Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልተናጋሪዎቹ ቴምብሮች የኢትዮጵያ ፖስታ ቀን ‹የካቲት 30 ቀን› ለምን አይከበርም?

ተናጋሪዎቹ ቴምብሮች የኢትዮጵያ ፖስታ ቀን ‹የካቲት 30 ቀን› ለምን አይከበርም?

ቀን:

‹‹ቴምብሮች ለዓለም ሕዝብ በብዙ መንገድ ከፍ ያለ ጥቅም ይሰጣሉ፡፡ አንደኛ ለዓለም የታሪክ ጸሐፊዎች የጥናታቸው መነሻ ናቸው፡፡ ሁለተኛ ታዳጊ ሕፃናትና ነፍስ ያወቁ ሰዎች የአገርን ታሪክ በቴምብር አማካይነት እንዲያውቁና እንዲማሩ ያስችላሉ፡፡ ሦስተኛ የመታሰቢያ ቴምብሮች መገለጫዎችና ፎቶግራፎች በየአገሩ ሲሠራጩ ቱሪስቶችን ይስባሉ፡፡ ቴምብሮቹ የቱሪስቶች መሳቢያ መሆናቸው ስለታመነበትም ብዙዎቹ አገሮች የሚያሳትሟቸው ቴምብሮች የተፈጥሮ ውበታቸውን፣ ታሪካቸውን፣ ማኅበራዊ ኑሮአቸውንና ሌሎች የመማረክ ኃይል ያላቸውን ነገሮች የሚይዙ ናቸው፡፡››

ተናጋሪዎቹ ቴምብሮች የኢትዮጵያ ፖስታ ቀን ‹የካቲት 30 ቀን› ለምን አይከበርም? | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የጥንት ፖስታ አመላላሽ

ይህ በጽሑፍ ሠፍሮና ተሰንዶ የደረሰን ኃይለ ቃል ከ49 ዓመት ገደማ በፊት ያስተጋቡት፣ በዘመኑ አጠራር የፖስታ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ገብረ ጻድቅ ደገፉ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ ይህን ስለ ቴምብሮች ጠቀሜታ የማስገንዘቢያ ቃላቸውን ያሰሙትም፣ በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ ብሔራዊ የፖስታ ቴምብሮች ሙዚየም ተቋቁሞ በተመረቀበት ማክሰኞ ነሐሴ 13 ቀን 1967 ዓ.ም. (19 August 1975) ነበር፡፡

ብሔራዊ የፖስታ ቴምብሮች ሙዚየም ከ49 ዓመት በፊት ይመሥረት እንጂ የፖስታ አገልግሎት የተቋቋመው ግን በዳግማዊ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ አማካይነት ከ130 ዓመት በፊት የካቲት 30 ቀን 1886 ዓ.ም. መሆኑ ታሪካዊ ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም የፖስታ ኅብረት አባል የሆነችው በ1901 ዓ.ም. ሲሆን፣ አባል እንድትሆን ጥያቄውን ያቀረቡት ደግሞ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጥር 22 ቀን 1900 ዓ.ም. ደብዳቤ (ጦማር) በመጻፍ ነበር፡፡ በጦማራቸው ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፡፡

ተናጋሪዎቹ ቴምብሮች የኢትዮጵያ ፖስታ ቀን ‹የካቲት 30 ቀን› ለምን አይከበርም? | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
በተለያዩ ዘመኖች የታተሙ የፖስታ ቴምብሮች

‹‹የኢትዮጵያ፡ ቴሌግራፍና፡ ፖስታ፡ እንደ፡  ሮፓ፣ መንግሥት፡ ደንብ፡ ከኡኒዮን፡ ፖስታ እንዲገባ፡ አስታዉቃለሁ፡፡ ሌሎች፡ መንግሥቶች፡ እንደሚከፍሉት፡ ገንዘብ፡ እኛም፡ ባመት እንደ፡ ደንቡ፡ ለኡኒዮን፡ ፖስታል፡ እንሰጣለን፡፡ የፖስታና፡ ቴሌግራፍ፡ ሠራተኞች፡ ከዚህ ቀደም፡ ስድስት ሰዎች፡ እንድታስመጣልን፡ ጠይቀንኽ፡ ነበር፡፡ አሁንም፡ በቶሎ እንድታስመጣልን፡ ይሁን፡፡ ደሞዛቸውንም፡ እንደ ሥራቸው፡ መጠን፡ ከመቶ አንስቶ እስከ፡ መቶ፡ አምሳ፡ ድረስ፡ በተዋረድ፡ እንሰጣለን፡፡…››

የዓለም ፖስታ ኅብረት በስዊስ በርን ከተማ የተመሠረተበትን ኦክቶበር 9 ቀን 1874 (መስከረም 30 ቀን 1867 ዓ.ም.) መሠረት በማድረግ፣ በየዓመቱ የዓለም የፖስታ ቀን በአባል አገሮቹ ‹ኦክቶበር 9› እንዲከበር ያደርጋል፡፡

እንደ ኅብረቱ መግለጫ የክብረ ቀኑ ዓላማ፣ የፖስታ ዘርፉ በሰዎችና በቢዝነሶች ውስጥ ያለውን የዕለት ተዕለት ሕይወት ሚና፣ እንዲሁም ለአገሮች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያለውን አስተዋፅኦ ማስገንዘብ ነው፡፡ ዘንድሮ በዓሉ መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም. በተለያዩ አገሮች ‹‹በኅብረት ለመተማመን›› (Together for Trust) በሚል መሪ ቃል ተከብሯል፡፡

በኢትዮጵያም ይኸው ዓለም አቀፍ የፖስታ ቀን ‹‹ፖስታ ለፕላኔታችን›› በሚል መሪ ቃል እሑድ ጥቅምት 4 ቀን እንደሚከበር፣ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሃና አርዓያ ሥላሴ ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

 ተቋሙ ከጥቅምት መባቻ ጀምሮ ‹‹ፖስታ ትናንት፣ ዛሬና ነገ›› በሚልም የተለያዩ ዝግጅቶችን ቀደምት ቴምብሮችን ጭምር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ  በማስተዋወቅ ቀኑን እያሰበ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ፖስታ፣ የዓለም ፖስታ ቀን ምክንያት በማድረግ መስከረም 28 ቀን በማኅበራዊ ገጹ ላይ ባተመው መግለጫው፣ በዓሉ የኅብረቱ አባላት በሆኑ 192 አገሮች ‹‹Together for Trust- በኅብረት ለደኅንነት›› በሚል እንደሚከበር ነበር የገለጸው፡፡  

መግለጫው አያይዞም ለ129 ዓመታት በዘርፉ ማኅበረሰቡን በማገልገል የቆየው የኢትዮጵያ ፖስታ፣ ከ700 በላይ በሚሆኑት ቅርንጫፎቹ በመላ አገሪቱ ተደራሽ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን፣ ባለፉት ዓመታት በተገበረው ሪፎርም የአገልግሎት ጥራትን በማሻሻል ከፍተኛ ውጤትን ማስመዝገቡንም አመልክቷል፡፡ በፖስታ አገልግሎት፣ በኢኤምኤስ፣ በሎጂስቲክስ፣ በፋይናንስ፣ በፖስታ መደብር፣ በመንግሥት አገልግሎቶች እንዲሁም በፊላቴሊ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶችን የሚሰጠው ድርጅቱ፣ በቀጣይ ደንበኞችን በተሻለ ለማገልገል ‹‹ፖስታ በስፋትና በጥልቀት›› የሚል አዲስ የሦስት ዓመት ስትራቴጂ በ2016 ዓ.ም. መተግበር መጀመሩንም አስታውቋል፡፡

‹የምን ይልክ ፖስታ› 130ኛ ዓመት

‹‹ምን ይልክ፣ ምን ይልክ፣ ምን ይልክ እያሉ

በፖስታ ቤት ዙርያ ይጠያየቃሉ፡፡

ዛሬማ ምን አይልክ!

ሁሉን በየዓይነቱ ሰፍሮ በልክ በልክ

ብቅ ብሎ ባየው መሥራቹ ምን ይልክ፡፡››

በአንድ ወቅት በእታጉ በዛብህ የቀረበ ግጥም ነው፡፡

ይህ ግጥም ከ130 ዓመታት በፊት የተጀመረውን የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት የሚያዘክር ነው፡፡ አዲስ አበባ ከተማ በተመሠረተች በሰባተኛው ዓመት መልዕክት መላኪያ የሆነውን የፖስታ አገልግሎት መጀመሩ ይወሳል፡፡

ከፖስታ አገልግሎት ጋር የማይነጠለው ቴምብርም ታትሞ ለዕይታ የበቃው ኅዳር 14 ቀን 1887 ዓ.ም. (ኖቬምበር 24 ቀን 1894) እንደሆነ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የፖስታ ቴሌግራምና ቴሌፎን ሚኒስቴር ያሳተመው የቴምብር ካታሎግ ይገልጻል፡፡

በፈረንሳይ ከታተሙት ሰባት ቴምብሮች በአራቱ ዳግማዊ ምኒልክ ዘውድ ደፍተው ሲታዩበት ሦስቱ ደግሞ የይሁዳ አንበሳ ባለመስቀል ሰንደቅ ዓላማ በአማርኛ ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚል ከራስጌ፣ ከግርጌው የዘመኑ መገበያያ የነበረውን ‹‹ግርሽ›› ባለ 1፣2፣4፣8 እና 16 ይዟል፡፡

ከ1887 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 1961 በኢትዮጵያ የታተሙና ከባሕር ማዶ ተሻግረው የመጡ ቴምብሮች በካታሎጉ ውስጥ ተካትተዋል፡፡ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶችን የጥንትና የቅርብ ዘመናት ነገሥታት፣ መንፈሳዊ መሪዎችና ጠቢባን፣ የአየርና የመሬት መሠረተ ልማት፣ ስፖርትና ኦሊምፒክን የሚያሳዩ ቴምብሮችን፣ በአገልግሎት ላይ የዋሉ ቴምብሮችን ‹‹ካርታ ጶስታል›› (ፖስት ካርድ) የቴምብር ኦርጂናል ዲዛይኖችንም ያካተተ ነው፡፡

የኢትዮጵያን ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የአገር ውስጥ የውጭ ነገሥታትና የታዋቂ ሰዎች ምስል የያዙ በርካታ ቴምብሮች ይገኙበታል፡፡ ከታሪካዊ መታሰቢያ ቀናት ጋር ከተያያዙት ውስጥ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን በባቡር ሐዲድ ዝርጋታ የጉልበት ሠራተኞች ተግባር የሚያሳይ፣ በከሰል ይንቀሳቀስ የነበረው ተጎታች ባቡር፣ ዘመናዊው ባቡርና በአዲስ አበባ የሚገኘው ታሪካዊው የለገሀር ባቡር ጣቢያ ሕንፃ፣ የመጀመርያው አውሮፕላን ቴምብር ከታተመላቸው ይገኙበታል፡፡

የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ፣ የልዑል ራስ ተፈሪ መኰንን ምስል የያዙ ቴምብሮች የታተሙት በ1920 ዓ.ም. አዲሱ ጠቅላይ ፖስታ ቤት ሲቋቋም ነበር፡፡ በንግሥቱቱ ምስል ዙሪያ ‹‹ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ›› የሚል፣ በአልጋ ወራሽ ልዑል ራስ ተፈሪ ምስል ዙሪያ ‹‹ኢትዮጵያ ታበፅሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር›› የሚል አለበት፡፡ ሸዋና ጎጃምን በሚያዋስነው የዓባይ ወንዝ ላይ የተገነባው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ድልድይም በ1943 ዓ.ም. ስድስት ዓይነት ቴምብር ታትሞለታል፡፡

ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ያረፉበት 100ኛ ዓመት በ1960 ዓ.ም. ሲዘከር የንጉሠ ነገሥት ምስሉን በተለያየ መልክ ይዘው ከወጡት ቴምብሮች መካከል በጎንደር ቤተ መንግሥታቸው ከአንበሶች መካከል ተቀምጠው የሚታዩበት አንዱ ነው፡፡ ምስሉ ሥነ ቃሉን ፎክሎሩን የሚያስታውስ ነው፡፡

አሐዳዊት ኢትዮጵያን በማስረፅ የሚታወቁትና ‹‹አባ ታጠቅ›› በተሰኘው የፈረስ ስማቸው የሚጠሩት አፄ ቴዎድሮስ፣ ሚያዝያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም. መቅደላ ላይ ራሳቸውን መሰዋታቸው፣ እምቢኝ ለአገሬ ብለው፣ ‹‹ሽጉጣቸውን አጉርሰው መጉረሳቸው›› ይታወሳል፡፡ እንግሊዞች እንደደረሱም ሙተው ያገኟቸዋል፡፡ በገና ደርዳሪውም እንዳለው፣

‹‹ገደልን እንዳይሉ ሙተው አገኟቸው

ማረክን እንዳይሉ ሰው የለበጃቸው

ምን አሉ እንግሊዞች ሲገቡ አገራቸው

ለወሬ አይመቹም ተንኮለኛ ናቸው፡፡››

በካታሎጉ ውስጥ ከተካተቱት ቴምብሮች እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በርካታ ሥራዎች ይገኙበታል፡፡ በ1950ዎቹ በተከታታይ ዓመታት ‹‹የኢትዮጵያ ታላላቅ መሪዎች›› (Great Ethiopian Leaders) በሚል ርዕስ የነገሥታቱ ባዜን፣ ኢዛና፣ ካሌብ፣ ላሊበላ፣ ይኩኖ አምላክ፣ ዘርዐ ያዕቆብና ልብነ ድንግል ሰባት ቴምብሮች፤ እንዲሁም የሠርፀ ድንግል፣ ፋሲለደስ፣ ኢያሱ፣ ቴዎድሮስ፣ ዮሐንስ፣ ምኒልክ ስድስት ቴምብሮች ታትመዋል፡፡

ለመንፈሳዊ መሪዎች ለጠቢባንም በሳቸው የተሣሉና የታተሙላቸው አቡነ ሰላማ፣ አቡነ አረጋዊ፣ ቅዱስ ያሬድ፣ አቡነ ተክለ ሃይማኖትና ፈላስፋው ዘርዓ ያዕቆብ ናቸው፡፡ እንዲሁም ለዓድዋ ጦርነት ድል 68ኛ ዓመት መታሰቢያም ‹‹ታላላቅ ንግሥታት›› (Great Empresses) በሚል ርዕስ ሳባ፣ እሌኒ፣ ሰብለ ወንጌል፣ ምንትዋብ እና ጣይቱ በሥነጠቢቡ ምናብ ተሥለው ለቴምብር አገልግሎት ውለዋል፡፡ እነዚህ ብቻም አይደሉም የጠቢቡ ትሩፋቶች የአርሲ፣ ጋሞ ጎፋ፣ ጎጃም፣ ከፋ፣ ሐረር፣ ኢሉባቦርና ኤርትራ ባህላዊ አልባሳት ሥዕሎችም ተተምብረዋል (በቴምብር ታትመዋል)፡፡

ፊላቴሊ

ቴምብር መሰብሰብ ጠቃሚ መረጃን ከመስጠት፣ ያለፈን ታሪክ ከመዘከር ባለፈ ባህልንና የተፈጥሮን ገጽታ በማስተዋወቅ ረገድ ሚናው የጎላ ነው፡፡ ቴምብርን ከመሰብሰብ ጋር የሚያዘው ቃል ፊላቴሊ ነው፡፡  ጥሬ ቃሉ የተገኘው ከግሪክ ቋንቋ ሲሆን ‹‹ፊሎስ›› ማለት ፍቅር፣ ‹‹ቴሌይን›› ደግሞ ቀረጥ ማስከፈል ነው፡፡ ከነዚህ ሁለት ቃላት የተገኘው ፊላቴሊ ባንድ በኩል ለቴምብር ያለን ፍቅር ሲያሳይ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ቴምብሮች ተለጥፎባቸው የሚላኩ ደብዳቤዎች ከላኪው በቅድሚያ ቀረጥ የተከፈለባቸው መሆናቸውንና ለተቀባይ ደግሞ ከክፍያ ነፃ መሆናቸውን ያመለክታሉ፡፡

አምስት አሠርታት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የፖስታ ሙዚየም፣ ከተቋቋመበት ጊዜ አንሥቶ እስካሁን ድረስ የታተሙ ኦሪጅል ቴምብሮች አሰባስቦ ይዟል፡፡ ሙዚየሙ በቴምብሮቹ አማካይነት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት ታሪካዊ ቦታዎች፣ ባህላዊ ነክ ቅርሶችን፣ የተፈጥሮ ሀብት ገጽታዎችን፣ ለአገሪቱም ሆነ ለዓለም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ መሪዎችና ታዋቂ ግለሰቦችን አቅፏል፡፡ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ነክ ገጽታዎችን በብሔራዊ ደረጃ የሚያንፀባርቁ ቅርሶችንም አጠቃሎ ይዟል፡፡

ጠቅላይ ፖስታ ቤቱ ከኢትዮጵያ ፖስታ መሥራቹ ከዳግማዊ ምኒልክ ዘመን አንሥቶ እስከ 1961 ዓ.ም. ድረስ የታተሙ ቴምብሮችን የያዘ ካታሎግ ቢያሳትምም ተግባሩን አልቀጠለበትም፡፡ ከ1961 ዓ.ም. በኋላ በየዓረፍተ ዘመኑ የወጡትን የሚያሳይ ካታሎግ የሕትመት ብርሃን ያገኘ አይመስልም፡፡

 የመጨረሻው ባለ ዘውድ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የመጨረሻዎቹ አምስት ዓመታት፣ ከዘመነ ደርግ ኢሕዲሪ (የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ) እስከ ዘመነ ኢሕአዴግ ኢፌዴሪ (የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ) መንግሥታት ድረስ የወጡትን የመታሰቢያ ቴምብሮችና የእነርሱ ጓዞችን ‹‹ሁሉን በያይነቱ ሰፍሮ በልክ በልክ›› አድርጎ በካታሎግ የሚታተሙበት ጊዜ መቼ ይሆን?

የዓለም ፖስታ ኅብረት፣ የተመሠረተበትን ቀንን ኦክቶበር 9ን ይዞ የዓለም ፖስታ ቀን እንደሚያስከብር ሁሉ፣ የኢትዮጵያ ፖስታስ በአገሪቱ አገልግሎቱ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን የተጀመረበትን የካቲት 30 ቀንን (1886)  ይዞ  በብሔራዊ ደረጃ ለምን አያስከበርም?

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...