በ2015 በጀት ዓመት የታቀደው የ16.5 ሚሊዮን የፓልምና 32 ሚሊዮን ሊትር የሱፍ ዘይት ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት አስታወቀ፡፡
በ2015 በጀት ዓመት ጎልድ አፍሪካ ከተሰኘ የዘይት አምራች የገዛውን 4.8 ሚሊዮን ሊትር ወደ አገር ውስጥ ገብቶ ማከፋፈሉን፣ ቀሪውን 11.7 ሚሊዮን ሊትር ዘይት በባቡርና በተሽከርካሪ እያጓጓዘ መሆኑን ድርጅቱ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት የኢንዱስትሪና ውጤቶች ግዥ ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ወርቁ፣ በ2015 በጀት ዓመት ለመግዛት ታቅዶ የነበረው 16.5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ወደ አገር ውስጥ መጓጓዝ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ 32 ሚሊዮን ሊትር የሱፍ ዘይት ግዥ ለመፈጸም ኢትዮ ብላክ ከተሰኘ ድርጅት ጋር ውል ተገብቶ በሒደት ላይ የሚገኝ መሆኑን ያስረዱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የውጭ ምንዛሪ ብድር ለማስፈቀድ በሒደት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የሱፍ ዘይት ግዥ ለመፈጸም 43 ሚሊዮን ዶላር ብድር እንደሚያስፈልግ፣ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚከፈል መሆኑንና 16.5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት በ23 ሚሊዮን ዶላር እንደተገዛ አስረድተዋል፡፡
ድርጅቱ ወደ አገር ውስጥ የገባውን ፓልም ዘይት በተለያዩ የክልል ከተሞች በሚገኙ 83 ቅርንጫፎች በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ እንደሚያሠራጭ ዋና ዳይሬክተሩ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በ2016 በጀት ዓመት ደግሞ ለአገር ውስጥ አምራች ድርጅቶች 100 ሺሕ ኩንታል ስኳርና 10 ሚሊዮን ሊትር ፓልም ዘይት ለማቅረብ ውል መገባቱን፣ ነገር ግን አቅራቢ ድርጅቱ የተለያዩ እክሎች ስለገጠመው ችግሩ እስኪፈታ እየተጠባበቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለአገር ውስጥ አምራች ድርጅቶች የሚቀርበው ዘይትና ስኳር ለመግዛት 1.7 ቢሊዮን ብር እንደሚጠይቅና ድርጅቱ ተከታትሎ ምርቱን ለሚፈለገው ዓላማ እንደሚያቀርብ አስረድተዋል፡፡
የአገር ውስጥ ዘይት አቅርቦትን በተመለከተ ከፌቤላ ዘይት አምራች ኩባንያ ለመግዛት ውል መግባቱን የገለጹት አቶ ፈጠነ፣ ይሁን እንጂ ፋብሪካው የሚገኝበት የአማራ ክልል ባለው የፀጥታ ችግር ሳቢያ መረከብ አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
ድርጅታቸው በምዕራብ፣ በሰሜን፣ በማዕከላዊ ደቡብና በምሥራቅ ዲስትሪክቶች አማካይነት ግዥ እንደሚፈጽም ገልጸው፣ በፀጥታ ምክንያት ከሰሜን ዲስትሪክት ውጪ የምግብ ፍጆታዎችንና ሸቀጦችን መግዛት ለኅብረተሰቡ እየተሠራጨ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ድርጅቱ የሚያቀርባቸው የዘይትም ሆነ ሌሎች ምርቶች ከመደበኛ ገበያው ጋር ሲነፃፀር ዋጋው ዝቅተኛና ተመጣጣኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሥርጭት ሁኔታው የሱፍ ዘይት በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በሚደለደለው መሠረት እንደሚሠራጭ፣ ሌሎች ምርቶች ግን በድርጅቱ ቅርንጫፎች አማካይነት ለኅብረተሰቡ እንደሚቀርቡ ተናግረዋል፡፡