አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጨዋታዎች ለሚጠብቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) አዲስ አሠልጣኝ እንደሚቀጥር ታወቀ፡፡
ከሁለት ዓመታት በላይ ከዋሊያዎቹ ጋር ከቆዩት አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር በስምምነት የተለያየው ፌዴሬሽኑ፣ ብሔራዊ ቡድኑን እንዲመሩ ጊዜያዊ አሠልጣኝ መመደቡ ይታወሳል፡፡
ሆኖም ፌዴሬሽኑ ዋሊያዎቹን የሚረከብ አሠልጣኝ ሲያፈላልግ ከቆየ በኋላ፣ የኢትዮጵያ መድን እግር ኳስ ክለብ አሠልጣኝ የሆነውን ገብረ መድኅን ኃይሌ ለመቅጠር ከጫፍ መድረሱ ተሰምቷል፡፡
ዋሊያዎቹ በቀጣይ ወር ለሚጀምረው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ለማዘጋጀት ፌዴሬሽኑ ከአሠልጣኝ ገብረ መድኅን ጋር መነጋገሩን መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ዓምና ወደ ፕሪሚየር ሊግ ካደገው መድን ጋር ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘውን አሠልጣኝ ገብረ መድኅን ምርጫው ማድረጉ ተወስቷል፡፡
በዚህም መሠረት አሠልጣኙ ሥራውን እንዲጀምር፣ ፌዴሬሽኑ ከክለቡ ጋር እየተወያየ እንደሚገኝ የተጠቀሰ ቢሆንም፣ አሠልጣኙ ክለቡን የመልቀቅ ፍላጎት እንደሌለው ተጠቁሟል፡፡ ስምምነቱ ካልሰመረ ፌዴሬሽኑ ‹‹ማንን ይመርጣል?›› የሚለው የሁሉም ሰው ጥያቄ ነው፡፡