Sunday, December 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ የዕዳ ሽግሽግ ጥያቄ ምላሽ እስኪያገኝ ክፍያ እንድታቆም ለመወሰን አበዳሪዎች እየተወያዩ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ያለባት ከፍተኛ የውጭ ዕዳ እንዲራዘምና እንዲሸጋሸግ ያቀረበችው ጥያቄ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ የመክፈያ ጊዜያቸው የደረሱ ዕዳዎችን መክፈል እንድታቆም ለመወሰን፣ ለኢትዮጵያ ያበደሩ አገሮች ውይይት እያደረጉ መሆናቸው ተሰማ።

መረጃውን ይፋ ያደረገው ዓለም አቀፍ የሉዓላዊ አገሮች ዕዳ መማክርት (Global Sovereign Debt Roundtable) ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባወጣው የእስካሁን የሥራ አፈጻጻም ሪፖርቱ ነው።

ዓለም አቀፍ የሉዓላዊ አገሮች ዕዳ መማክርት እ.ኤ.አ. በፌብርዋሪ 2023 የተቋቋመ ሲሆን፣ የተቋቋመበት ዓላማም በዕዳ ጫና ውስጥ የሚገኙ አገሮች የሚያቀርቧቸው የዕዳ ሽግሽግ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ ለማቀላጠፍ ነው።

መማክርቱን በጋራ የሚመሩት፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ዋና ዳይሬክተር፣ የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንትና የቡድን 20 አገሮች የወቅቱ ፕሬዚዳንት የሆነችው የህንድ የገንዘብ ሚኒስትር ሲሆኑ፣ በአባልነት ደግሞ የፓሪስ ክለብ አባልና የፓሪስ ክለብ አባል ያልሆኑ አበዳሪ አገሮች፣ የግል ዘርፍ አበዳሪዎችና ተበዳሪ አገሮች ይሳተፉበታል።

መማክርቱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ያከናወናቸውን ተግባራት ይፋ ባደረገበት ያለፈው ሳምንት መጨረሻ መግለጫው፣ የኢትዮጵያን የዕዳ ማሻሻያ ጥያቄ ለመመልከት የተቋቋመው የአበዳሪ አገሮች ኮሚቴ (ፈረንሣይና ቻይና በጋራ የሚመሩት) ከኢትዮጵያ መሪዎች ጋር በጉዳዩ ላይ በመነጋገር ሥራውን እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በዓለም የገንዘብ ድርጅት የሚደገፍ የኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም ያረቀቀ ሲሆን፣ በዚህ የኢኮኖሚ ፕሮግራም መለኪያና መሥፈርቶች ላይ በኢትዮጵያ ባለሥልጣናትና በገንዘብ ተቋሙ (IMF) ባለሙያዎች መካከል ስምምነት እንደተደረሰ የአበዳሪዎች ኮሚቴው የኢትዮጵያን የዕዳ ሽግሽግ ጥያቄ ወደፊት ለማስኬድ ዝግጁነት እንዳለው ሪፖርቱ አመልክቷል።

መግለጫው አክሎም የኢትዮጵያ አበዳሪዎች ኮሚቴ፣ ኢትዮጵያ ያቀረበችው የዕዳ ሽግሽግ ጥያቄ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ የመክፈያ ጊዜያቸው የደረሱ ዕዳዎችን ክፍያ እንዳትፈጽም ለመወሰን ውይይት እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቋል። 

‹‹ኢትዮጵያ በቅርቡ ከቻይና ጋር የመክፈያ ጊዜያቸው የደረሰ ዕዳዎችን ክፍያ እንዳትፈጽም የሚያስችላት ስምምነት አድርጋለች፤›› ያለው የመማክርቱ መግለጫ፣ ‹‹ሌሎች አበዳሪ አገሮችም (የግል ዘርፍ አበዳሪዎችን ሳይጨምር) የኢትዮጵያ የዕዳ ሽግሽግ ጥያቄዋ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ የደረሱ የዕዳ ክፍያዎችን እንዳትፈጽም ማድረግ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ በአበዳሪዎች ኮሚቴ ውስጥ ውይይት እያካሄዱ ይገኛሉ፤›› ሲል አስታውቋል።

የኢትዮጵያና የቻይና ባለሥልጣናት ከጥቂት ወራት በፊት ባደረጉት ስምምነት፣ ኢትዮጵያ የመክፈያ ጊዜያቸው የደረሰ ዕዳዎችን ለአንድ ዓመት እንዳትከፍል መፈቀዱ ይታወሳል። በዚህም ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት ለቻይና መክፈል ይጠበቅባት የነበረ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ገደማ ዕዳ ክፍያ ከእነ ወለዱ የመክፈያ ጊዜው ለአንድ ዓመት እንደተራዘመላት መረጃዎች ያመለክታሉ። በመሆኑም ኢትዮጵያ ከሌሎች አበዳሪዎች ተመሳሳይ የዕዳ ክፍያ ማቆያ ዕድል ካገኘች በትንሹ ቢዚህ ዓመት በጀቷ ውስጥ ለዕዳ ክፍያ የያዘችውን 159 ቢሊዮን ብር ለልማት ፕሮግራም ማዋል፣ አልያም ከውጭ የግል ዘርፍ አበዳሪዎች ተበድራ ያልከፈለችውን ዕዳ ለማቅለል ዕድል ይሰጣታል። ይሁን እንጂ አበዳሪ አገሮች የዕዳ ክፍያ ማቆያ ዕድሉን ያለ ቅድመ ሁኔታ መስጠት መቻላቸው ካለመረጋገጡም ባሻገር፣ የሚሰጡትን ዕድል በቅድመ ሁኔታውች ሊያጥሩት እንደሚችሉ በዚሁ የመማክርቱ መግለጫ ላይ አመላካቾች ተቀምጠዋል።

መግለጫው እንደሚያትተው የአበዳሪ አገሮቹ ኮሚቴ ለኢትዮጵያ የዕዳ ክፍያ ማቆያ ዕድል ለመስጠት ከጀመረው ውይይት በተጨማሪ፣ የዕዳ ጫና ያለባቸው ሌሎች ተበዳሪ አገሮችንም ጭምር የሚያስተናግድ ወጥ የሆነ ሥርዓት ለማበጀት እየመከረ ነው።

ውይይቱ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የቡድን 20 አገሮች በሰጡት የዕዳ ማቅለያ የጋራ ማዕቀፍ ዕድል (Common Framework) ለመስተናገድ የጠየቁ አገሮች የዕዳ ሽግሽግ ጥያቄያቸው ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ፣ የደረሱ ዕዳ ክፍያዎችን መክፈል እንዲያቆሙ የሚቻልበትን አጠቃላይ ሥርዓት ለማበጀት ያለመ ነው።

ይሁን እንጂ በዚህ ውይይት ላይ አበዳሪ አገሮች ልዩነት የሚንፀባረቅባቸው የተለያዩ ሐሳቦችን ማንሳታቸውን መግለጫው ይጠቁሟል። አንዳንዶቹ አበዳሪ አገሮች የዕዳ ሽግሽግ የጠየቁ አገሮች ከአይኤምኤፍ የባለሙያዎች ቡድን ጋር የኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም ስምምነት ከደረሱበት ጊዜ ጀምሮ፣ በሁለትዮሽ የብድር ስምምነት በተገኘ ብድር ላይ የሚፈጽሙት የዕዳ ክፍያ በቀጥታ እንዲቆም ይደረግ የሚል ሐሳብ ማራመዳቸውን አስታውቋል። ይህንን ማድረግም ከፍተኛ የዕዳ ክፍያ ሸክም ለተጫናቸው ተበዳሪ አገሮች የገንዘብ ዕፎይታ እንዲያገኙ የሚረዳ ሲሆን፣ አበዳሪዎችም የዕዳ ሽግሽግ ሒደቱን እንዲያፋጥኑ ያበረታታል የሚል አመክንዮ ሐሳቡን ባቀረቡት አበዳሪ አጋራት በኩል መራመዱን አስረድቷል።

ሌሎች አበዳሪዎች ደግሞ የዕዳ ሽግሽግ የጠየቁ አገሮች ድርድሩ እስኪጠናቀቅ ድረስ የዕዳ ክፍያ ለማቋረጥ ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ አበዳሪ አገሮችና የአበዳሪ አገሮች ኮሚቴ ተመካክረውና ጥያቄ ያቀረበው አገር፣ በአይኤምኤፍ ፕሮግራም ለመታቀፍ የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረሱን አረጋግጠው የዕዳ ክፍያ ማቋረጥን (የዕዳ ከፍያውን ማዘግየት) ቢፈቅዱ ይሻላል የሚል አማራጭ ሐሳብ እንዳቀረቡ መግለጫው አመልክቷል። እነዚህ አገሮች ባቀረቡት አማራጭ ሐሳብ መሠረት የዕዳ ሽግሽግ ጥያቄ ያቀረበ አገር ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ ዕዳ ክፍያ ማቆም የሚችለው ክፍያ ለማቆም እንዲፈቀድለት ሲጠይቅና ጥያቄው በአበዳሪ አገሮች ተቀባይነት ሲያገኝ ነው። በተጨማሪም ከአይኤምኤፍ የባለሙያዎች ቡድን ጋር የኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም ስምምነት ማድረግን በቅድመ ሁኔታነት ያስቀምጣል። የተቀሩት አበዳሪ አገሮች ደግሞ የዕዳ ሽግሽግ ለጠየቁ አገሮች በጊዜ የተገደበ የዕዳ ክፍያ ማቆያ ቢፈቀድ የተሻለ ነው የሚል አቋም ማራመዳቸውን መግለጫው ያስረዳል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በአይኤምኤፍ ፕሮግራም ውስጥ ለመካተት የሚያስችል የኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም ቀርፆ ከገንዘብ ድርጅቱ ባለሙያዎች ጋር ውይይት ማድረግ ከጀመረ በርካታ ወራት የተቆጠሩ ቢሆንም፣ ሁለቱ ወገኖች በተወሰኑ ነጥቦች ላይ ለመግባባት እንዳልቻሉ ምንጮች ጠቁመዋል። 

አይኤምኤፍ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም ለመደገፍ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የአገሪቱን ብር የመግዛት አቅምን በከፍተኛ መጠን ማዳካም አለበት የሚል ምክረ ሐሳብና አቋም መያዙ መሠረታዊው የልዩነት ነጥብ እንደሆነ ምንጮች ተናገረዋል።

በመሆኑም አበዳሪ አገሮቹ ለኢትዮጵያ ለመስጠት ያሰቡትን የዕዳ ክፍያ ማቆያ፣ እንዲሁም አጠቃላይ የዕዳ ሽግሽግ ሒደቱን ‹‹ከአይኤምኤፍ ጋር በሚደረስ ስምምነት›› በሚል ቅድመ ሁኔታ ካሰሩት የኢትዮጵያን እጅ እንደ መጠምዘዝ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል። ምክንያታቸውን ሲያስረዱም፣ ኢትዮጵያ በዕድሉ ለመጠቀም የብር የመግዛት አቅምን በከፍተኛ ደረጃ እንድታዳክም የሚያስገድድ ሁኔታ ውስጥ ትወድቃለች፣ ይህ ደግሞ አሁን ባለው የዋጋ ንረት ላይ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብን ፈተና ውስጥ ይከታል፣ እንዲሁም የውጭ ዕዳ መጠኑን በዕጥፍ እንዲጨምር ያደርገዋል ብለዋል።

አይኤምኤፍ ባለፈው ሳምንት ባወጣው የዓለም የኢኮኖሚ ሁኔታ ሪፖርት ላይ በከፍተኛ የዋጋ ንረት ውስጥ የሚገኙ አገሮች የውጭ ምንዛሪ ሥርዓታቸውን በማስተካከል የመገበያያ ገንዘባቸውን አቅም ማዳከም ዘላቂ መፍትሔ የሚሰጣቸው ቢሆንም እንደ ኢትዮጵያ፣ ብሩንዲ፣ ዚምባብዌና ማላዊ ያሉ አገሮች ገንዘባቸውን በማዳከም የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ሙሉ በሙሉ እንዲስተካከል ከመፍቀድ መቆጠባቸውን አመልክቷል።

እነዚህ አገሮች የገጠማቸውን የውጭ ምንዛሪ ተመን ግፊት በማጤን የመገበያያ ገንዘባቸውን ማዳከም የሚጠበቅባቸው ቢሆንም፣ በኢኮኖሚያቸው ውስጥ የዋጋ ንረትን እንደሚያመጣ፣ የኑሮ ውድነትን እንደሚጨምርና ማኅበረሰባዊ አለመረጋጋትን እንደሚፈጥር በመሥጋት መቆጠባቸውን ገልጿል። የአገራቱ ሥጋት ተገቢነት ያለው ቢሆንም ምርጫቸው ግን የተፈጠረባቸውን ሥጋት የሚቀርፍ እንዳልሆነ ገልጿል። ለአብነትም ኢትዮጵያን ጨምሮ በአንዳንድ አገሮች ላይ በኦፊሴላዊው የውጭ ምንዛሪ ገበያና በትይዩ (ጥቁር) ገበያው መካከል መዛባትንና በመጠባበቂያ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ላይ መሳሳትን ማስከተል መጀመሩን አስገንዝቧል።

የውጭ ምንዛሪ ተመን ማስተካከያ ግፊት መከሰት፣ አገሮች ኢኮኖሚያቸውን ከውጭ ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ጋር ማጣጣም እንዳለባቸው የሚጠቁም አስፈላጊ ምልክት በመሆኑ ግፊቱን መቃወም እንደሌለባቸውም አይኤምኤፍ በሪፖርቱ አሳስቧል። ይህ ሁኔታ ሲከሰት አገሮች የውጭ ምንዛሪ ተመናቸውን በማስተካከል የመገበያያ ገንዘባቸውን ከማዳከም ይልቅ ሁኔታውን በመቃወም ባለበት እንዲቀጥል የሚያደርጉ ከሆነ፣ ኢኮኖሚያቸውን ከውጭ ኢኮኖሚዊ ቀውሶች ጋር ለማጣጣም እንደሚቸገሩ፣ ከዚህም ባለፈ ወደፊት የውጭ ምንዛሪ ተመናቸውን ለማስተካከል የሚገጥማቸው ሸክም ሊጨምር እንደሚችል አመላክቷል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች