፍ [An archipelago off the southern-most tip of the South American Mainland]፣
- ዳቨር ‹‹DOVER STRAIT›› እንግሊዝን ከተቀረው አውሮፓ ጋር የሚያገናኝ የባህር መስመር ነው፡፡
ስለቀይ ባህር ‹‹በር›› መስመሮች ጠቃሚ መረጃዎች
የቀይ ባህር በር አፍሪካን ከአውሮፓና ከእስያ ጋር፣ በባብኤል መንደብና ኤደን ባህረ ሰላጤ ደግሞ ከህንድ ውቅያኖስ ጋር ይገናኛሉ፡፡ ቀይ ባህር በሰሜን ከሲናይ ባህር ወሽመጥ፣ ከዓቃባ ባህረ ሰላጤና ከስዊዝ ካናል ጋር ይዋሰናል፡፡ የአፍሮ ኤሽያ ስምጥ ሸለቆ አካል ነው፡፡ ስፋቱ 438,000 ካሬ ኪሎ ሜትር ያህላል፡፡ አማካይ ጥልቀቱ 490 ሜትር ነው፡፡ የሚገኘው በምሥራቅና በሰሜን አፍሪካ እንዲሁም በምዕራብ እስያ ነው፡፡ ከጫፍ እስከ ጫፍ ‹‹ከሰሜን እስከ ደቡብ ርቀቱ 2,250 ኪሎ ሜትር ወይም 1,400 ማይልስ ነው፡፡›› በሉል ላይ 22° ሰሜን 38° ምሥራቅ/22° ሰሜን 38° ምሥራቅ ይገኛል፡፡ በአካባቢው የሚገኙ አገሮች ከአፍሪካ ግብፅ፣ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ጂቡቲ፣ ሶማሊያ ሲሆኑ ከሰሜን በሲናይ በኩል ሊባኖስ፣ እስራኤል፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የመን ናቸው፡፡ በውስጡ ከሚገኙ ደሴቶች ፐሪም፣ ጀበል አልጣሂር፣ ሐኒሽ፣ ሮኪ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
በቀይ ባህር አካባቢ ያሉ ዋና ዋና አሥር ወደቦች
- ጂዳ ወደብ ‹‹ሳዑዲ ዓረቢያ›› 56 በመቶ ዕቃ የሚጫንበትና የሚራገፍበት፣ 7.5 ሚሊዮን ቶን የመያዝ አቅም ያለው፣ የልዩ ልዩ ዕቃዎች፣ የመኪና፣ የነዳጅ መርከቦች የሚያርፉበት፣
- ያንቡ ወደብ የሳዑዲ ዓረቢያ ወደብ ስትሆን ከዶሃ በስተደቡብ ትገኛለች፡፡ ርዝመቷም ሁለት ኪሎ ሜትር ያህላል፡፡ በአንድ ጊዜ 12 ያህል መርከቦችን ታስተናግዳለች፡፡ 13.5 ቶን የሚጫንባትና የሚራገፍባት ናት፡፡ ከመካና ከመዲና ጋር በመንገድ ትገናኛለች፡፡
- ሳጋፋ ከግብፅ ወደቦች አንዷ ናት፡፡ የፎስፌት ማዕድን የሚጫንባት፣ በየዓመቱ ብዙ ቱሪስቶች የሚስተናገዱባት ናት፡፡ አምስት የመርከብ ማሪፊያ ጣቢያዎች አሏት፡፡
- ኤየላት ወደብ ከኢስራኤል ወደቦች አንዷ ስትሆን ከቀይ ባህር ጋር የምትገናኘውም በዓቃባ ባህር ወሽመጥ በኩል ነው፡፡ እስከ 300,000 ቶን ነዳጅ ይመላለስባታል፡፡ ሌሎችም ጭነቶች ይጫኑባታል፣ ይራገፉባታልም፡፡
- ፖርት ሱዳን ምሥራቅ፣ ምዕራብና ደቡብ ተብለው የሚጠሩ ክፍለ ከተሞች የሚጠቃለሉበት፣ ከአሥር በላይ የኮንቴይነር መከማቻ ያሉት፣
- ጂቡቲ ወደብ በአብዛኛው ኢትዮጵያን የሚያገለግል ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ዶራሌ ወደብ ተጨምሯል፡፡
- ምፅዋ ወደብ፣ የኤርትራ ሲሆን ይህም ወደብ ከዙላ ወደብ በስተሰሜን ይገኛል፡፡ አገልግሎቱ ለጭነት መርከቦች ማረፊያ ነው፡፡ በዚህ ወደብ በአማካይ ከ300 በላይ የሆኑ መርከቦች አቋርጠው ያልፋሉ፡፡
- አሰብ ወደብ በኤርትራ ከሚገኙ ወደቦች ሁለተኛዋ ስትሆን 95 በመቶ አገልግሎቱ ለኢትዮጵያ ነው፡፡ በአሰብ ወደብ ሰባት የመርከብ ማረፊያዎች ሲኖሩ አንዱ የመኪና፣ ሁለተኛው የነዳጅ የተቀሩት የዕቃ መጫኛዎች ናቸው፡፡
- ሁደይዳ ወደብ ከደቡብ ሳዑዲ ዓረቢያ የምትዋሰን የየመን ከፍተኛ ወደብ ናት፡፡ 5,700,000 ቶን ጭነት ይጫንና ይራገፍባታል፣ 1,000,000 ቶን ነዳጅ ይመላለስባታል፡፡
- ኤደን ወደብ ሁለተኛዋ የየመን ወደብ ስትሆን ቀይ ባህርና ባብኤል መንደብ ይገናኙባታል፡፡ ዘጠኝ የመርከብ ማረፊያዎች ሲኖሯት፣ በዓመት እስከ 2,000 ያህል መርከቦች ልዩ ልዩ ዕቃዎችን፣ እንስሳትን፣ ኮንቴይነሮችን፣ ነዳጅን ጭነው ይመላለሱባታል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ከአሜሪካ፣ ከእንግሊዝ፣ ከፈረንሣይና ከጀርመን ሌላ የቀይ ባህር የንግድ መስመርን ለመቆጣጠር የሚፈልጉ አገሮች ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት የዓረብ ኢሚሬት፣ ግብፅ፣ ቱርክ፣ ቻይና፣ ጃፓን፣ ሩሲያ፣ ኢራን፣ እስራኤል ይገኙበታል፡፡
የአፋር ሕዝብ በአፋር ሦሰት ማዕዘናዊ ግዛት ተብሎ በሚታወቀው ስምጥ ሸለቆ የሚገኘውን ግዛትንና ነዋሪውን ይወክላል፡፡ ይህም ሕዝብ በኢትዮጵያ፣ በጂቡቲና በኤርትራ ይገኛል፡፡
ቀይ ባህርና የኢትዮጵያ ጥቅም
ኢትዮጵያ ከጥንት ዘመን ጀምሮ የቀይ ባህር የባህር መስመር ተጠቃሚ እንደሆነች በርካታ መረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል ጥቂቶቹን በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ለማካተት ይደረጋል፡፡ ይህም እንደ ሚከተለው ቀርቧል፡፡
ኢትዮጵያ በጥንታዊ ስሟ ፑንት ‹‹የዚያኔዋ ሐበሻ›› በቀይ ባህር የበላይነት ያሰፈነችው መች እንደሆነ ባይታወቅም በታሪክ ተመዝግቦ የሚገኘው ከ3407-2888 ዓ.ም. በነበረው ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ግብፆች ከኢትዮጵያ ሸቀጦች የበለጠ የሚፈለጉት መልካም መዓዛ ያለው ዕጣንና ከርብ ነበር፡፡ ከ2708-2697 ዓ.ም. በሥልጣን ላይ የነበረው ግብፃዊ ንጉሥ ሳሁር ወደ ኢትዮጵያ በመርከብ በመምጣት መለኪያው ምን እንደሆነ ባይገለጽም 80 ሺሕ ‹‹ስልቻ›› ከርቤ፣ 2,600 ያህል ውድ መልካም ሽታ ያላቸው ‹‹ምናልባት ቡከቡባ›› አጣናዎች፣ ስድስት ሺሕ ወርቅ ይዞ ወደ አገሩ ተመልሷል፡፡ ከ2271-2112 ዓ.ም. የነገሠው ሜንቱሆተፕ ዳግማዊ፣ ሄኑ የተባለውን ዓቃቤ ንዋዩን ያኔ «የእግዚአብሔር አገር» ትባል ወደ ነበረችው ኢትዮጵያ በመርከብ በመላክ ጊዜ ያላለፈበትን ከርቤ ከዚያው ከምንጩ እንዲያመጣለት አድርጓል፡፡ ከ1501-1479 ዓ.ም. የነበረችው የግብፅ ንግሥት ሐትሸበፐስት በ1495 ዓ.ም. ኢትዮጵያን ስትጎበኝ የከርቤ ዛፍ፣ ብዙ ከረጢት ከርቤ፣ የዝሆን ጥርስ፣ ትልልቅ ጦጣዎች፣ ወርቅ ከዚያ ወደ አገሯ ተመልሳለች፡፡ በመሠረቱ የንግድ መርከብ ይዘው የሚመጡና የሚፈልጉትን ሸቀጥ ይዘው የሚመለሱት ግብፃውያን ብቻ አልነበሩም፡፡ ኢትዮጵያውያንም ወደ ግብፅ በመሄድ በወቅቱ የነበረውን ሸቀጥ ይዘው ይመለሱ ነበር፡፡ ከእነዚህም መካከል በአፄ አሜን ሆቴፕ ዳግማዊ ዘመነ መንግሥት ‹‹1447-1420 ዓ.ም.›› ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች ወደ ግብፅ ሄደዋል፡፡ የዚያን ጊዜ የነበሩት የኢትዮጵያ መርከቦች ከኋላና ከፊት ክብ፣ ቀለማቸው ሐምራዊና ምሰሷቸው ትልቅ ነበሩ፡፡ የጥንት ግብፃውያን ታሪክ እነደሚነግረን የንጉሥ ሰለሞን ‹‹973-930›› መርከቦች ከርቤ፣ ዕጣን፣ የከርቤ ዛፍና የከበረ ድንጋይ ለመግዛት ወደ ኢትዮጵያ ‹‹አፋር›› መጥተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ በሳልሳዊ ፕቲለሚ ‹‹305-285 ዓ.ም.››፣ በቀዳማዊ ኢርገተስ ‹‹246-221 ዓ.ም.›› ግብፃውያን ከኢትዮጵያውያን ጋር ይነግዱ ነበር ‹‹ሪቻርድ ፓንክረስት፣ ዘ ኢትዮጵያን ቦርደርላነድስ፣ ገጽ 3-21››፡፡
ዴቪድ ሃሚልተን የተባሉት የታሪክ ተመራማሪ እ.ኤ.አ. በጁላይ 1967 በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር መጽሔት ቅጽ 5 ቁጥር 2 ላይ ‹‹ኢምፔሪያሊዝም ኢንሸት ኤንድ ሞደርን‹‹ በሚል ርዕስ እንዲህ በማለት አሥፍረዋል፡፡
በሦስተኛውና በአራተኛው ክፍለ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ የአክሱም አፄያዊ መንግሥት ግዛቱን እስከ ደቡባዊ ምዕራብ ድረስ አስፋፍቶ ነበር፡፡ በዚህም ዘመን አይላ ወይም አዩላስት የተባሉት ግዛቶች በዚያኔው የአክሱም መንግሥት ሥር እንደነበሩ ሪቻርድ በርተን ‹‹ፈረስት ፋትስቴኘ ኤንድ ሊስት ኦፍ ሀካ ‹‹ለንደን 1856›› በተሰኘ መጽሐፉ በገጽ 66 ላይ አሥፍሯል፡፡
በዚህ ጊዜ የአክሱም መንግሥት ሥልጣኑን እስከ ተጠቀሰው ግዛት ሲያስፋፋ በመርከብ እየተጓጓዘና የንግድ ሥራ እያካሄደ እንደነበረ አያጠያይቅም፡፡ ኤም ፐርሐም የተባለ ታሪክ ጸሐፊ ‹‹ዘ ገቨርመንት ኦፍ ኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ በ1948 እ.ኤ.አ. ባሳተመው መጽሐፍ እንደገለጸው በስድስተኛው ምዕተ ዓመት አጋማሽ በኋላም የአክሱም መንግሥት ሠራዊት ደቡብ ዓረቢያን በመያዝ፣ ክርስትናን እንዳስፋፋና ለመንግሥቱ ተጠሪ የሆነ አካል አስቀምጦ ነበር፡፡ ሆኖም በስምንተኛው ክፍለ ዘመን እስልምና እየገነነ ሲመጣ የደቡብ ዓረቢያ ግዛት ብቻ ሳይሆን አዱሊስን በዚህም ጊዜ ቢሆን የዓረቦችና የኢትዮጵያ ሕዝቦች በመርከቦች ንግድ ልውውጥ ማድረግ መቀጠሉ አልቀረም፡፡
ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ‹‹ዘ ኢትዮጵያን ቦርደርላንድስ ገጽ 168-169›› ዓረብ ፈቂን ‹‹ሺሃበዲን›› የተባለውን የመናዊው የአህመድ ግራኝ ዜና መዋዕል ጸሐፊን ጠቅሰው እንደሚገልጹት አፄ ልብነ ድንግል ወርቅ፣ ወርሲ፣ የዝሆን ጥርስ፣ ዝባድና ባሪያ ወደ ዓረብ አገር ለሚሄዱ ነጋዴዎች ይልኩ ነበር፡፡ ሙስሊሞች ቀይ ባህርንና በምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ የነበሩትን ድንበሮች ከስምንተኛው ክፍለ ዘመን አንስተው ለሌላ አንድ ክፍለ ዘመን ያህል ሲቆጣጠሩ የአካባቢው ኀብረተሰብ የእስልምናን ሃይማኖት ተቀብሎ ከመካከለኛውና ከሩቅ ምሥራቅ አገሮች ጋር የንግድ ልውውጥ ያደርግ እንደነበር ስለሐረር ሡልጣኖች የተጻፉት በርካታ ታሪኮች ያረጋግጣሉ፡፡ ከ1468-1480 የአዳል ሡልጣኔትን ይመራ የነበረው አሚር ማህፉዝ በሸዋው አፄያዊ መንግሥት ላይ ተከታታይ ጦርነት እንዳደረገና እስከ ምሥራቅ ሸዋ ድረስ እንደ ዘለቀ ስናስታውስ፣ ከጦርነቱ ባሻገር በዘየላና በበርበራ በኩል ሸቀጥ ይገባና ይወጣ እንደነበረም መዘንጋት የለበትም፡፡ የአሚር ማህፉዝን ልጅ ያገባውና ግዛቱን ከዘይላ እስከ ሰሜን ኢትዮጵያ አስፋፍቶ የነበረው አህመድ ግራኝም ‹‹1506-1543›› በ15 ዓመት የሥልጣን ዘመኑ ዘይላንም በአጠቃሎ ይገዛ ስለነበር በሩቅ ምሥራቅና ከመካከለኛው ምሥራቅ ጋር ይደረግ የነበረው የንግድ ልውውጥ እንደቀጠለ ነበር፡፡ በእርግጥም የሐረር ሡልጣኔቶች እንደ ወርሲ፣ ቡና፣ ጥራጥሬ ዝባድና የመሳሰሉትን ሸቀጦች በዘይላ በኩል አድርገው ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የመንና ወደሩቅ ምሥራቅ አገሮች ሲልኩ በምትኩም የጨርቃ ጨርቅና ሌሎች ቁሳቁሶችን በመርከብ ያስመጡ እንደነበር በወቅቱ ሐረርን ከየመን ከነጋዴዎች ጋር ገብቶ የጎበኘው ሪቻርድ በርተን በሰፊው ያስረዳ ነበር፡፡ ዕውቁ የታሪክ ምሁር ስፔንሰር ‹‹ኢስላም ኢን ኢትዮጵያ‹‹ በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. 1965 ለንደን ባሳተመው መጽሐፉም በመርከብ በኩል የነበረውን ግንኙነት ሳይጠቅስ አላለፈም፡፡
ከ1874 ጀምሮ ቱርክ ሐረርን ስትይዝም የመርከብ ንግዱ ከእዚህ አንፃር ቀጥሎ ነበር፡፡ በዚህ ክፍለ ዘመን ቱርኮች፣ እንግሊዞችና ፈረንሣዮች ኃይል የነበሩ ሲሆን፣ ሁሉም ይዞታቸውን በቀይ ባህር አካባቢ አስፋፍተው የንግድ መርከብ ልውውጥ ለማድረግ ፍላጎት ነበራቸው፡፡ ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በዲሴምበር 1859 ‹‹ለየመን›› የተባለች መርከብ ዘይላንና ምፅዋን የጎበኘች ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ጋር የንግድ ልውውጥ ለማድረግ ፍላጎት እንደነበረው የታሪክ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የግብፁ ራዑፍ ፓሻ መረጃ ደርሶት ከሥፍራው አባረራቸው እንጂ፣ ‹‹ሩባቲኖ ስቲም ፓኬት›› የተባለ የኢጣሊያ ኩባንያ እ.ኤ.አ. በ1870 መርከቡን በአሰብ ወደብ ለማሳረፍና ራሂታ የተባለውን ግዛት በ8,200 ዶላር ለግዛት ችለው ነበር፡፡ ከዚያም ከአሥር ዓመታት በኋላ ማለትም በ1880 ላይ ግን የሩባቲኖ ኩባንያ የንግድ መርከብ በአሰብ ላይ ነበረች፡፡ ሆኖም በዚህ ጊዜ ግብፃውያን የጦር አበጋዞች ተቃውሞ አልነበራቸውም፡፡ ሰር ኤ ፔድ የተባለው እንግሊዛዊ እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 20 ቀን 1879 ለሎርድ ሳሊስበር በላከው ማስታወሻ እንደጠቀሰውም፣ ሲኞር ሩባቲኖ በተደጋጋሚ የእሱ የንግድ መርከብ በአሰብ ወደብ ላይ መገኘት ከንግድ ጋር እንጂ ከመንግሥት ጋር በፍፁም የተገናኘ አይደለም ሲል ገልጿል፡፡ ወደ ፖለቲካው መሄድ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ አይደለም እንጂ፣ እ.ኤ.አ. ሜይ 19 ቀን 1881 የኢጣሊያ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን ምንም እንኳን የሲኞር ሩባቲኖ ዓላማ በንግድ ላይ የተመሠረት ቢሆንም የግዛቷ የበላይ ግን የኢጣሊያ መንግሥት ነው ሲል መግለጫ አውጥቷል፡፡ ይህም እ.ኤ.አ. ከማርች 10 ቀን 1882 ጀምሮ የፀና ሆኗል፡፡ ስለዚህም የሲኞር ሩባቲኖ ኩባንያ አሰብ ላይ በማረፍ የመርከብ ንግድ ሥራውን በቀይ ባህርና በህንድ ውቅያኖስ አስፋፍቶ ሲሠራ መቆየቱ አንድ ሐቅ ሲሆን፣ ኢትዮጵም የዚህ ንግድ ዋና ተቋዳሽ መሆኗ የግድ ነው፡፡
ዴቪድ ሐሚልተን ወደ ጽሑፋቸው ማጠቃለያ ላይ ሲደርሱ፣ ‹‹ከጥንት ሳባውያን አንስቶ እስከ ዘመናችን ድረስ የተካሄደው የግዛት መስፋፋት ከንግድ ጋር የተያያዘ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ለምሳሌ ሎርድ ሳሊስበሪ የኤደን ወደብን ለመጠበቅ የፈለጉበትን ምክንያት ሲገልጹ ወደዛች ግዛት የምግብ አቅርቦት ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ነበር፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ በክርስትናና በእስልምና እምነት ስም የተካሄዱት እንቅስቃሴዎች ሳይቀሩ፣ ከንግድ ትርፉ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት እንዳላቸው አጠያያቂ አልሆነም፡፡
ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 1974 ላይ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር መጽሔት ቅጽ 12 ቁጥር አንድ ‹‹ዘ ባንያን ኦር ኢንዲያን ፕረዘንስ አት ማሳዋ፣ ዘ ዳህላክ አይላንድስ ኤንድ ሆርን ኦፍ አፍሪካ›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናት፣ ‹‹ፐሪፕለስ ኦፍ ዘ ኤርትሪያን ሲ›› በተሰኘው የመጀመርያው የክርስትና ምዕተ ዓመት የታሪክ መረጃ ተተንትኖ እንደምናገኘው ህንዳውያን በንግድ መርከቦች ልዩ ልዩ ሸቀጦችን ጭነው በመምጣት ከኢትዮጵያ ጋር ይነግዱ ነበረ፡፡ በወቅቱ ወደ ኢትዮጵያ ይገቡ ከነበሩት ሸቀጦች መካከል ተራ ብረት፣ ዓረብ ብረት፣ ሞቻ እየተባለ የሚጠራው የህንድ ልብስና ሌሎች በልዩ ልዩ ቀለም የተነከሩ ነዶ ጨርቆች ይገኙባቸዋል፡፡ በቅርቡ በደብረ ዳም በተደረገው የመሬት ከርሰ ቁፋሮም የብራህማን ቋንቋ የተጻፈባቸ ቀለበቶችና እ.ኤ.አ. በ2003 የተሠሩ 1ዐ3 ያህል ከወርቅ የተሠሩ ሳንቲሞች ተገኝተዋል፡፡
በ300 ዓ.ም. አካባቢም የቴብስ ምሁራን ያኔ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ወደነበረችው አክሱም መጥተው ይማሩ ነበር፡፡ በስድስተኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢም አፄ ካሌብ ዘጠኝ ያህል ጀልባዎችን ከህንድ ገዝተው ቀይ ባህርን ተሻግረው ደቡብ ዓረቢያን እንዳጠቁ ይጠቅሳል፡፡ ፍራንስ አልቫሬዝ የተባለው የፖርቱጋል ቄስም በደቡባዊ ትግራይ ማናደለይ በተባለች የገበያ ሥፍራ የሁሉም አገሮች ነጋዴዎች፣ በተለይም ጥቁር ህንዶች በብዛት ይገኙ እንደነበረ በኪንግሃምና ጂ ደብሊው ቢ ሐንቲንግተን የተባለ የታሪክ ምሁራን ዘ ፕሪስተር ጆን ኦቭ ዘ ኢንዲስ በተባለው ሥራቸው (እ.ኤ.አ. 1961) ምዕራፍ አንድ ገጽ 5 ላይ አሥፍረዋል፡፡
ባንያውያን ከአዱሊስ እስከ ዘይላና በርበራ ተንሰራፍተው ይነግዱ የነበሩ ሲሆን፣ በምሥራቅ ኢትዮጵያም ሐረር ድረስ በመግባት ልዩ ልዩ ሸቀጦችን ያመጡ እንደነበር ሮበቺ ብሪቸሪ የተባለው ኢጣሊያዊ ተጓዥ «ኔል ሐሪር» በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. በ1896 ‹‹ሚላን›› ባሳተመው መጽሐፉ ይጠቅሳል፡፡ ፒ ፖሊቲስኪ የተባለው ጀርመናዊ የታሪክ ተመራማሪም «ሐረር» በሚል ርዕስ በ1888 ዓ.ም. ‹‹ላየፕዚግ›› ባሳተመው መጽሐፉ «ህንዳውያን በሐረር ከፍተኛ ንግድ ያንቀሳቅሱና ሸቀጣቸውን ሸጠው ከኦጋዴንና ከሸዋ በርካታ የዝሆን ጥርስ በመግዛት በንግድ መርከቦቻቸው ወደ ሌላ ገበያ ይወስዱ ነበር፤» ብሏል፡፡
ብዙ የታሪክ ምሁራን እንደ መረጃ የሚጠቅሱት ኮስማስ ኢንዲኮፕሌይትስ የተባለው ግብፃዊ መነኩሴ እ.ኤ.አ. በ525 አዶሊስን ከጎበኘ በኋላ ኢትዮጵያና ኑቢያ ከህንድ፣ ከሲሎንና ከሌሎች አገሮች ጋር ይነግዱ እንደነበረ በያዘው ማስታወሻ ላይ አሥፍሯል፡፡ ኮስማስ በዚያን ጊዜ የነበሩት አክሱማውያን በግዛታቸው አድርገው ያልፉ የነበሩት መርከቦች በሙሉ ግብር እንዲከፍሉ ያስገድዱ እንደነበረና ከፍተኛ የንግድ ልውውጥ ይካሄድ እንደነበረ ይገልጻል (ለተጨማሪ መረጃ ሪቻርድ ፓንክረስት፣ ዘ ኢትዮጵያን ቦርደርላንድስ፣ 1997 ገጽ 24 – 25 ይመልከቱ)፡፡
ብዙዎቻችን የኢትዮጵያ የመርከብ ንግድ ከጥንት ጀምሮ በቀይ ባህር ብቻ የተወሰን ይመስለናል፡፡ ነገር ግን የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች በህንድ ውቅያኖስ በኩል እስከ ዛንዚባር በመርከብ ይነግዱ ነበር፡፡ ሪቻርድ ፓንክረስት የተለያዩ የታሪክ ጸሐፊዎችን እየጠቀሱ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ጆርናል ቅጽ 3 ቁጥር ሁለት እ.ኤ.አ. 1965 ከገጽ 37-74 እንደሚያስገነዝቡን የደቡብ ኢትዮጵያ ጫፍ ሕዝቦች በኪስማዮ፣ በበርበራ፣ በሞቃዲሹ፣ በበናዲር፣ በመርካ፣ በበርቫ፣ ወዘተ በኩል ከብት፣ ቡና፣ የዝሆን ጥርስ፣ ቆዳ፣ በቅሎ፣ ፈረስ፣ አህያ፣ ከርብ፣ ሙጫ፣ የጎሽ ቀንድ ለገበያ እያቀረቡ በምትኩ ጨርቃ ጨርቅ፣ ብረት፣ ቴምር፣ ስኳር፣ ጌጣጌጥ፣ ዛጎል፣ ወዘተ. በ1880ዎቹ ውስጥ ያስገቡ ነበር፡፡ ሪቻርድ ፓንክረስትና ሮቤቺ-ብሪቸቲን በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ጆርናል ቅጽ 2 ቁጥር ሁለት እ.ኤ.አ. 1965 ከገጽ 74-88 ጠቅሰው እንደሚያስረዱን በሐረር በኩል በትንሹ አንድ ሚሊዮን ኪሎ የዝሆን ጥርስ፣ 2,000 ሺሕ ቆዳ፣ ገበያው ከፍ ሲል ደግሞ ከ15 ሚሊዮን እስከ 22.5 ሚሊዮን ኪሎ ቡና ለገበያ ይቀርብ ነበር፡፡ በአጭሩ ቀደም ሲል ለአብነት ያህል ብቻ የተጠቀሱት የታሪክ ማስረጃዎች ይፋ እንደሚያደርጉልን፣ ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ተጠቃሚ የነበረችና አሁንም የሆነች አገር መሆኗን ነው፡፡
(ክፍል ሁለት ይቀጥላል)
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው bktesheat@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡