Monday, December 11, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የተቀደሰው የሰላም ጥረት በድሽታ ግና ምድር

በገብሬ ይንቲሶ ደኮ (ፕሮፌሰር)

ድሽታ ግና የመነጨው በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከሚገኘው የአሪ ብሔረሰብ ነው። የድሽታ ግና ዕሴቶች ፈጣሪን ማመሥገን፣ ዕርቀ ሰላም ማውረድ፣ የተቸገሩትን መርዳት፣ ፍቅርና አብሮነትን መስበክ፣ እንዲሁም ውስጣዊና ውጫዊ ገጽታዎችን ማፅዳት/ማስዋብን ያካትታል። በ2014 ዓ.ም. የድሽታ ግና ምድር (አሪ) ክፉኛ በነውጥ ተመቶ ብዙ ጉዳት ደርሶ ነበር። ሰሞኑን የአዲሱ አሪ ዞን ከፍተኛ አመራር የዞኑን ሰላም ቀዳሚ አጀንዳ በማድረግ፣ በየቦታው ሕዝብ ማወያየት መጀመሩ ይበል የሚያሰኝ ብቻ ሳይሆን፣ ጤናማ ዕሳቤ ያላቸው ሰዎች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያደርጉ ዘንድ የሚያነሳሳ የተቀደሰ ጅማሮ ነው። 

ዘወትር እንደሚወሳው ሰላም ከሌለ ወጥቶ መግባት፣ ወልዶ መሳም፣ ሠርቶ መኖርና ልማት ብሎ ነገር የለም። አንድ እጅ ብቻውን አያጨበጭብም፡፡ አንድ እንጨት ብቻውን አይነድም እንደሚባለው፣ ሰላምን ለማረጋገጥ የአመራሩ ጥረት ብቻ በቂ አይደለም። ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ያለ ቅድመ ሁኔታ ቂምና ቁርሾን አስወግደው የሰላም ግንባታው ተባባሪ ሊሆኑ ይገባል። ሲጀመር የአስታርቁን ጥያቄው የብዙኃኑ ከተማና ገጠር ሕዝብ ጥያቄ ስለሆነ፣ የአመራሩ ጥረት ይሳካል የሚል እምነት አለኝ። ይህ የሰላም ተነሳሽነት በአንድ ዞን የተስተዋለ ቢሆንም፣ በመልካምነት ሊጠቀስ የሚገባ ተሞክሮ ነው።

ከዚህ ቀደም አሪ ውስጥ ተከስቶ የነበረውን የግጭትና የቁርሾ ዓውድ መጥቀስ ለተሟላ ግንዛቤ ይረዳል። በሚያዝያ ወር 2014 ዓ.ም. በቀድሞ የደቡብ ኦሞ ዞን (በአሁኑ የአሪ ዞን) በተለይም በጂንካ፣ በጋዘር፣ በሜፀር፣ በቶልታ፣ በበርካና በሸንጋማ ቢሊ ከተሞች አስከፊ ግጭት ተቀስቅሶ የአካል ጉዳት መድረሱ፣ ንብረት መውደሙ፣ ዜጎች መፈናቀላቸውና ሕይወት መጥፋቱ፣ በኋላ በነፃ የተለቀቁ ንፁኃን ወጣቶች ያለ ጥፋታቸው እስር ቤት ለብዙ ወራት መማቀቃቸው ይታወቃል። በግጭቱ ተፈናቅለው እስካሁን ወደ ቀዬአቸው ያልተመለሱ ወገኖችና በጥርጣሬ ታስረው እስካሁን ያልተፈቱ ዜጎች አሉ። ሚያዝያ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. የተከሰተው አሳዛኝ ጉዳትና ይህንን ተከትሎ የተስተዋሉ አስከፊ በደሎች በሰላምና በፍቅር ይኖር በነበረ ማኅበረሰብ ውስጥ ያላስፈላጊ ክፍፍል፣ ጥላቻ፣ ቁርሾና ያለ መተማመን አስከትለዋል። ብዙ ሰዎች የክስተቱ ሰለባ ሆነዋል።

እኔም የሴረኞቹ አንዱ ታርጌት እንደነበርኩ ብዙዎች ያውቃሉ። የግጭቱ ጠንሳሾችና ተንኳሾች በፌስቡክ ዘመቻና በስብሰባ ወቅት ቀድመው ከጣሪያ በላይ በመጮህ፣ ያለ ምንም መረጃና ማስረጃ የእኔን ስም ለማጠልሸት መሞከራቸው ይታወሳል። የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በነበርኩበት ጊዜ ከሕወሓት ተልዕኮና ገንዘብ ተቀብዬ የአሪ ወጣቶችን (ሸከን) ያደራጀሁ አስመስለው ጥላቻ ዘርተዋል።

ከጀርመን በኢንተርፖል ተይዤ እንደምመለስ ጆሮ ለሰጣቸው ሁሉ ወሸከቱ። ዘጠና ዓመት ለተጠጋች አዛውንት እናቴ ልጅሽ ታስሮ መጥቶ በተወለደበት ሜፀር ከተማ ላይ ይሰቀላል ብለው ልቧን ሰበሩ። ታናሽ ወንድሜ ያለ ምንም ጥፋት አምስት ወራት ታስሮ በነፃ ተለቀቀ።

 አሳሳች የፌስቡክ ነውረኞችና ተራ የሠፈር ወሬኞች በእኔ ሰበብ በአሪና በሌሎች ወገኖች መሀል የከፋ ዕልቂት እንዲከሰት ውሸት እየፈበረኩ በድብቅ በፌስቡክ ብቻ ሳይሆን በይፋም በየስብሰባው መድረክ ሲቀሰቅሱ ሃይ ባይ አመራር ከቶ አልነበረም። ይልቁንም አንዳንዱ አመራር ውሸቱን ይበልጥ ያራግቡ እንደነበርና በሐሰት ውንጀላ እኔን ለመክሰስ ጭራሽ የእስር ማዘዣ ማውጣታቸውን ሰማሁ። በግፍ እስከ እዚህ ርቀት ለመሄድ ድፍረቱ ከነበራቸው በተቀነባበረ የሐሰት ውንጀላ ስንቱ ታስሮ ይሆን? 

ትምህርት ቤትና ሆስቴል በማሠራት፣ ድሽታ ግና (የአሪ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ በዓል) እንዲያንሰራራ አስተዋጽኦ በማድረግና የአሪ ሕዝብ ልማት ማኅበር ምሥረታን በማገዝ ሕዝቡን በተለይም ሸከኖችን አነቃ ብለው የሚከሱኝም ነበሩ። እነዚህ ተግባራት ሁሉንም ዜጋ የሚጠቅሙ የሚያስመሠግኑ የልማት ሥራዎች እንጂ የሚያስኮንኑ ጥፋትና ወንጀል አልነበሩም፣ አይደሉምም።

‹‹እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል፣ ውሸትና ስንቅ እያደር ይቀላል›› እንዲሉ፣ ይህ ሁሉ ቅጥፈትና በጥቂት ክፉ ግለሰቦች የተቀነባበረ አደገኛ ሴራ እንደነበረ ተረጋገጦ፣ እነዚህ የዘመናችን ጉዶች ይሄው ዛሬ ተጋለጡ፣ ክፉኛ ቀለሉ፣ አፈሩ፣ አንገትም ደፉ። ከዚህ በመነሳት የክፋት ተግባር ከሕዝብ፣ ከመንግሥትና ከፈጣሪ ዕይታ ውጪ እንደማይሆንና የውሸት መንገድ ወደ ውድቀት እንደሚያመራ የማይረዳ ሰው ካለ ምንጊዜም አይገባውም። ከግጭቱ በፊት ጀምሮ ባሠራጩት ውሸትና በረጩት መርዝ ስንቱ በግፍ እንደተጎዳና ስንቱን እንዳሳሳቱ ቤቱ ይቁጠረው። 

አንዳንዴ በውስጥ አምቆ ከመብከንከን አውጥቶ መተንፈስ ይረዳል። ከላይ የተዘረዘረውን ስለራሴ ትንሽ መተንፈስ የፈለግኩበት ምክንያት አውርቼው ወጥቶልኝ መቋጫና ማሳረጊያ ለማበጀት እንጂ፣ ቀጣይ የተቋጠረ ቂም መኖሩን ለማመልከት አይደለም። ከእንግዲህ ወደፊት እንጂ ወደኋላ ማየት አልፈልግም። ከይቅርታ ልብ ሌላ የበቀል ልብ እንዲኖረኝ ስለማልሻ እነማን በውሽት ስሜን እያጠለሹ ውድቀቴን ይመኙ እንደነበር ለማወቅ አልፈግልም። እኔ በስም ባላውቃቸውም በከተሞች የጥላቻ ዘር መዝራታቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁ ሰዎች ይታዘቧቸው። ምናልባት የሚሠሩትን አያውቁ ይሆናልና የሰማዩ ጌታ ይቅር ይበላቸው፣ ወደ ልቦናቸውም ይመልሳቸው። 

ከእንግዲህ የእኔ ምኞትና ተስፋ በአሪ ዞን፣ በጎረቤት ዞኖችና በመላው አገራችን ግጭት ተወግዶ፣ ሰላም ሰፍኖና ልማት ተረጋግጦ ማየት ብቻ ነው። ከግጭት የሚያተርፉ ጥቂት ሴረኞች ሲቀሩ የአብዛኛው ሕዝብ ፍላጎትም ከዚህ የተለየ እንዳልሆነ እረዳለሁ። ነገር ግን ስለተመኘንና ተስፋ ስላደረግን ብቻ ሰላምና ልማት ስለማይመጣ፣ የአሪ ዞን ከፍተኛ አመራር ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ከልብ በመቀበልና ተነሳሽነታቸውን በማበረታታት ለተግባራዊነቱ መረባረብ የሁላችንም ኃላፊነትና ግዴታ ነው። እኔ በበኩሌ በእኔና በቤተሰቤ ላይ የደረሰውን በደል ይቅር ብዬ በመተው ለአካባቢያችን ሰላምና ልማት የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ በመንቀሳቀስ ላይ እገኛለሁ። ሌሎችም ይህንን ፈለግ መከተል ከቻሉ ወደ ቀድሞ ፍቅራችን ለመመለስ ጊዜው ሩቅ አይሆንም።

ዘላቂ ሰላም ለማረጋጋጥ ወደ ይቅርታና ዕርቅ ስናቀና የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱና በጥፋት ሳይሆን በፖለቲካ ሴራ ቅንብር የታሰሩ ካሉ እንዲፈቱ ያልተቆጠበ ትብብር ማድረግ ከሁሉም አካላት ይጠበቃል። ሴረኞች ትናንት በረቀቀ የውሸት ጥበብና ትንኮሳ ያጋጩት ሕዝብ ዛሬ እንዲታረቅ ስለማይፈልጉ አዛኝ ቅቤ አንጓች መስለው ሰበብ እየፈጠሩ ለሰላም ጥሪው እንቅፋት እንዳይሆኑ መንቃት ያስፈልጋል። በአስመሳዮች ሴራ ሕዝቡ ሁለት ጊዜ መታለል የለበትም።

አዲሱን የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር አመራር መደገፍና አሁን ጊዜ ሰጥቶ በኋላ በውጤታቸው መገምገም ሲገባ፣ ገና ከወዲሁ ሥራ ሳይጀምሩና ሳንደግፋቸው መተቸትና ማጣጣል ተገቢ አይደለም። በእርግጥ ሒስ ደካማ ጎንን ለማጠናከር ታስቦ በቅንነት የሚቀርብ ከሆነ ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም። ይህን መሰል ገንቢ ትችት ታዲያ በፌስቡክ አደባባይ መውጣት ሳያስፈልግ በአካል፣ በቀጥታ ስልክ ወይም በውስጥ መስመር ማድረስና መነጋገር ይቻላል። 

በሌላ በኩል አዲሶቹ አመራሮች የሰዎች ስብስብ እንጂ እንከን የለሽ ጻድቃን አይደሉም። ስለዚህ በሚቀርቡት ትችቶች ምንም ሳይረበሹና መሠረተ ቢስ አድርገውም ሳያጣጥሏቸው ቅሬታዎችን እያዳመጡ፣ ውስጣቸውንም እየፈተሹና ተገቢውን ምላሽ ሳይዘገይ በወቅቱ እየሰጡ እኛ ካገዝናቸው ሕዝቡን ያሻግራሉ የሚል እምነት አለኝ። ይህ ዕይታ የአሪ ዞን አመራርን ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም በቅንነት ሕዝብ ለማገልገል ቆርጦ የተነሳን የመንግሥት መዋቅር ይመለከታል። 

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአንትሮፖሎጂ ፕሮፌሰርና የጂንካ ዩኒቨርሲቲ መሥራች ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ከምርምር ሥራዎቻቸው መካከል የብሔረሰቦች ግንኙነት፣ የግጭት አፈታት ዘዴዎች፣ የአገር በቀል ዕውቀቶችና ልማዳዊ ሕጎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሚና፣ እንዲሁም ሠፈራና የምግብ ዋስትናን የተመለከቱ ይገኙባቸዋል፡፡ አሁን የግል ተመራማሪና አማካሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው gebred@gmail.com. ማግኘት ይቻላል፡፡     

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles