Wednesday, December 6, 2023

የትውልድ ስብራት ሊያስከትል የሚችለው ግጭት አመጣሽ የትምህርት መቆራረጥ ቀውስ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በሚያዝያ ወር 2015 ዓ.ም. የጀመረውና ስድስት ወራት ያስቆጠረው የሱዳን ጦርነት፣ ከወዲሁ 19 ሚሊዮን ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ማራቁ ተነግሯል፡፡ በሱዳን በዘንድሮው ትምህርት ዘመን ተማሪዎችን ለመቀበል የማይችሉ ትምህርት ቤቶች በርካታ መሆናቸውን፣ የተመድ ዓለም አቀፍ የሕፃናት ፈንድ (UNICEF) እና የዓለም የሕፃናት አድን ድርጅት (Save the Children) በጋራ አስታውቀዋል፡፡

በሱዳን በአሁኑ ጊዜ ከሦስት ሕፃናት አንዱ ማለትም 6.5 ሚሊዮን ታዳጊዎች በብጥብጥና በፀጥታ መቃወስ የትምህርት ዕድል አጥተዋል ተብሏል፡፡ በግጭት ቀጣናዎች 10,400 ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፡፡ በተያያዘም የፀጥታ ሥጋት ባለባቸው ቀጣናዎች 5.5 ሚሊዮን ታዳጊዎች ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ አስቻይ ሁኔታ መኖር አለመኖሩን ባለሥልጣናት ማረጋገጫ መስጠት አለመቻላቸው ታውቋል፡፡

በሱዳን ጦርነቱ በይፋ ከመጀመሩ ከሚያዝያ በፊት ሰባት ሚሊዮን ታዳጊዎች ትምህርታቸውን አቋርጠው ነበር፡፡ ጦርነቱ እንደ እስካሁኑ ተባብሶ የሚቀጥል ከሆነ ደግሞ በሱዳን አንድም ታዳጊ የትምህርት ቤት ደጅን መርገጥ አይችልም በማለት ነው፣ የዩኒሴፍና የሴቭ ዘ ቺልድረን ሰሞነኛ ሪፖርት ያተተው፡፡

ግጭትና ጦርነት የትምህርት ዕድልን ከሚዘጉ ችግሮች ዋናው ነው ይባላል፡፡ በዓለማችን ከትምህርት ገበታ የተነጠሉ ታዳጊዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ ይወሳል፡፡ በግጭት አዙሪት ውስጥ በሚገኙ አገሮች ደግሞ ከትምህርት ገበታ የሚነጠሉ ታዳጊዎች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ነው የሚነገረው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሱዳን፣ ሶሪያ፣ የመን፣ በርማ፣ ጋዛ፣ ዩክሬን፣ ናጎርኖ ካራባኽና በሌሎችም የግጭት ቀጣናዎች በርካት ታዳጊዎች በትምህርት ዕጦት የሚቀጡባቸው አካባቢዎች መሆናቸው ተደጋግሞ ይዘገባል፡፡

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ (Universal Declaration of Human Rights) የሰው ልጆች ትምህርት የማግኘት መብት፣ በማንኛውም ሁኔታ ሊገደብ የማይችል መሆኑን ደንግጓል፡፡ ይሁን እንጂ ግጭት በተፈጠረባቸው ቀጣናዎች ትምህርት ቤቶች መውደማቸውና የተማሪዎች ሕይወት አደጋ ላይ መውደቁ የተለመደ ዓለም አቀፍ ችግር ሆኗል፡፡

ለምሳሌ በግጭት ቀጣናዎች የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ለማጠናቀቅ የሚበቁ ተማሪዎች ቁጥር 30 በመቶ ብቻ ነው፡፡ በስደተኞች/ተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ ከሚገኙ ሕፃናት ውስጥ ትምህርት ከሚያገኙ መካከል 50 በመቶ ብቻ ናቸው አንደኛ ደረጃን የሚጨርሱት፡፡ እ.ኤ.አ. በ2017 ዕድሜያቸው ለትምህርት ከደረሰ ታዳጊዎች ውስጥ ዘጠኝ በመቶዎቹ ወይም 64 ሚሊዮን ታዳጊዎች ትምህርት ቤት አልገቡም ተብሎ ነበር፡፡

በዋናነት በትምህርት ዕጦት ወይም መቋረጥ ተጎጂ የሚሆኑት ደግሞ በታዳጊ ወይም በደሃ አገሮች የሚገኙ ታዳጊዎች ናቸው፡፡ በግጭትም ሆነ በጦርነት የትምህርት ዕጦት ሰለባ የሚሆኑ ታዳጊዎች መፃኢ ሕይወት የጠወለገ እንደሚሆን ነው ጥናቶች የሚጠቁሙት፡፡ የትምህርት ዕጦት በትውልዱ ላይ የጤና ዕጦት፣ የገቢ መቀነስና የተስተካከለ የአዕምሮ ሥነ ልቦና ዕጦት የሚያስከትል ነው ይባላል፡፡

አንድ ታዳጊ ከትምህርት ገበታ የሚርቅበት ጊዜ በረዘመ ቁጥር ደግሞ ወደ ተማሪ ቤት የሚመለስበት ዕድል እየጠበበ እንደሚሄድ ነው የሚታመነው፡፡

ዓለም አቀፉ የሕፃናት ፈንድ ሪፖርት እንደሚጠቅሰው እ.ኤ.አ. በ2020 በመላው ዓለም 535 ጥቃቶች በትምህርት ቤቶች ላይ ተፈጽመዋል፡፡ ይህ ቁጥር ደግሞ በ2019 ከነበረው 17 በመቶ ያደገ ነው ይባላል፡፡ በዚህ ሪፖርት ውስጥ ኢትዮጵያም ተጠቅሳለች፡፡ በሴራሊዮን እ.ኤ.አ. ከ1991 እስከ 2002 በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት 14 ሺሕ ታዳጊዎች ከትምህርት ገበታ ተነጥለው ለጦርነት ተማግደው ነበር ተብሏል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ አሁንም ቢሆን እንደ ሶሪያና የመን ባሉ የግጭት ቀጣናዎች ሲደጋገም ይታያል፡፡ በግጭት ቀጣና ያሉ ታዳጊዎች በተለይ ሴቶች ያለ ዕድሜያቸው ለማግባት ከመገደድ ጀምሮ ብዙ ዓይነት ፆታ ተኮር ችግር ይገጥማቸዋል ይባላል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2023 በአማካይ በቀን ከ2.15 ዶላር በታች በሆነ አነስተኛ ገቢ ኑሮን የሚገፉ የዓለም ሕዝቦች ቁጥር 648 ሚሊዮን መሆኑን የሚገልጸው ሪፖርቱ፣ ብዙዎቹ የድህነት አዙሪት (Cycle of Poverty) ውስጥ የወደቁ መሆናቸውን ያትታል፡፡ የድህነት አዙሪትን በአንድ ማኅበረሰብ (አገር) ከሚፈጥሩ ችግሮች ዋናውና ቀዳሚው ደግሞ፣ የትምህርት ዕጦት ወይም መቋረጥ አንዱ መሆኑን ሪፖርቱ ያወሳል፡፡

የድህነት ዓይነቶችን በዑደታቸው ‹‹ኦኬዥናሊ ፑር፣ ሳይክሊካሊ ፑር፣ ዩዡዋሊ ፑርና ኦልወይስ ፑር›› በማለት በአራት መደቦች የመደበው ሪፖርቱ የትምህርት ዕጦትን የዘለዓለም የድህነት ነቀርሳ የሚያስከትል ችግር ሲል ይመድበዋል፡፡

ይህን ጉዳይ የሚስማሙበት በትምህርትና በሕፃናት ዕድገት ላይ የሚሠራው የአማኑኤል የልማት ድርጅት መሥራችና ዋና ዳይሬክተር ተሰማ በቀለ (ዶ/ር)፣ የትምህርት መቆራረጥ ጉዳት ዘርፈ ብዙ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

‹‹ኢዱኬሽን ሎስ ይሉታል የትምህርት መቋረጥን፡፡ ውድ የሆነ የመማሪያ ጊዜ ወይም ዕድሜ የሚያባክን ነው፡፡ ይህ የጊዜ ብክነት በተለያዩ መንገዶች ሊካካስ እንደሚችል አምናለሁ፡፡ ፈጣን የትምህርት አሰጣጥ ፕሮግራሞችን መከተል አንዱ ነው፡፡ ትምህርት ሚኒስቴርም ቢሆን ይህንን በማመን በጦርነቱ ወቅት ካሪኩለም በማዘጋጀት ከአምስተኛ ክፍል በታች ባሉ የትምህርት እርከኖች ውጤታማ ሥራ ሞክሯል፡፡ በዚህ ላይ ተጨማሪ ጥናት ያስፈልጋል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

በግጭትና በጦርነት ተማሪዎች ትምህርት ማቋረጣቸው በአብዛኛው ‹የትምህርት መቋረጥ ችግር› እየተባለ በተማሪዎች አኃዝ ተደግፎ ይቀርባል፡፡ ነገር ግን ይህ የትምህርት መቋረጥ ችግር በትክክል እንዴት የጉዳቱ ሁኔታ ሊለካ የሚችለው የሚል ጥያቄ ለተሰማ (ዶ/ር) ተነስቶላቸው ነበር፡፡

ይህንን በጣም ትልቅ ጥያቄ ሲሉ የጠቀሱት ባለሙያው፣ ‹‹ይህን ያህል ተማሪ ወደ ትምህርት ቤት መሄድ አልቻለም ተብሎ ይቀመጣል፡፡ ግን እሱ ብቻ አይደለም ጉዳቱ፡፡ ኢዱኬሽን ሎስ በኢኮኖሚ ይተመን ከተባለ በአገር ላይም ትልቁ የጂዲፒ (ጥቅል ዓመታዊ ኢኮኖሚያዊ ገቢ) ጉዳት ያመጣል፡፡ በአንድ አገር ውስጥ ላለው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የሚያስፈልግ የተማረ የሰው ኃይል እጥረት የሚያስከትል ነው፡፡ ትምህርት ቢቋረጥም እንኳ አስተማሪዎች ደመወዝ ይከፈላቸዋል፡፡ ተማሪዎች ትምህርት በሚያቋርጡባቸው ጊዜ ሊገጥሟቸው የሚችሉ የሕይወት ተግዳሮቶች ሁሉ ተሰልቶ ነው የትምህርት መቋረጡ ጉዳት በትክክል ሊቀመጥ የሚችለው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ በቅርብ ዓመታት በተደጋጋሚ ጊዜ የትምህርት መቆራረጥ አደጋ እያጋጠመ ነው፡፡ አገሪቱ ባለፉት ዓመታት የገጠማት ተከታታይ ግጭትና የፀጥታ መደፍረስ ችግር የትምህርት ዘርፉን ክፉኛ እንደፈተነው ይነገራል፡፡ ከፖለቲካ ለውጡ ቀደም ብሎ ሲያጋጥሙ የነበሩት ተቃውሞዎች፣ እንዲሁም በክልሎችና በማኅበረሰቦች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶች ቀላል የማይባል የትምህርት መቆራረጥ ማስከተላቸው ይነገራል፡፡

ከፖለቲካ ለውጡ በኋላ እየባሱ የመጡ ግጭቶች መበራከትና በሒደትም ደም አፋሳሽ ጦርነቶች መከሰታቸው የትምህርት መቆራረጥ ችግሩን አባብሰውታል፡፡ እነዚህ ጦርነቶች ደግሞ በሰላም ስምምነቱ ዕልባት አገኙ ቢባልም፣ ነገር ግን አሁንም ቢሆን በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች እየተካሄዱ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በትምህርት ዘርፉ ላይ ሊያደርስ ከሚችለው ጉዳት በላይ በትውልድ ወይም በአገር ላይ ሊያመጣ የሚችለው ጉዳት ከወዲሁ እያሳሰበ ነው፡፡

ሰኔ 5 ቀን 2015 በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ዘ ሉሚኒስ ፈንድ ተቋም ከመቀሌና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ያቀረበው ጥናት፣ ጦርነቱ በክልሉ ተማሪዎች ላይ ያደረሰውን ተፅዕኖ በሰፊው ዘርዝሮታል፡፡ ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ክፍል የደረሱ 600 ታዳጊዎችን የመማር አቅም በመሠረታዊ የሒሳብና የቋንቋ ትምህርት ፈተናዎች የለካው ጥናቱ፣ ጦርነቱ የክልሉ ተማሪዎችን ትምህርት የመቀበል አቅም እንደጎዳው አስቀምጧል፡፡ በዋናነት መቀሌ ከተማ አቅራቢያ በመጠለያ ካምፖች ውስጥ ያሉ ከምዕራብ ትግራይ (ወልቃይት) አካባቢ የተፈናቀሉ ተማሪዎችን የመማር አቅም የመዘነው ይህ ጥናት፣ አምስት በመቶዎቹ ብቻ አጥጋቢ ውጤት ማምጣታቸውን ይገልጻል፡፡ ወደ 35 በመቶዎቹ የማሟያ ውጤት ማምጣታቸውን የሚያክለው ጥናቱ ቀሪዎቹ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት ግን መሠረታዊ የቋንቋና የሒሳብ ፈተናዎች መውደቃቸውን አሳሳቢ ሲል ያስቀምጣል፡፡

ሰባት በመቶ ተማሪዎች በጥይት የመመታት አደጋ እንደገጠማቸው፣ 40 በመቶዎቹ የሞተ ሰው አስከሬን ማየታቸው፣ 29 በመቶዎቹ ሰዎች ሲገደሉ መመልከታቸውን፣ 72 በመቶዎቹ ተኩስ ሲካሄድ በቅርበት መመልከታቸውን/መስማታቸውን፣ 62 በመቶዎቹ በጦርነት እሞታለሁ የሚል ሥጋት እንደተሰማቸው፣ 70 በመቶዎቹ ደግሞ በረሃብ የመሞት ስሜት እንዳደረባቸው መናገራቸውን ይኼው ጥናት ማረጋገጡን ይገልጻል፡፡ የቤተሰባቸው አካል በግጭት ሲሞት የማየት፣ የጥይት ድምፅ በቅርበት የመስማት ብቻ ሳይሆን ማስፈራራት፣ እስራት፣ አስገድዶ መድፈርና ሌላም ችግር ተማሪዎቹ እንደገጠማቸው ጥናቱ በሰፊው ይዘረዝራል፡፡

ከተማሪዎች በተጨማሪ 450 ወላጆችንና 400 መምህራንን ጥናቱ ይፈትሻል፡፡ ጦርነቱ በትግራይ ክልል 2.4 ሚሊዮን ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጪ በማድረግ የትምህርት አቀባበል ችሎታቸውን ከመቀነስ በተጨማሪ፣ በርካታ ሥነ ልቦናዊና ማኅበራዊ ጉዳት አስከትሏል ይላል፡፡

ከጥናቱ ጎን ለጎን ከግጭት ጋር ተያይዞ በትምህርት ዘርፍ ላይ ስለደረሰው ጉዳት የተጠየቁት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ኪሮስ ጉዑሽ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ጉዳቱ ከግጭቱ እንደሚቀድም ነው የገለጹት፡፡

‹‹በትግራይ ለአራት ዓመታት ያህል ትምህርት ቆሟል፡፡ መጀመርያ መጋቢት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. በኮሮና ወረርሽኝ የተነሳ ትምህርት ቆመ፡፡ የኮሮናን ተፅዕኖ በመቋቋም ዳግም ትምህርት ለማስቀጠል ስንዘጋጅ ደግሞ ወደ ጦርነት ገባን፤›› በማለት ችግሩ የተራዘመ ጊዜ ማስቆጠሩን ገልጸዋል፡፡ ኪሮስ (ዶ/ር) እንደገለጹት ጦርነቱ የትምህርት ዘርፍ መሠረታዊ ዓምዶች የሚባሉትን ጎድቷቸዋል፡፡ የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማት ወድሟል፣ የሰው ኃይል ማለትም መምህራንና ተማሪዎች ሞተዋል፣ ቆስለዋል፣ ወይም ተፈናቅለዋል፡፡ በሌላ በኩል በሥርዓተ ትምህርቱ ላይም በቀላሉ የማይጠገን ጉዳት ደርሷል ብለዋል፡፡

ይህንኑ በትግራይ የተካሄደውን የመሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር በላይ ሐጎስ (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፣ ግጭትና ጦርነት ከባድ ተፅዕኖ በትምህርት ላይ እንዳላቸው በርካት የጥናት ውጤቶች ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹በመላ ኢትዮጵያ በተለያዩ ምክንያቶች በኮሮና፣ በድርቅ፣ በጎርፍ፣ በጦርነትና በመሳሰሉ ችግሮች የትምህርት መደነቃቀፍ እያጋጠመ ነው፡፡ ለዚህ ሲባል የትምህርት ሥርዓቱን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ ለሚገጥሙ የትምህርት መስተጓጎል ችግሮች ምላሽ አሰጣጥን ማጠናከር ያስፈልጋል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

ባለሙያው አክለውም፣ ‹‹ኢትዮጵያ በትምህርት መቆራረጥ ችግር አዙሪት ውስጥ ትገኛለች፤›› ብለዋል፡፡ ከ1960ዎቹ ጀምሮ ብዙ ትውልድ በዚህ ችግር መባከኑን አውስተዋል፡፡ ‹‹ከ1966/67 እስከ 1970 ዓ.ም. መምህራን የሌሉበት፣ በአብዛኛው በረሃ የገቡበትና ሥርዓቱ የተረባበሸበት ነበር፡፡ በሶማሊያ ጦርነት፣ በኢሕአፓም ሆነ በድርቅና ረሃብ፣ ችግሮች ብዙ ተማሪዎች ትምህርት ሳያገኙ ሕይወታቸው ሁሉ የተቀጠፈበት ነበር፡፡ ያ ችግር ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ ተመልሶ እንደገና መጣ፡፡ ይህ ራሱን መልሶ የሚደግም የትምህርት ዘርፍ የቀውስ አዙሪት ነው፤›› በማለት በየጊዜው አገሪቱን ያጋጠሙ የትምህርት መስተጓጎሎችን አስረድተዋል፡፡

ትውልዱ ከዚህ አዙሪት መውጣት እንዳለበት የተናገሩት በላይ (ተባባሪ ፕሮፌሰር)፣ ‹‹የሰላም ትምህርት (Peace Education) በካሪኩለም ቀርፆ መስጠትን አስፈላጊ ነው፤›› ብለውታል፡፡

ልክ እንደ ባዮሎጂ ወይም ሒሳብ ትምህርት ሁሉ የሰላም ትምህርትን አስፈላጊ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡ የሞራልና ግብረ ገብ ትምህርት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ለታዳጊዎች ከታች ጀምሮ እንደሚሰጠው ሁሉ የሰላም ትምህርት መስጠት ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ነው ብሎ ከታች ጀምሮ ማስተማርን እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡

‹‹አሁን በአገራችን ያለው መናናቅ፣ መጠላላትና መናቆር እንዳይኖር ከሥር ጀምሮ ዜጎችን በሞራልና በሥነ ምግባር ኮትኩቶ የሚያሳድግ ትምህርት መኖር አለበት፤›› በማለትም ገልጸዋል፡፡

ትምህርት ማለት ክፍል ውስጥ ብቻ ተቀምጦ ሞራል መማር ወይም ሀሁ መቁጠር አለመሆኑን ተናግረው፣ ‹‹በተግባር ሄዶ የተጎዳውን መርዳት፣ የቆሸሸውን ማፅዳት፣ ውጪ ወጥቶ የተለያዩ ድጋፎች ማድረግ፣ ማኅበረሰቡ ውስጥ ገብቶ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት ይጠይቃል፤›› በማለት ይገልጹታል፡፡

ከታች ከቅድመ መደበኛ ትምህርት ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ባሉ ዕርከኖች በተግባር የተደገፈ የሞራል ትምህርት እንደሚያስፈልግ በላይ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ይናገራሉ፡፡

‹‹ትውልዱን መታደግ የሚቻለው የተስተካከለ የትምህርት ሥርዓት በማበጀት ነው፡፡ ትምህርት ሳይስተጓጎል የሚሰጥበትን መንገድ በመዘርጋት ነው፡፡ የትምህርት መቆራረጥ ጉዳት አሁን ላይ ላይታየን ይችላል፡፡ ጉዳቱ ወደፊት በጊዜ ሒደት የሚታይ ነው፡፡ አሁን በዚህ ችግር ያለፉ ተማሪዎች ነገ አድገው የችግር ምንጭ ይሆናሉ፤›› በማለት የችግሩን ዑደት በመጠቆም ሐሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡

ከአንድ ወር ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለመጀመሪያ ጊዜ ባወጣው የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ዓመታዊ ሪፖርት፣ በኢትዮጵያ ትምህርት የማግኘት መብት በከፍተኛ ደረጃ አደጋ ላይ መውደቁን ይፋ አድርጎ ነበር፡፡

በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ ክልሎች ያጋጠመው ጦርነት ትምህርት ቤቶችና የትምህርት ቁሳቁሶች ላይ ከባድ ጉዳት ማስከተሉን ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየደረሱ ካሉ የፀጥታ መደፍረሶች ተጨማሪ ቀውስ እንደፈጠሩ የሚያክለው ሪፖርቱ፣ ድርቅና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎችም የትምህርት ማግኘት ዕድልን እየዘጉ ስለመሆኑ ያትታል፡፡

ሪፖርቱ የአዲስ አበባ ከተማን ችግር ሲያነሳ በተለይ የግል ትምህርት ቤቶች ከ20 እስከ 100 በመቶ በላይ የትምህርት ክፍያ ጭማሪ እናድርግ ማለታቸውን በሥጋትነት ይፈርጃል፡፡ በከተማው 40 በመቶ ለሆኑ ተማሪዎች የትምህርት አገልግሎት የሚሰጡት እነዚህ ተቋማት የዋጋ አጨማመር ትኩረት እንደሚያስፈልገው አሳስቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -