‹‹እወድሻለሁ›› ስልሽ
ደግመሽ እየደገመሽ ‹‹ምን ያህል?›› አትበይኝ
የመውደድን ልኬት
በጭራሽ የማላውቅ የዋህ አፍቃሪ ነኝ
‹‹ዓይንሽ እንደምን ነው?
ጥርስሽ እንደምን ነው?
ከንፈርሽ እንዴት ነው?›› ብዬ ብጠይቅሽ
ምን ዓይነት ነው መልስሽ?
ልክ እንደዛ ማለት የመውደድ ልኬት ነው
የሆነውን አውቀሽ ይህ ነው የማትይው
ከዚህ እስከ ሰማይ . . .
ያለውን ርቀት የትኛው ሰው ለካ?
የፀሐይን ሙቀት
የጨረቃን ደረት
የኮከብን ውበት
የምድሪቷን ክብደት የባህሩን ዲካ
የቱ ሰው አወቀ የትኛውስ ለካ?››
ልክ እንደዛ ማለት የመውደድ ልኬት ነው
የሆነውን አውቀሽ ይህ ነው የማትዪው
- ሰሎሞን ሳህለ ‹‹የልብ ማኅተም›› (2010)