Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ችግርን ማወቅ የመሰለ መፍትሔ የለም!

ሰላም! ሰላም! እንዴት ከረማችሁ ወገኖቼ? ይኼ ጊዜ እንዴት ይሮጣል እባካችሁ? ታላቁ የየካቲት 1966 ዓ.ም. አብዮት እንኳ ሃምሳ ዓመት ሊሞሉት አምስት ወራት ናቸው የቀሩት፡፡ የዚያ ዘመን ትውልድ ከፊውዳላዊ ወደ ሶሻሊስታዊ ሥርዓት አገሩን ለውጦ፣ ሕዝቡን ሀብታም አድርጎና አንቀባሮ ሊያኖር ያሰበው ትልም ሳይሳካ ቀርቶ ይኸው ዛሬም ድህነት ይጫወትብናል፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹በታላቁ ሕዝባዊ አብዮት መሬት ለአራሹ በሚባል ታላቅ ዓላማ እየተመራ ኢትዮጵያን የእኩልነት ምድር ለማድረግ ትልቅ ዕቅድ ነበረ፡፡ ዳሩ ግን አያያዙን ማወቅ ባለመቻሉ አንድ ትውልድ እርስ በርሱ ተበላልቶ ከንቱ ሆነ ቀረ፡፡ እኔ አሁን እዚህ ዘመን ላይ ሆኜ ያንን ትውልድ የመውቀስ ሞራላዊ ብቃት ባይኖረኝም፣ እኛ ግን ለምን ካለፉት ስህተቶች ተምረን የተሻሉ ነገሮችን ማስመዝገብ አቃተን የሚለው ይከነክነኛል…›› እያለኝ ነበር የሰነበተው፡፡ ወገኖቼ በስንቱ ችግር ስንቆጭ፣ ስንማረር፣ ስንብከነከንና ስንንገፈገፍ እንደምንኖር ሳስበው ይጨንቀኛል፡፡ ይህችን የመሰለች ውብ ምድር ይዘን ምግብ ብርቃችን ሆኖ፣ ሰላም ርቆንና ተስፋ ቢስ ሆነን ለምን እንኖራለን የሚለውን ሳስብማ ዕብደት ይቃጣኛል፡፡ ደግነቱ ለጊዜው ወሰድ መለስ ያደርገኛል እንጂ ጨርሶ አልወሰደኝም፡፡ ወፈፍ ግን አይቀሬ ነው!

ያኔ ነው አሉ ያኔ በአብዮቱ ዘመን፣ ‹‹በጠረጴዛ ዙሪያ በድርድር ሰላም የማይገኝ ከሆነ ከጦር ሜዳ ለማግኘት እንገደዳለን…›› የሚሉት መፈክር ነበር አሉ፡፡ አብዮቱ ‹‹ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም›› በሚባል መፈክር ተጀምሮ ለምን ደም በደም ሊሆን እንደቻለ በርካታ ተጠቃሽ ምክንያቶች አሉ ቢባልም፣ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት የገዛ ደመ ነውጠኛ ባህሪያችን ያመጣው ጦስ እንደሆነ አይጠፋኝም፡፡ ይኼው እንደምታዩት ሰላምን በንግግርና በድርድር ማስፈን ሲገባን፣ እርስ በርስ ደም እየተፋሰስን እኛም ችግራችንም በእጥፍ ተባዝተን እዚህ ደረስን። ወገኖቼ ለሰላም የሚከፈለው ዋጋ በፍቅርና በመተሳሰብ ላይ ቢመሠረት ኖሮ እኮ፣ ዛሬ በየአቅጣጫው እንደምናየው መግደልና ማገት የየዕለት ዜናችን አይሆኑም ነበር፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ከእዚህ ዘግናኝ አረንቋ ውስጥ ለመውጣት የባህል አብዮት ያስፈልገናል…›› ሲለኝ በባህል የተነሳ ደግሞ ሌላ ቅርቃር ውስጥ እንዳንገባ እሠጋለሁ፡፡ እሱ ግን፣ ‹‹የባህል አብዮት ማለት ለዘመናት ይዘን ከመጣነው ጎጂ አስተሳሰብና ልምድ መላቀቅ ነው…›› ቢለኝም፣ ከዚህ ውስጥ እንውጣ ሲባልስ ለምን ብሎ ‹ዘራፍ› እያለ የሚነሳው አተካረኛ ጉዳይ ያሳስበኛል፡፡ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሐሳብ ሲነሳ አይደል እንዴ የተኛው ሁሉ ከጥልቅ እንቅልፉ እየባነነ እየተነሳ ‹በመቃብሬ ላይ› እያለ ትከሻውን የሚያሳየን፡፡ ይደክማል እኮ እናንተ!

ትንሽ ከታገሳችሁኝ ብዙ የማነሳቸው ነገሮች ቢኖሩም የዕለት እንጀራዬን ፍለጋ ስኳትን የማገኛቸው ሰዎች ውሎም እንዳይረሳ፡፡ የብዙዎቹን ባህሪ በአጭሩ ግለጽልን ካላችሁኝ አንደበተ ቁጥብ፣ ወሬኛ፣ ሁሉንም ነገር አማራሪ፣ ክልፍልፍ፣ ከመጠን በላይ ራስ ወዳድ፣ ትሁት፣ ሰብዓዊ፣ ሌባ፣ ውሸታምና ሴሰኛ በየዓይነቱ ሞልተዋል፡፡ አንዱ አንድ ጊዜ በሰው ተዋወቅሁትና ሦስት ያለቀላቸው ጂፕላስ ቪላዎች እንዳሻሽጥለት ቀጠሮ ያዝን፡፡ ያስተዋወቀኝ ሰው እንደነገረኝ ሰውዬው ለአሥር ዓመታት ያህል ብቻ መንግሥት ቤት ሠርቷል፡፡ ለሦስት ዓመት ወረዳ፣ ለሰባት ዓመት ክፍለ ከተማ ማለት ነው፡፡ ይህ የረባ ትምህርት የሌለው ሰው መሬት አስተዳደር ውስጥ ተሸጉጦ ድርሻውን አንስቶ ነው አሉ ሦስት ቪላዎች ገንብቶ የሚሸጠው፡፡ ተገናኝተን ስናወራ አነጋገሩ ቁርጥ የካድሬ ነው፡፡ ‹አግባብ፣ ያለበት ሁኔታ፣ የልማቱ ፋይዳ፣ አጋር አካላት፣ ራዕይ…› እያለ ሲያሰለቸኝ፣ ‹‹ወንድሜ ባለሀብቶች ተርታ ተሠልፈህ እንደ ካድሬ በሰለቹ ቃላትና ሐረጎች ስታወራ ትንሽ አይከብድም…›› ዓይነት አስተያየት ስሰጠው፣ ‹‹አሁንም መሬት ፍለጋ ውሎዬ ወረዳና ክፍለ ከተማ ስለሆነ የንግግር ዘዬውን መተው የለብኝም…›› ብሎ አስደነገጠኝ፡፡ ድንቅ ነው!

እንግዲህ የዘመኑ ነገር እንዲህ ከሆነባችሁ ከመቻል ሌላ አማራጭ ያለ አይመስለኝም። እንኳን ይኼን አጉል አራዳ ስንቱን አስብቶ አራጅ አልቻልነውም እንዴ? መቻቻል ብቻ አይምሰላችሁ እኛን እኛ ያስባለው፣ መቻልም ጭምር ነው። አንዱ በቀደም እንዲህ ስለው፣ ‹‹መቻቻልና መቻል ምን ለየው?›› አለኝ። ‹‹እንዴት አይለያይም? እኩል መሸከምና አሸክሞ መንዳት አንድ ነው ወይ?›› አልኩት። ‹‹ይልቅ እሱን ተወው፣ አንድ ነገር ልመክርህ ነው አመጣጤ…›› ብሎ ተገላምጦ አጠገቡ ሰው እንደሌለ አየት አደረገ። ከዚያ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? ‹‹ጊዜው እየከፋ ነው፣ ሰው ትዕግሥቱ እዚህች አፍጫው ላይ ሆናለች። በቀደም አንዱ ምን እንዳደረገ አልሰማህም?›› እያለኝ ሕፃን ልጅን በሚያባብል አኳኋን መልስ ሲጠብቅ፣ ‹‹እኔ ምንም አልሰማሁም…›› አልኩት። ‹‹…ከፊቱ ያለ አሽከርካሪ መንገድ ይዘጋበታል፣ እሱም ባለመኪና ነው። አሳልፈኝ ብሎ ‘ክላክስ’ ይነፋል። ያኛው ደግሞ ጆሮ ዳባ ልበስ ይለዋል። እንደምንም ታኮ ለማለፍ እየሞከረ በመስኮት ‘ምነው ብታሳልፈኝ?’ ሲለው አጅሬ ምራቁን ተፋበት። ይኼኔ ይኼኛው ድንገት ሽጉጡን ከጎኑ መዞ ግንባሩን ብሎ ገደለው… ገደለው…›› እያለ ‹ገደለው›ን መሄጃ እንዳጣ ሰጋር ፈረስ በመቁነጥነጥ ደጋገመው። አሁን እዚህ ላይ ድንገት ከተከታዩ ሙዚቃ በኋላ ተመልሰን እንገናኛለን ብዬ ጣቢያውን ሁሉ በሞኖፖል እንደያዙት ዋዘኞች፣ የአስቴር አወቀን ‹ፍቅር ገደለ አሉ የወደደውን፣ እሱን ማን አስታሞ ይቀብረው ይሆንን…› ብጋብዛችሁ አትናደዱም? ታዲያ ምነው እኔ ላይ ብቻ!

ኦኦ ለካ ወዳጄ ‹የሰው ትዕግሥት አፍጫው ላይ ናት› ብሎኛል። ግን የሚገርመኝ አፍንጫ በመጥፎ ጠረን ተመቶ፣ በየሄድንበት የዓይነ ምድርና የሽንት ጠረን ተደፍኖ ሲያበቃ ትዕግሥት ማንጠልጠያ ሆና ቀረች ማለት ነው? እውነትም ዕቃ መጣል አንወድም እናንተ? ምናልባት ለዚያ ይሆን ውስጣችንና ጓዳችን በትርኪ ምርኪ ሐሳብና መጣል ባለባቸው አሮጌ ዕቃዎች ተጣቦ ቢያጣብበን፣ በየመንገዱና በየሰው ላይ መውደቅ ያበዛነው? ምናልባት ብዬ ነው፡፡ ቅጥቅጥ አውቶቡስ ላሻሽጥ ሁለት ደንበኞች ቀጥሬ ስለነበር ወዳጄ የሚለውን ብሎ እንዲለቀኝ፣ ‹‹ለምን ወደ ገደለው አትገባም?›› አልኩት። ‹‹አንበርብር ዘንድሮ ሳስበው ብዙ ጠላት ያለህ ነው የሚመስለኝ። ስለአንተ ብዙ እሰማለሁ። እንደሌለው መኖር የሚያዘወትረው ዕድሜውን ሙሉ በድለላ ስም ያጭበረበረውና ያምታታው ገንዘብ ቀልብ ስለነሳው ነው ይሉሃል…›› ሲለኝ አቋርጬው፣ ‹‹ሰውዬ የተከበረ የሥራ ሰዓቴ ላይ ከምትቀልድ የምትለውን አትልም?›› አልኩት። አያናድድም? እርር ቅጥል ብዬ የመጨረሻ ቃሉን ስጠባበቅ፣ ‹‹ልልህ የፈለግኩት መሣሪያ ግዛ ነው…›› አለ። እኔ ደግሞ አንዳንዴ ነገር ይዞርብኝ አይደል? እሱ እንዳለው ወይ ሲሉ እንደሰማው ቀልብ በነሳኝ በቀበርኩት ገንዝብ አንድ ማሽን ገዝቼ ፋብሪካ ከፍቼ ገንዘቤን እንድሠራበት የመከረኝ መስሎኝ ነበር። ለነገሩ በዚህ ጊዜ መልዓክ ካልሆነ ስለፋብሪካና ስለማሽን መትከል የሚያዋይና የሚመክር ወዳጅ ይኖራል ብዬ ማሰብም አልነበረብኝም። ከንቱ ልፋት!

ያው ሁሌም እንደምነግራችሁ በፍቅርና በመተሳሰብ ላይ በተዘረጋው ማኅበረሰባዊ ትዕዛዝ ልጅነቴ ስለተቃኘ፣ ሸብቼም ይኼው ጡት እንዳልጣለ ሕፃን በሞኝነት ጎኔ እገኛለሁ። እናማ፣ ‹‹ይሁን ጥሩ ብለሃል፣ ግን እስኪ መጀመርያ የታማሁትን ዓይነት ሀብታም ልሁንና አስብበታለሁ…›› ስለው፣ ‹‹ኧረ በቀላል ገንዘብ እኔ ራሴ አስመጣልሃለሁ…›› ሲለኝ ግራ ገብቶኝ፣ ‹‹እኮ ምኑን?›› ብለው፣ ‹‹ሽጉጡን!›› ብሎኝ አረፈው። ‹‹እኔ የምሸጎጥበትም፣ የምሸጉጥለትም፣ የሚሸጉጥብኝም ጠላት የለኝም…›› ብዬው አፈፍ ብዬ ስነሳ፣ ‹‹ተው ግዴለህም መጪው ጊዜ አያስተማምንም እየተባለ ነው…›› ብሎ ትዕግሥቴን ጨረሰው። አላወቅኩትም እንጂ ለካ የእኔም ትዕግሥት አፍንጫዬ ላይ ደርሳለች። ‹‹ስማ ልንገርህ አገሬ ይህንን መከራ ተሻግራ ታብባለች፣ ትለማለች፣ ሰላም ይትረፈረፋል፣ ሕዝቧም በሀብት ላይ ሀብት አግኝቶ በደስታና በፍቅር አብሮ መኖሩን ይቀጥላል። አንተ የምትለውን ወሬ ሄደህ ለመሣሪያ ሻጮችና ለአሸባሪዎች ንገራቸው…›› ብዬ ጢሙን አበረርኩለት። እሱ ግን እኔን ጭራሽ እንደ ሞኝ እያየ ሲስቅ ጤንነቱ አጠራጠረኝ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ መሰሉኝ ተስፋችንን ነጥቀው ወደ ገደል የሚመሩን፡፡ ምነው ግን ሰው እንዲህ ጭር ሲል አልወድም ሆነ!

ያልኳችሁን ቅጥቅጥ አውቶቡስ ገዥንም ሻጭንም አገናኝቼ ለማስፈተሽ ላይ ታች እያልኩ ሳለ ማንጠግቦሽ ደወለች። ሳነሳው፣ ‹‹ኧረ ቶሎ ድረስ አንበርብር!›› እያለች አስደነገጠችኝ። የትንፋሽዋ ቶሎ ቶሎ መቆራረጥ የበለጠ አስደንግጦኝ ለሰከንዶች በድን ሆንኩ። እንደምንም ብዬ ራሴን ካረጋጋሁ በኋላ፣ ‹‹ረጋ በይና የሆንሽውን ንገሪኝ?›› ስላት ለአስፔዛ ገበያ ገንዘብ ፈልጋ ነበር የፈለገችኝ። ደንበኞቼ እየተስማሙልኝ ቢሆንም የደረሰውን ድንገተኛ ነገር ነግሬያቸው ጥያቸው ጠፋሁ። በማንጠግቦሽ አሳሳቢነት ወደ ገበያ አብሬ ሄድኩ፡፡ በእግራችን እየተራመድን ዙሪያ ገባውን ስቃኝ አንድ መለስተኛ ገበያ መሳይ መደብር በራፍ ላይ፣ ሽንኩርት ኪሎውን በ25 ብር ሒሳብ የሚል ማስታወቂያ ሳይ በድንጋጤ ክው አልኩ፡፡ የዋጋ ቅናሽ ያስደነግጣል እንዴ? ውዴ ማንጠግቦሽ ሁናቴዬ አስደንግጧት ወደ መደብሩ ማስታወቂያ ስታማትር የእኔ ድንጋጤ ሲጋባባት ይታየኝ ነበር፡፡ ‹‹እንዴ አንበርብር ምን ጉድ ነው?›› አለችኝ፡፡ ድምጿ ውስጥ የመደመም ስሜት የሰማሁ መሰለኝ፡፡ ምን ጉድ ነው አስደንጋጭ እንደሚሆነው ሁሉ የደስታ ስሜት ይፈጥር ይሆን እንዴ? ለማንኛውም እስቲ ጠጋ ብለን እንቃኝ መሰለኝ፡፡ መሆን አለበት!

እኔም ይህ ጉድ በገሃድ ወይስ በሕልም ብዬ እጇን እንደያዝኩ ወደ መደብሩ በራፍ ስጠጋ ሰዎች ተሠልፈዋል፡፡ እኛም የሕልም ይሁን ወይም የገሃድ ገበያ ለመታደም በደመነፍስ ተሠለፍን፡፡ ሽንኩርት ኪሎው 130 ብር ገብቶ እዚህ በ25 ብር ሲሸጥ ገነት ውስጥ እንጂ የምድራዊው ሲኦል ውስጥ ያለን አልመሰለኝም ነበር፡፡ ተራ ደርሶን ውስጥ ስንገባ አንድ ሰው አምስት ኪሎ ሽንኩርት፣ ሁለት ኪሎ ቲማቲም፣ ሁለት ኪሎ ጥቅል ጎመን፣ ሁለት ኪሎ ቀይ ሥር፣ ሁለት ኪሎ ድንች 446 ብር ከምናምን ሳንቲም፣ ወይም ሌሎች የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ከሆኑ ደግሞ ሰባት መቶ ምናምን ብር የሚል ዝርዝር ተለጥፎ አየሁ፡፡ ዞር ብዬ ማንጠግቦሽን ሳያት፣ ‹‹በል እኔ ከአንዱ ዝርዝር አንተ ደግሞ ከሌላው ዝርዝር ገዝተን ይህንን ዕድል እንጠቀምበት…›› ስትለኝ የእኔ አላዋቂነትና የእሷ ብልህ አስተሳሰብ እያስገረመኝ ከበረከቱ ተቋደስን እላችኋለሁ፡፡ ምናለበት የአገራችን የንግድ ሥርዓት እንዲህ በጤናማ መንገድ ቢሳለጥ ብዬም ተመኘሁ፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹እንዲህ ዓይነት የጣምራ ምርቶች ሽያጭ (Bundling) በእኛም አገር በደርግ ዘመን በኅብረት ሱቆች የተለመደ ነበር፡፡ ምን ያደርጋል ማስቀጠል ባለመቻላችን የማንም ሌባ ነጋዴ መጫወቻ ሆንን፡፡ ይህንን ዓይነቱን አዲስ ጅምር ይበል ነው ማለት ነው ያለብን…›› ሲለኝ ለመልካም ተግባር ቸር እንመኝ አልኩ፡፡ ይበል ብለናል!

በሉ እስኪ እንሰነባበት። ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ድህነትና ግጭት አብረው የተቦኩ ይመስል በተራበ አንጀት በመሣሪያ እየተታኮስን ስንገዳደል፣ አቅማችን ኮስምኖ ፋታ ፈልገን ጊዜያዊ ሰላም ያሰፈንን ስንመስል ለሰላምና ለልማት ተነሳሽነትና ርብርብ ካላሳየን ዋጋም ያለን አይመስለኝም። የሰው ልጅ ቢያጣ ቢያጣ እንዴት ምግብ ያጣል? በ21ኛው ክፍለ ዘመን በምግብ ዕጦት ክቡር የሰው ልጅ ሞተ ሲባል ለምን አንደነግጥም?›› የሚለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነበር፡፡ አሁንማ እሱም ስልችት ብሎት ነው መሰል የምግብ ዕጦት ነገር ሲነሳ ይታክተዋል፡፡ መልካም ጅምሮችን ማበረታታት፣ መልካም ዕሳቤዎችን ወደ ውይይት መድረክ ማምጣት፣ ለአገርና ለሕዝብ መቆርቆርን ባህል ማድረግና በአጠቃላይ መልካም ነገሮች ላይ ማተኮር ትልቁ ተግባሩ ነው፡፡ ‹‹ሁልጊዜ ግን ከችግሮቻችንና ከእጥረቶቻችን ተነስተን ወደ መልካም ጎዳና ለማቅናት እንነጋገር…›› የሚለው ሐሳቡ ይጥመኛል፡፡ ለማደግና ለመመንደግ ችግርን ማወቅ የመሰለ መፍትሔ የለም ነው የሚለው፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት