የኢትዮጵያ ኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ታምሩ ገምበታን ጨምሮ ቁጥራቸው ለጊዜው ያልታወቁ ሰዎች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው መታሰራቸው ተሰማ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሰሞኑን መሆኑንና አቶ ታምሩ ገምበታ ግን ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. መሆኑ ታውቋል፡፡
የምክትል ዳይሬክተሩ ቤት በፍርድ ቤት የብርበራ ፈቃድ መበርበሩንና ዛሬ ጥቅምት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ሊቀርቡ እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡
የመንግሥት አስተዳደር ለውጥ ከተደረገ ጀምሮ የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ አገልግሎት ተቋም ውስጥ የተለያዩ ለውጦች (ሪፎርም) የተደረገ ቢሆንም፣ አንዳንድ የተቋሙ ሠራተኞች በድለላ ሥራ የተሰማሩ አካላት ጋር በመመሳጠር የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው በቁጥጥር ሥር ውለው በምርመራ ላይ እንዳሉም ይታወቃል፡፡
አገልግሎቱን በዋና ዳይሬክተርነት ይመሩ የነበሩት አቶ ብሩህተስፋ ሙሉጌታ፣ ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ፍራኦል ጣፋና አቶ ታምሩ ገምበታን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሦስት ወራት በፊት ሐምሌ መጀመሪያ ሳምንት አካባቢ ከኃላፊነት ማንሳታቸው ይታወሳል፡፡
ተቋሙ ከፓስፖርትና መሰል አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ ቅሬታ ሲቀርብበት መቆየቱንና ከዜጎች ከፍተኛ ገንዘብ በመቀበል በሕወጥ መንገድ ወደ ውጭ አገር ሲልኩ ነበር የተባሉ 16 የተቋሙ ሠራተኞች፣ እንዲሁም አምስት በአሠሪና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ስም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውም ይታወሳል፡፡
በተያዘው ሳምንት በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የተሰማው ምክትል ዳይሬክተሩን ጨምሮ ሌሎች ሰዎችም ከሙስና ጋር በተያያዘ መጠርጠራቸው ተገልጿል፡፡