በአፍሪካ ቀዳሚ የአውቶሞቲቭ ማዕከል ለመሆን አቅዶ የተነሳው ካኪ ሞተርስ ኩባንያ፣ በ450 ሚሊዮን ብር በዓለም ገና ያስገነባውን የአይሱዙ ተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካ ጥቅምት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. አስመርቆ ሥራ አስጀመረ፡፡
ፋብሪካው በአይሱዙ ሞተርስ ኩባንያ ሙሉ የቴክኒክ ድጋፍና ክትትል መገንባቱን፣ ለኢትዮጵያ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንደሚያስመዘግብ፣ የካኪ ሞተርስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ገብረ ሚካኤል ግርማይ በሥራ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡
ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ በዓመት 2,500 የጭነት ተሽከርካሪዎችን ማምረት ይችላል ያሉት አቶ ገብረ ሚካኤል፣ ከ780 በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም የሥራ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡
ይህም የሥራ አጥ ቁጥርን ከመቀነስ አኳያ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለመደገፍ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡
በ20 ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ፋብሪካው ለሽያጭና ለድኅረ ሽያጭ ማዕከሉ አጠቃላይ 450 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት መሆኑን፣ በቀጣይ ለማስፋፋት አምስት ሚሊዮን ዶላር ታሳቢ መደረጉን አቶ ገብረ ሚካኤል አክለው ገልጸዋል፡፡
ዘመናዊ የጥገና ማዕከል አብሮ በመገንባትና የተሟላ የመለዋወጫ አቅርቦት እንዲኖረው በማድረግ ተሽከርካሪዎቹ ያለ ምንም የቴክኒክ ችግር አገልግሎት እንዲሰጡ የአቅርቦት ሰንሰለቱ ላይ ከፍተኛ እሴት እንዲጨምር ማድረግ መቻሉን ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ አክለዋል፡፡
‹‹ድርጅታችን ለሰው ሀብት ልማት ቅድሚያ ትኩረት ይሰጣል፤›› ያሉት አቶ ገብረ ሚካኤል፣ ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት ጋር በመነጋገር የላቀ የትምህርት ውጤት ያላቸውን ተመራቂ ተማሪዎች በመቅጠር በንድፈ ሐሳብ የተማሩትን በተግባር ልምምድ እንዲያዳብሩ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ባለሙያዎችን ከዘመናዊ አሠራርና ከቴክኖሎጂ ጋር እንዲተዋወቁ ለማድረግ የሥልጠና ማዕከል በማቋቋም፣ ተከታታይ ሥልጠና እየተሰጠ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ካኪ ሞተርስ በአሁኑ ወቅት አራት የተሽከርካሪና አምስት የመለዋወጫ፣ እንዲሁም የጥገና አገልግሎት ማዕከላትና አንድ ዋና የመለዋወጫና የማከማቻ ዴፖ እንዳለው ያሳወቁት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ በቀጣይ በሐዋሳ፣ በድሬዳዋ፣ በዱከም፣ በባህር ዳር፣ በጅማና በመቀሌ የሽያጭ የጥገና ማዕከላት እንደሚከፈቱ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ትልቅ ዕምቅ አቅም ያላት አገር ናት ያሉት ደግሞ፣ የአይሱዙ ሞተርስ ኢንተርናሽናል ፕሬዚዳንት ሚስተር መንሱር አህመድ ናቸው፡፡
‹‹ካኪ ሞተርስ በምሥራቅ አፍሪካ የአምራች ዘርፍ መናኸሪያ እንዲሆን ትልቅ ራዕይ አለኝ፤›› ያሉት ሚስተር አህመድ፣ በዚህም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ውስጥ ትልቅ ቦታ እንደምትይዝ ያላቸውን እምነት አስታውቀዋል፡፡
አይሱዙ ኩባንያ ካኪ ሞተርስን በማገዝ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ በተለይ በአፍሪካ ትልቅ ተወዳዳሪ ይሆናል ሲሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
‹‹ለአምራች ኢንዱስትሪ ያለን ቁርጠኝነት ከፍተኛ ነው፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ሌሎች ኢንቨስተሮችም ወደ ኢንቨስትመንት ገብተው በአገሪቱ ትልልቅ አምራች ድርጅቶች እንዲፈጥሩ በትጋት እንደሚሠሩ ተናግረው፣ የመንግሥት ድጋፍን እንደሚሹ ጠቅሰዋል፡፡
‹‹ከዚህ ባሻገር የብሔራዊ አውቶሞቲቭ ፖሊሲ ለኢንዱስትሪው ዕድገት ትልቅ ዕገዛ የሚያደርግ በመሆኑ፣ መንግሥት በዚህ ረገድ እንዲያግዘን እንፈልጋለን፤›› ብለዋል፡፡ ይህንን በማድረግ የአገር በቀል አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪው በተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲልና ተፎካካሪነቱን እንዲያሳድግ እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡
ካኪ ሞተርስ አሁን ማምረት ከሚችለው በዓመት 200 ወደ 2,500 ተሽከርካሪዎች በዓመት በማሳደግ፣ ከ1,500 በላይ ተጨማሪ የሥራ ዕድሎችን በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት መፍጠር እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ በተሰጠ ልዩ ትኩረት ካለው ውስን በጀት ከፍተኛውን ለመንገድ ዘርፉ በማዋል ላለፉት አራት ዓመታት በቅርቡ ግንባታቸው የሚጠናቀቁትን ጨምሮ 28 ሺሕ ኪሎ ሜትር መንገድ መሠራቱን የተናገሩት፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ከ1.1 ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ የቆዳ ስፋትና እስካሁን ባለው ሁኔታ 167 ሺሕ ኪሎ ሜትር የመንገድ ስፋት እንዳላት የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ከዚህ ውስጥም 28 ሺሕ ኪሎ ሜትር የሚሆነው መንገድ የተጠናቀቀው ባለፉት አራት ዓመታት ነው ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ በአገሪቱ በአጠቃላይ ያለው የተሽከርካሪዎች ብዛት ከ1.2 ሚሊዮን እንደማይበልጥ ገልጸው፣ ይኼም ከአጠቃላይ የሕዝብ ብዛት አኳያ ሲታይ የተሽከርካሪ ብዛት ከአንድ በመቶ እንደማይበልጥ ተናግረዋል፡፡
‹‹በተዘረጋው መንገድ ልክ የሚመጥን ተሽከርካሪዎች ሊኖሩን ይገባል፤›› ያሉት አቶ መላኩ፣ ከውጭ በሚገቡ ተሽከርካሪዎች ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥ በማምረትና በመገጣጠም በቂ የሆኑ ፋብሪካዎችን መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ከካኪ ሞተርስ መገጣጠሚያዎች በተጨማሪ ሌሎች የማምረቻና የመገጣጠሚያ ፋብሪካዎች መስፋፋት አለባቸው ብለው፣ ‹‹በአገሪቱ የሥራ አጥነት ችግር በዋናነት የሚነሳ ሲሆን፣ ችግሩን ለመፍታት ያሉትን ጥሬ ዕቃዎች ተጠቅመን በምርት ላይ እሴት በመጨመር ወደ ገበያ ማቅረብና ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ማምረት ስንችል ብቻ ነው፤›› ሲሉ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡