Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዝግጅት ተጠናቆ በቀጣይ ወራት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊላክ መሆኑ...

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዝግጅት ተጠናቆ በቀጣይ ወራት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊላክ መሆኑ ተሰማ

ቀን:

በኢትዮጵያ ያለፉ በደሎችና የመብት ጥሰቶች በሽግግር ፍትሕ ሒደት መፍትሔ እንዲያገኙ ለማድረግ የተጀመረው የፖሊሲ ዝግጅትና በአማራጮች ላይ ሲደረግ የቆየው የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ተጠናቆ፣ በመጪዎቹ ጥቂት ወራት ውስጥ ተጠናቆ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚላክ ተሰማ፡፡

ኅዳር ወር 2014 ዓ.ም. ይፋ የተደረገውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የጋራ የምርመራ ውጤት ምክረ ሐሳብ፣ እንዲሁም በጥቅምት 2015 ዓ.ም. በተደረሰው የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ላይ በመመሥረት ሥራውን ሲያከናውን መቆየቱን የፍትሕ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የባለሞያዎች ቡድን አስተባባሪ ታደሰ ካሳ  (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በፖሊሲ ዝግጅት አማራጮች ላይ ሲከናወን የነበረው ሒደት ትልቅ ርቀት የተሄደበትና በበርካቶች ዘንድ ተስፋ የታየበት ነው ብለዋል፡፡

በቀጣይ ባሉት ሦስት ወራት በረቂቅ ፖሊሲው የመጨረሻ ሰነድ ላይ በተመረጡ አማካይ ከተሞች ላይ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ለሚንስትሮች ምክር ቤት ተልኮ የባለሙያው ቡድንም ተልዕኮ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች በውይይት ሒደት ወቅት በብዙዎቹ ዘንድ ጥሩ የሚባል የድጋፍ ድምፅ መሰማቱን የገለጹት ታደሰ (ዶ/ር)፣ ነገር ግን ቁጥራቸው ትንሽ ሊባሉ የሚችሉ ሰዎች ደግሞ ሥጋት እንዳላቸው ሲያስተጋቡ እንደነበር አውስተዋል፡፡

የብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ሰኞ ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ የሽግግር ፍትሕ አገራዊ ፖሊሲን በማጠናቀቅ ሒደት በቀጣይ ምዕራፍ የሚከናወነው ዋና ሥራ፣ የሪፖርትና የፖሊሲ ረቂቅ ዝግጅት መሆኑን ገልጿል፡፡

ከዚህ በፊት የተከናወኑ አጠቃላይ የምክክር ሥራዎችን ሒደት በመዳሰስ፣ የተሰበሰቡ ግብዓቶችን ዓለም አቀፋዊ ደረጃን በጠበቀ መንገድ በማጠናቀር በቀጣይ ጊዜያት ትንታኔ ይደረግበታል ብሏል፡፡

ረቂቅ ፖሊሲው በውይይት የተገኙ ግብዓቶችን፣ ድምዳሜዎችንና የሽግግር ፍትሕ ዋና ዋና አላባዎችን ማለትም የክስ፣ እውነትን የማፈላለግ፣ የዕርቅ፣ የምሕረት፣ የማካካሻ፣ የተቋማዊ ማሻሻያ፣ የሽግግር ፍትሕ የጊዜ ወሰን፣ የባህላዊ አደረጃጀቶችና የክልሎች ሚና ምንነት በመዘርዘር፣ እንዲሁም የቀረቡ ምክረ ሐሳቦችን በማካተት እንደሚደራጁ ተገልጿል፡፡

በቀጣይ ረቂቅ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ሰነድ ለሕዝብ በይፋ ቀርቦ በኅዳር 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በሚደረጉ ተጨማሪ የድኅረ ፖሊሲ ውይይቶች ዳብሮ የመጨረሻ ገጽታውን ይይዛል ተብሏል፡፡

የሽግግር ፍትሕ ባለሙያ ቡድን በክልሎች ከሚገኙ 36 ዩኒቨርሲቲዎች በተውጣጡ 216 የሕግ ትምህርት ቤት ባለሙያዎች ታግዞ፣ በእስካሁኑ ሒደት 47 ክልላዊና ስምንት አገር አቀፍ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮችን ማዘጋጀቱን የብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም ዘጠኝ በልዩ ሁኔታ በተለዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ ያተኮሩ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮችን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተለያዩ ቢሮዎች፣ ከአፍሪካ ኅብረት፣ ከኢጋድና ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በቅንጅት ማካሄዱን ሚኒስቴሩ  አክሏል፡፡

የባለሙያዎች ቡድኑ በ12 ክልሎችና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የማወያየትና ግብዓት የመሰብሰብ ሥራዎችን አካሂዶ፣ የመጀመርያው ‹‹ወሳኝ›› የግብዓት ማሰባሰብ ምዕራፍ እያገባደደ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በመድረኮቹ ከከተሞችና ከአጎራባች አካባቢዎች የመጡ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሰለባዎች በግብዓት ማሰባሰብ መድረኮቹ ቀዳሚ ትኩረት እንደተሰጣቸው ያስታወቀው የፍትሕ ሚኒስቴር መግለጫ፣ በእያንዳንዱ መድረክ ከተጋበዙ ተሳታፊዎች እስከ 60 በመቶ የሚደርሱ ሰዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጎጂዎች ናቸው ብሏል፡፡ ተጎጂዎቹ በልዩ ሁኔታ በሁሉም መድረኮች በቀረቡ አማራጮች ላይ አቋማቸውን በነፃነት እንዲያንፀባርቁና የራሳቸውን አማራጮች እንዲያቀርብ፣ አስቻይ ዕድሎች እንዲፈጠሩ ስለመደረጉም ገልጿል፡፡

የምክክር ሒደት ፆታዊ ዕይታን ታሳቢ ያደረገና ለፆታዊ ጉዳዮች ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ለማረጋገጥ በእያንዳንዱ መድረክ ላይ ከተሳተፉ ሰዎች 40 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች እንደነበሩ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

ለግብዓት ማሳሰቢያነት የዋለው የፖሊሲ አማራጮችን በሰነድና የውይይት መድረኮቹ በሚመሩባቸው ደጋፊ ሰነዶች በኦሮሚኛ፣ በትግርኛና በሶማሊኛ ቋንቋዎች ቀደም ብለው መተርጎማቸው ሒደቱ ውጤታማ እንዲሆን ስለማድረጉም ተገልጿል፡፡

በምክክር ሒደቱ ላይ አሉታዊ አመለካከት ያንፀባረቁ ጥቂት ተሳታፊዎች፣ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የቀጠለው ግጭትና የፀጥታ ሁኔታ ለሽሽግር ፍትሕ ሒደቱ አስቻይ ዓውድ እንዳይፈጠር እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ሥጋታቸውን መግለጻቸው በመግለጫው ተካቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...