በኢትዮጵያ በሴቶች ላይ የሚደርሰው ፆታዊ ጥቃትና የመብት ጥሰት እንዲገታ መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መሥራት ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
ሆኖም ሥር የሰደደውን በሴቶች ላይ የሚደርሰውን በደል ለማስቆም፣ እንዲሁም ትክክለኛ የሆነ ፍትሕ እንዲያገኙ ለማስቻል መንግሥት ፖሊሲዎች ቀርፆ ቢሠራም፣ ያን ያህል ለውጥ ማምጣት እንዳልቻለ ይወሳል፡፡ በተለይ ግጭትና ጦርነት ባሉባቸው ሥፍራዎች ሴቶች የእልህ መወጫ እስከሚመስሉ ድረስ የፆታዊ ጥቃት ሰለባ መሆናቸው ችግሩን ይበልጥ አባብሶታል፡፡
ይሁን እንጂ መፍትሔ በማፈላለግ ረገድ መንግሥታዊም ሆኑ ያልሆኑ ተቋማት የተለያዩ ጥረቶችን ማድረጋቸው አልቀረም፡፡ ታዳጊ ሴቶችን በሁሉም ቦታ በማንኛውም አጋጣሚ ብቁ እንዲሆኑ ማድረግ የሚለውን መርህም ሰንቀው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡
በየዓመቱ ኦክቶበር 11 ቀን (መስከረም 30) የሚከበረውን የዓለም የታዳጊ ሴቶች ቀንን፣ ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ከሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ‹‹ታዳጊ ሴቶችን እናብቃ፣ መብትና ደኅንነታቸውንም እንጠብቅ›› በሚል መሪ ቃል በሒልተን አዲስ በውይይት አክብሯል፡፡
በውይይት መድረኩ፣ ንግግር ያደረጉት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ አማካሪ ወ/ሮ ዘቢዳር ቦጋለ እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ አሁንም ድረስ ታዳጊ ሴቶች ለተለያዩ የመብት ጥሰቶች ከመዳረጋቸው ባለፈ፣ ለልዩ ልዩ አዕምሯዊ፣ አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ እንዲሁም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየተጋለጡ ነው፡፡
በተለይ ከተዛባ የሥርዓተ ፆታ ግንኙነትና በማኅበረሰቡ ዘንድ እየተተገበሩ ባሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና ጥቃቶች፣ እንዲሁም በአስፈጻሚው አካላት መካከል የሚታየው የቅንጅታዊ አሠራር መጓደል የተነሳ ችግሩ እየባሰ መምጣቱንም አክለው ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚነሱ ግጭቶችና ተፈጥሯዊ አደጋዎች በርካታ ቁጥር ያላቸው ሕፃናትና ታዳጊ ሴቶች ከመኖሪያ ቤታቸው እንደሚፈናቀሉ፣ ከትምህርት ገበታቸውም ከመሰናከል በዘለለ ፆታዊ ጥቃት የሚደርስባቸው መሆኑን አማካሪዋ ተናግረዋል፡፡
በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ ግጭቶች ምክንያት ታዳጊዎች ለከፋ ችግር እንዳይጋለጡ ሊጠበቁ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል፡፡
በተለይ ወላጆችና ትምህርት ቤቶች በልጆች አስተዳደግና ሰብዕና ቀረፃ ላይ የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ፣ ታዳጊ ሴቶችን ማዕከል የሚያደርግ ተግባሮች መፈጸም እንደሚገባቸው፣ ተስፋቸውን የሚያደናቅፉ ማናቸውንም ነገሮች መግታት እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል፡፡
ዓለም አቀፉ የታዳጊ ሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ፣ ታዳጊ ሴቶችን ማብቃት በሚቻልበት አግባብ ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጥልቀት ለመወያየትና የቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማመላከት እንዲረዳ፣ ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ያዘጋጀው መድረክ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የሚኒስትር ደኤታዋ አማካሪ አስረድተዋል፡፡
የፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ መቅደም ጉልላት እንደገለጹት፣ ሴት ልጆች መብታቸው ተጠብቆ የፈለጉትን አገልግሎት እንዲያገኙ ተቋሙ ፕሮግራም ቀርፆ እየሠራ ነው፡፡
በተለይ በአገሪቱ በሚፈጠሩ ግጭቶች ላይ የሚታየውን የመብት ጥሰትና ፆታዊ ጥቃት ለማስቀረት በየጊዜው ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት ሥራ አስኪያጇ፣ ይህንንም ተፈጻሚ ለማድረግ ተቋሙ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር የሚሠራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም በእንዲህ ዓይነት ችግር ውስጥ ኖረው፣ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ቦታው ድረስ በመሄድ የትምህርት ግብዓት፣ የምግብ፣ የአልባሳትና ሌሎች ነገሮች ማቅረብ መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡
ሴት ልጆች የተለያዩ የመብት ጥሰቶችን ሲፈጸምባቸው አዕምሯዊ፣ ሥነ ልቦናዊና አካላዊ ጉዳት ይደርስባቸዋል ያሉት ሥራ አስኪያጇ፣ ይህንን ችግር ለማለፍና መብቶቻቸውን ለማስከበር መንግሥት ቋሚ የሆነ አሠራር መዘርጋት ይኖርበታል ብለዋል፡፡