Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊትራኮማን ለማጥፋት በተሠሩ ሥራዎች የተገኙ ተስፋዎች

ትራኮማን ለማጥፋት በተሠሩ ሥራዎች የተገኙ ተስፋዎች

ቀን:

የትራኮማ (በዓይን ማዝ) በሽታ በአብዛኛው እናቶችና ሕፃናትን እንደሚያጠቃ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

በዚህም በርካታ የኢትዮጵያና የአኅጉሪቱ አፍሪካ እናቶችና ሕፃናት፣ እንዲሁም ሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች በበሽታው ተጠቅተው ለከፋ ችግር ሲጋለጡ ይስተዋላሉ።

በቀላሉ ታክመው መዳን ሲችሉ በሕክምና እና በመድኃኒት ዕጦት ምክንያት ብርሃናቸውን አጥተው ዓይነ ሥውር በመሆን ከቤት የሚውሉ ባለ ታሪኮች ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡

የግልና የአካባቢ ንፅህና መጓደል እንዲሁም የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ተደራሽ አለመሆንና ሌሎች በርካታ ምክንያቶች ለትራኮማ መከሰት መንስዔዎች ናቸው።

ትራኮማ በወቅቱ ሕክምና ካገኘ በቀላሉ የሚድን በሽታ ሲሆን፣ በአንፃሩ ክትትል ካልተደረገለት የዓይን ብርሃንን እስከ ወዲያኛው የሚነጥቅ በሽታ ነው።

 በሽታውን ለማጥፋት የጤና ሚኒስቴርና ኦርቢስ በጎ አድራጎት ድርጅት በርካታ ሥራዎችን እየሠሩ እንደሚገኙ መስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄዱት ስብሰባ ገልጸዋል።

በቀላሉ ሊድን በሚችለው ትራኮማ በሽታ ሳይጠቁ ቅድመ መከላከል ከማድረግ በተጨማሪ፣ በበሽታው ለተጠቁ ግለሰቦች የሕክምና አቅርቦት ለማመቻቸት በሚያስችሉ አጀንዳዎች ዙሪያ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ተወያይቷል።

በሽታውን ለመቀነስ ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ በመሆኑ አንፃራዊ መሻሻል ቢኖርም፣ አሁንም በመድኃኒት አቅርቦት እጥረት በርካቶች ለበሽታው ተጋላጭ እንደሆኑ በውይይቱ ወቅት ተነስቷል።

የትራኮማ በሽታን ቀድሞ ከመከላከል ጀምሮ የተጠቁ ሰዎችን ሕክምና በመስጠት እንዲሁም ከዓይን ቆብ መቀልበስ ጋር ተያይዞ ለዓይነ ሥውርነት ከመዳረጋቸው በፊት፣ ቀዶ ሕክምና በማድረግ ብዙዎችን ከዓይነ ሥውርነት መታደግ መቻሉን የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

በተለይ ደግሞ ላለፉት ሁለት አሠርታት መከላከልን መሠረት ያደረጉ ሥራዎች ተሠርተዋል ያሉት ሚኒስትሯ፣ የንፁህ ውኃ አቅርቦትን ከማስፋፋት ጀምሮ የግል ንጽሕና ማስጠበቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑን፣ ለማኅበረሰቡም አስፈላጊው ማስገንዘቢያ መሰጠቱን አብራርተዋል።

ትራኮማ በወቅቱ ሕክምና ካላገኘ እየከፋ ሲሄድ የዓይን ቆብ መቀልበስን የሚያስከትል ሲሆን ቶሎ የዓይን ቆብ ቀዶ ሕክምና ካልተደረገለት ለዓይነ ሥውርነት ያጋልጣል ብለዋል።

ለ1.6 ሚሊዮን ወገኖች የዓይን ቆብ ቀዶ ሕክምና በማድረግ ከዓይነ ሥውርነት መታደግ ሳይገልጹ አላለፉም።

አሁንም ቢሆን በሽታውን ለመቀነስ ሰፊ ሥራን መሥራትን ይጠይቃል ያሉት ሚኒስትሯ፣ የንፁህ ውኃ አቅርቦትን ከማስፈን ባለፈ የግል ንጽሕና ላይ ኅብረተሰቡ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረውና ራሱን ከበሽታው እንዲከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እንደሚሠሩ አስታውቀዋል።

ኅብረተሰቡ በሽታው ሲከሰትበት ሕመሙን ችሎ መኖር ሳይሆን፣ አገልግሎቱን በአቅራቢያው ባሉ የጤና ጣቢያዎች እንደሚያገኝ ተገንዝቦ ቶሎ በመታከም ራሱን ከዓይነ ሥውርነት መታደግ እንደሚኖርበት ሊያ (ዶ/ር) መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ቀጣይነት ያለው የማኅበረሰብ ግንዛቤን በማሳደግ በተለይ ዋና ስትራቴጂ የሆነውን ቀዶ ሕክምና፣ መድኃኒት በአግባቡ መጠቀም፣ ፊትን በተገቢው መንገድ መታጠብና አካባቢን በንፅህና በመያዝ የባህሪ ለውጥ በማምጣት ትራኮማ የማኅበረሰብ ጤና ችግር እንዳይሆን በትኩረት እየተሠራ እንደሆነም በጤና ሚኒስቴር ትኩረት የሚሹ ሐሩራማ በሽታዎች መከላከል ዴስክ ኃላፊ የሆኑት አቶ ፍቅሬ ሰይፈ ገልጸዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የተገኙት የእንግሊዝ ዘውዳዊ ቤተሰብ የሆኑት መስፍኒተ ኤደንብራ ልዕልት ሶፊ፣ ትራኮማን ለመከላከል የማኅበረሰብ ጤና ችግር ወደማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ በሚሠራው ሥራ የእንግሊዝ መንግሥት እየደገፈ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 የዓይን አምባሳደር የሆኑት ልዕልቲቱ አያይዘውም የትራኮማ በሽታን ለማጥፋት ከማስተማርና ከማስገንዘብ ባለፈ፣ በትምህርት ተቋማት የንፁህ ውኃ አቅርቦትና የመፀዳጃ ቤቶች ይዞታን ማሻሻል አስፈላጊነቱን ጠቅሰዋል። ከልማት አጋሮች ጋር በመሆንም በኢትዮጵያ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ያለውን የንጹህ ውኃ አቅርቦትና የመፀዳጃ ቤቶች ችግር ለመቅረፍ መንግሥታቸው እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።

 

ምስክርነት

በመድረኩ በበጎ አድራጎት ድርጅቶች ድጋፍና ክትትል ባገኙት ሕክምና ከበሽታው በቀላሉ ያገገሙ ሰዎችም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ከእነዚህም መካከል ወ/ሮ ነፊሳ ከድር ከጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ የመጡ እናት ይገኙበታል፡፡

ሕክምና ከማግኘታቸው በፊት እሳቸውና ባለቤታቸው በትራኮማ ይሰቃዩ እንደነበር የተናገሩት ወ/ሮ ነፊሳ፣ በአቅራቢያቸው በሚገኝ ጤና ጣቢያ መታከም ቢፈልጉም ነፃ ሕክምና መኖሩን ባለማወቃቸው ግን ሳይታከሙ ሕመሙን ችለው መቆየታቸውን፣ በሌላ በሽታ ታሞ የነበረ ልጃቸውን ለማሳከም በሄዱበት አጋጣሚ መረጃውን አግኝተው መታከማቸውን ገልጸዋል፡፡

እሳቸው ሕክምናውን በነፃ ካገኙና የዓይናቸው ጤንነት ከተመለሰላቸው በኋላ ‹‹በትራኮማ በሽታ መሰቃየት በእኔ ይብቃ›› በማለት በአካባቢያቸው ያሉ ከ80 በላይ ታማሚዎች ሕክምና ማግኘት እንደሚችሉ ቤት ለቤት እየተዘዋወሩ በማስተማር ወደ ጤና ጣቢያ ሒደው ሕክምና እንዲያገኙ ማድረጋቸውን ምስክርነት ሰጥተዋል።

በዚህ ቀና ተግባራቸውም ከሰዎች ምሥጋና እንደተቸራቸውም ከወ/ሮ ነፊሳ በተጨማሪ ሌሎች ታማሚዎችም ከትምህርታቸውና ከሌሎች ማኅበራዊ እንቅስቃሴያቸው ተገድበው የነበሩ ወጣት ሴቶችም ተሞክሯቸውን አካፍለዋል።

አንዳንዶቹ ለበሽታው መድኃኒት መኖሩን ሳያውቁ ሌሎች ደግሞ ከፍለን የምንታከምበት ገንዘብ የለንም በማለት በበሽታው ሲሰቃዩ መቆየታቸውን የተናገሩ ሲሆን፣ ነፃ ሕክምና መኖሩን ካወቁ በኋላ ወደ ሕክምና ሄደው ተገቢውን ክትትል በማድረግ በአሁኑ ወቅት ወደ ቀድሞ ጤንነታቸው ተመልሰው በሰላም ሥራቸውን እየሠሩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...