በአገር አቀፍ ደረጃ እስከ በስድስት ዓመታት ውስጥ ለ20 ሚሊዮን ወጣቶች የሥራ ዕድልን ለመፍጠር ማቀዱን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
አገሪቱ ያለችበት ችግርና ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮቶች ተደማምረው የራሳቸውን አሉታዊ ተፅዕኖ ቢያሳድሩም፣ በእነዚህ ችግሮች ውስጥ በመሆን የሥራ ዕድሎች እየተፈጠሩ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ደኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን አስታውቀዋል፡፡
ከፍተኛ የሥራ ዕድል ከሚፈጠርባቸው ዘርፎች መካከል የቴክኖሎጂ ዘርፍ አንዱ ነው ያሉት አቶ ንጉሡ፣ አገራዊ የሰላምና የፀጥታ ሁኔታም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር በሚገኙ ኢንቨስተሮች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ነገር ግን በተጨባጭ ምን ያህል ተፅዕኖ እየደረሰ ነው የሚለውን መረጃ የሚመለከተው መሥሪያ ቤት የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ስለሆነ ዝርዝሩን ከዚያ ማግኘት እንደሚቻል ጠቁመዋል፡፡ አገራዊ ሰላም ካልተረጋገጠና ዜጎች በሰላም ተንቀሳቅሰው መሥራት የሚችሉበት ሁኔታ ካልተፈጠረ ኢንቨስትመንቱ ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ያሳድራል ብለዋል፡፡
ሰላም ሲረጋገጥ ምቹ የሆነ የሥራ ዕድል ፈጠራ ይኖራል ያሉት ሚኒስትር ደኤታው፣ የሥራ ዕድል መፍጠር ደግሞ ሰላምን ለማረጋገጥ መንገድ ይሆናል ብለዋል፡፡
አቶ ንጉሡ ይህንን የተናገሩት ጥቅምት 10 ቀን 2016 ዓ.ም. በዲጂታል ኢኮኖሚ ላይ ትኩረት ያደረገውን የእንቆጳ ጉባዔ ባስጀመሩበት ወቅት ነው፡፡
ጉባዔው ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም ለዓለም ለማስተዋወቅና የአገር ውስጥ እንዲሁም የውጭ ኢንቨስተሮችን በዘርፉ ለማሰማራት ያግዛል ብለዋል፡፡
እንቆጳ ማለት በግዕዝ ‹‹የወርቅ ጥሬ ሀብት›› ማለት ነው ያሉት አቶ ንጉሡ፣ ይህንን ጥሬ ሀብት ለዓለም ካስተዋወቅነውና በደንብ ከተጠቀምንበት የሚያብረቀርቅ ሀብት ይሆናል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ከፍተኛ የሆነ የወጣት ኃይል መኖሩና የዲጂታል ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት በአገሪቱ እየተስፋፋ መምጣቱ ሲታይ ያለንበት አካባቢ ምቹ የወጣቶች ከፍተኛ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ እንደሆነ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር የአገር በቀል ኢኮኖሚን በተመለከተ ትኩረት ከተሰጠባቸው ዘርፎች የዲጂታል ቴክኖሎጂው ቀዳሚ መሆኑን አቶ ንጉሡ አብራርተዋል፡፡
በጉባዔው ከ26 በላይ አገሮች የታደሙ ሲሆን፣ በመድረኩም ልምድ ከማጋራታቸው ባሻገር ኢትዮጵያ ያላትን ፀጋና አቅም አይተው የሚሄዱበት ይሆናል ብለዋል፡፡
ይህም የሥራ ዕድልን ለመፍጠር መልካም አጋጣሚ ይሆናል ሲሉ ሚኒስትር ደኤታው አብራርተዋል፡፡
የጉባዔው ዋና ዓላማ በቴክኖሎጂ የተሰማሩ ኩባንያዎች ድርጅቶችና ኢንቨስተሮች ኢትዮጵያ ያላትን አቅም እንዲመለከቱና ዕድል መፍጠር፣ አዲስ ቴክኖሎጂ ያፈለቁና ወደ ሥራ የገቡ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎችም ሐሳባቸውን የሚገልጹበት መድረክ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡