የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከትቂት ወራት በፊት ያወጣው የገንዘብ ፖሊሲ ወደ ትግበራ ገብቷል፡፡ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ዋነኛ ዓላማ ያደረገው ይህ ፖሊሲ፣ የባንኮች የብድር ምጣኔ ካለፈው ዓመት ከ14 በመቶ በላይ እንዳይበልጥ ገደብ የጣለ ነው፡፡
ይህ መመርያ መተግበር ከጀመረ ወዲህ ግን ከጅምሩ አንዳንድ ተፅዕኖዎች መታየት ስለመጀመራቸው ይጠቀሳል፡፡ በተለይ ባንኮች የሚሰጡት ብድር በገንዘብ ፖሊሲው ከተጣለባቸው ገደብ ጋር ለማጣጣም በማሰብ ቀደም ብለው የፈቀዷቸውን ብድሮች ጭምር ከመልቀቅ እንዲቆጠቡ ወይም መሰል አሠራርን እንዲከተሉ እያደረጋቸው ስለመሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከመመርያው መውጣት ቀደም ብለው የተፈቀዱ ብድሮች ሊለቀቅላቸው እንዳልቻለ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የተለያዩ ባለሀብቶችና የንግድ አንቀሳቃሾች ገልጸዋል። በዚህም ምክንያት የተፈቀደላቸውን ብድር ታሳቢ በማድረግ የገቧቸው የቢዝነስ ስምምነቶች እየተፋረሱባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ቤትና ተሽከርካሪ ግዥ ውሎች ሳይቀሩ በእንጥልጥል እንዲቆዩ ማድረጉንም ካነጋገርናቸው ተበዳሪዎች ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
ብድሩ እንዲለቀቅላቸው ማረጋገጫ አግኝተው የነበሩት ተበዳሪዎች፣ አሁን ብድሩን ማግኘት ለምን እንዳልቻሉ ለሚያቀርቡት ጥያቄ የሚያገኙት ምላሽ አዲሱ የገንዘብ ፖሊሲ የጣለው የብድር ዕቀባ መሆኑንም ያስረዳሉ።
አንዳንዶቹም የተፈቀደላቸውን ብድር በትዕግሥት እንዲጠብቁ እንደተነገራቸው ያመለክታሉ፡፡ ቤት ለመግዛት ተዋውለው ከሚገለገሉበት ባንክ የፈቀደላቸውን ብድር እየተጠባበቁ የነበሩ አንድ ተበዳሪ ብድሩ እንደሚያገኙት በተገለጸላቸው ወቅት ሊለቀቅላቸው ባለመቻሉ የቤት ሽያጭ ውላቸው ሊፈርስባቸው እንደሆነ ገልጸዋል። እንዲህ ያለው ችግር በአብዛኛው በግል ባንኮች አካባቢ የሚስተዋል ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የተለያዩ የባንክ የሥራ ኃላፊዎች እንደገለጹትም፣ ሁኔታው ተጠባቂ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ የመመርያው ተፅዕኖ በባንኮች ላይ ብቻ ሳይሆን ብድር ጠያቂዎች ላይም ጫና ማሳደሩ አልቀረም፡፡ በተለይ አነስተኛ ብድር ይሰጣሉ የተባሉ ባንኮች ላይ ጫናው ሊበረታ የሚችል እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
እንደ ባለሙያዎቹ ገለጻ ከሆነ መመርያውን ለመተግበር ባንኮች አዲስ አሠራሮችን መተግበር ያለባቸው በመሆኑ የተፈቀዱ ብድሮች ቢሆኑም ዳግም እንዲታዩ የሚያስገድድ ነው። በተለይ የአንድ የግል ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ በሰጡን ሰፋ ያለ ማብራሪያ፣ ‹‹የብድር ገደብ መመርያው መውጣት በኋላ የተፈቀዱ ብድሮች በቶሎ ላለመለቀቃቸው አንዱ ምክንያት እንደተባለው ከመመርያው ጋር ሊያያዝ የሚችል መሆኑ ነው፡፡ ጉዳዩ እንደየባንኩ ሁኔታ የሚለያይ ቢሆንም፣ የብድር ጥያቄዎች የሚስተናገዱበት መንገድ ቀደም ካለው አሠራር የተለየ ሊሆን ይችላል፡፡ የተፈቀደ ብድርን መከልከል እንኳን ባይቻል ጥያቄው የሚስተናገድበት ጊዜ ሊረዝም እንደሚችል፣ ይህ የሚሆነውም የብድር አፈቃቀዱን ከመመርያ ጋር ለማጣጣም እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡ በእሳቸው እምነት ግን የተፈቀዱ ብድሮች በቶሎ አለመለቀቅም ሆነ አዳዲስ ብድሮችን በቶሎ ለማስተናገድ ባንኮች ተግዳሮት የሆነባቸው የብድር ገደቡ ብቻ ሳይሆን ባንኮች ካለባቸው ወቅታዊ የገንዘብ እጥረት ጋር ያያይዙታል፡፡
ከመመርያው መውጣት በፊት የተፈቀዱ ብድር ከዚህ ጋር ለምን ይያያዛል የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው እኚሁ ከፍተኛ የባንክ ባለሙያ፣ ይህ በባንኮች ውሳኔ ላይ የሚመሠረት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን ብድር የተፈቀደላቸው ተበዳሪዎች በየተራ የሚስተናገዱበት ሁኔታን እንዲከተሉ ስለሚያስገድድ በዚህ መሀል ክፍተት ሊፈጠር እንደሚችልም አስረድተዋል፡፡
ከብድር አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ግን ዋናው ችግር ሊሆን የሚችለው ከዚህም በኋላ ቢሆን ሊፈትናቸው የሚችለው ጉዳይ ባንኮች የሚቀርብላቸውን የብድር ጥያቄ በአዎንታዊ መንገድ ለመመለስ በቂ ገንዘብ ይኖራቸዋል ወይ ነው? ከዓመታዊ ብድራቸው ላይ ትሬዠሪ ቦንድ እንዲገዙ የሚያስገድደው መመርያ ራሱን የቻለ ተፅዕኖ ፈጥሮ የነበረ በመሆኑ፣ በባንኮች ላይ የገንዘብ እጥረት ችግር (ሊኪውዲቲ ችግር) አምጥቷል።
ስለዚህ ከብድር ገደቡ መመርያ በላይ ባንኮች ለሁሉም የቢዝነስ ዘርፍ ሊያበድሩ የሚችሉት በቂ ገንዘብ ስለሌላቸው ነው የሚለውን አመለካከት ያጠነክራሉ፡፡ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ንረቱን ያባባሰው በኢኮኖሚ ውስጥ የተሠራጨው የብድር ምጣኔ ከፍተኛ በመሆኑ የብድር ገደብ መጣሉን ብዙ የማይስማሙበት ባለሙያው፣ ባንኮች በእጃቸው ያለውን ገንዘብ ሳይወዱ በግድ በተመረጡ አትራፊ ላሏቸው ዘርፎች እንዲያበድሩ መገዳዳቸው በራሱ ትልቅ ተፅዕኖ መሆኑንም ይጠቅሳሉ፡፡
በእሳቸው እምነት ከብድር ጋር ለተያያዙ ጥያቄዎች በቶሎ እያስተናገዱ ላለመሆኑ ዋነኛ ምክንያት አድርገው የሚጠቅሱት፣ የገንዘብ እጥረት የተፈጠረው ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች መሆኑን ያመለክታሉ፡፡
አንደኛው ገንዘብ ከንግድ ግል ባንኮች እየወጣ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሄድ እያደረገ መምጣቱ አንድ ምክንያት ነው፡፡ ለምሳሌ ዲጂታል የነዳጅ ግብይት ተግባራዊ ይሁን ሲባል አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ቀድመው ፈቃድ ያገኙት ኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመሆናቸው፣ ይህንን አገልግሎት ለማግኘት ከግል ባንኮች ወደ ንግድ ባንክ የተላለፈው ገንዘብ ተፅዕኖ ነበረው፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ባንኮች የሚቀርብላቸውን የብድር ጥያቄ ደንበኞቻቸው በፈለጉት ልክ ላለማስተናገድ እንዳይችሉ ያደረጋቸውና የገንበዝ እጥረት ሊፈጥር የቻለው ከባንክ ውጪ ያለው ገንዘብ እንደገና እየጨመረ በመምጣቱ ነው፡፡
አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአሁኑ ወቅት ከባንክ ውጪ ያለው ገንዘብ ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ በመሆኑ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ለብድር የሚዘረጉ እጆችን ይሰበስባሉ፡፡
ብሔራዊ ባንክ ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ በ2014 በጀት ዓመት ከባንክ ውጪ ያለ ገንዘብ ከ198 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ገልጾ ነበር፡፡ አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ ኃላፊነቱን በተረከቡ ማግሥት ይህ ከባንክ ውጪ ያለው ገንዘብ ባንኮች ተጨማሪ ቁጠባ ለማሰባሰብ ዕድል የሚሰጥ እንደሆነ ማመላከታቸው ባይዘነጋም፣ የባንክ ባለሙያው ግን በዚህ ሐሳብ እምብዛም አይስማሙም፡፡ በአብዛኛው ከባንክ ውጪ ያለ ገንዘብ ሆን ተብሎ የወጣ በመሆኑ፣ ይህንን በቁጠባ መልክ መልሶ ለማምጣት የባንኮች አቅም የሚፈቅደው አይሆንም፡፡
ስለዚህ ከዚህ ቀደም ከባንክ ውጪ የነበረን ገንዘብ መልሶ ለማሰባሰብ ተችሎ የነበረው የገንዘብ ኖት ለውጡ ከተደረገ በኋላ መሆኑን ያስታወሱት እኚሁ ባለሙያ፣ አሁንም ከባንክ ውጪ ያለው ገንዘብ መጠን እያደገ መምጣቱ ባንኮች የገንዘብ እጥረት እንዲገጥማቸው እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ይህም በመሆኑ ነው አሁን ላይ ‹‹የተፈቀዱ ብድሮች ሁሉ በቶሎ ሊለቀቁልን አልቻሉም›› የሚል አስተያየት የመጣው፡፡ እንደ እሳቸው እምነት ግን ዋናው ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ ከባንክ ውጪ ያለው የገንዘብ መጠን እንደገና እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር የተያዘ ነው ይላሉ፡፡
በእነዚህ በሁለቱ ምክንያቶች ገንዘብ ከባንኮች መውጣትና በግለሰብ እጅ እየተያዘ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ስለዚህ ከባንክ ውጪ ያለው ገንዘብ መጠን እየጨመረ ከመጣ ደግሞ የባንኮች የማበደር አቅምን መፈታተኑ ስለማይቀር አፋጣኝ ዕርምጃ ያስፈልጋዋል፡፡
ከባንክ ውጪ ያለው የገንዘብ መጠን ለመጨመሩ ሌላው ምክንያት ተደርጎ የሚጠቀሰው፣ ግለሰቦችና ኩባንያዎች ከባንክ ውጪ መያዝ የሚገባቸው የገንዘብ መጠንን የሚደነግገው መመርያ በአግባቡ ሊተገበር ባለመቻሉ ነው፡፡
እንዲህ ያለው ጉዳይ በቀጥታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ጣልቃ ገብነት የሚፈልጉ መሆናቸውን ያነጋገርናቸው የባንክ የሥራ ኃላፊዎች ይስማሙበታል፡፡ ምክንያቱም አሁን ከባንክ ውጪ አለ የሚባለው የገንዘብ መጠን ቀላል የሚባል ባለመሆኑ ብሔራዊ ባንክ ከባንክ ውጪ ያለውን ገንዘብ መልሶ ወደ ባንክ የሚሰበስብበትን መንገድ መፈለግ አለበት፡፡ ከዚህ ቀደም የገንዘብ ኖት ሲቀየር ውጭ ያለ ገንዘብን ወደ ባንክ እንዲመጣ ያስቻለ መሆኑንም በማስታወስ አሁንም ተመሳሳይ ዕርምጃ ወይም በሌላ መንገድ ገንዘቡ ወደ ባንክ እንዲመለስ ማድረግ የሚያስፈልግ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የኢኮኖሚ ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ በረሃ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ከባንክ ውጪ የሚወጣ ገንዘብ በእርግጥም ለሕገወጥ ንግድ ሥራ የሚውል ነው፡፡ ጥቁር ገበያውን እንዲስፋፋ የሚያደርግ ነው፡፡ አንዳንዶቹም በባንክ በኩል በሚደረግ ግብይት መንግሥት ከፍተኛ ግብር ይጠይቀናል በሚል ገንዘቡን አውጥተው ንብረት ይገዙበታል፡፡ ስለዚህ ከባንክ ውጪ ያለውን ገንዘብ መልሶ ለመሰብሰብ ብሔራዊ ባንክ በራሱ መንገድ የሚሠራው ሥራ ሊኖር እንደሚችል ያምናል፡፡ በትክክል ምን ያህል ገንዘብ ባንክ ውስጥ እንዳለ፣ ምን ያህሉ ከባንክ ውጪ እንደሆነ ስለማያውቅ፣ ይህንን ቀመር መሠረት አድርጎ ዕርምጃ ሊወስድ ይችላልም ብለዋል፡፡
የባንክ ባለሙያዎቹ በበኩላቸው፣ አለ ላሉት ችግር እንደ መፍትሔ ብለው የተለያዩ ሐሳቦችን ሰንዝረዋል፡፡ በመጀመርያ ለችግሩ መባባስ ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ ከባንክ ውጪ ያለው ገንዘብ መጠን እየጨመረ ለመምጣቱ ብዙ ምክንያቶች ያሉ ሲሆን፣ ለምሳሌ አንዳንዶቹ ግብር ይበዛብናል ብለው የሚያካሂዱት የገንዘብ እንቅስቃሰ ከባንክ ውጪ የሚከናወን መሆኑን በመጠቆም ከቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) ሐሳብ ጋር ይስማማሉ፡፡
በኢትዮጵያ ከፎርማል ቢዝነሱ ይልቅ ኢንፎርማል የሆነ ቢዝነሱ ሰፋ ያለ ከመሆኑ ጋር የተያይዘ የገንዘብ እንቅስቃሴ ከባንክ ውጪ እንዲሆን ያደርጋል ተብሎ ስለሚታመን ይህንንም ከግንዛቤ ያስገባ መፍትሔ ማፈላለግ ጠቃሚ መሆን የባለሙያዎቹ ማብራሪያ ያስረዳል፡፡
ስለዚህ መንግሥት የብር ኖት መለወጥ አንዱ ለመፍትሔው በቀዳሚነት የሚጠቅሱት እነዚህ የባንክ ባለሙያዎች ከዚህ ጎን ለጎን ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጣ ቢሆንም ሌሎች አማራጮችም እንዳሉ ያመለክታሉ፡፡
ከባንክ ውጪ ያለውን ገንዘብ ወደ ባንክ ለመመለስና የገንዘብ እንቅስቃሴን በአግባቡ ለመቆጣጠር ዲጂታል ከረንሲን መዘርጋት አማራጭ ነው፡፡ ለምሳሌ ጋና ዲጂታል ናሽናል ከረንሲ የሚባል አሠራር እየዘረጉ ስለመሆኑ በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡
ይህ አሠራር በተለይ እንደ እኛ ላሉ አገሮች ትልቅ ጠቀሜታ ስላለው ጉዳዩ ተጠንቶ ተግባራዊ ቢሆን ሕጋዊ አሠራርን ለማስፈንና የነበሩ ችግሮችን ይቀርፋል፡፡ እንዲህ ባለው አሠራር መዘርጋቱ ሰዎች ገንዘባቸውን ዲጂታል እንዲይዙ ያስችላል፡፡ የትኛው ገንዘብ የት እንዳለ ይታወቃል፡፡ የተለያዩ በሕጋዊ መንገዶች እንዲካሄዱ መንገድ ይከፍታል፡፡ ለቁጥጥርም ቢሆን አመቺ ስለሚሆን ምንም ያህል ከፍተኛ ወጪ ቢያስወጣ እንዲህ ያለውን አሠራር መሞከሩ ሊጠቅም ይችላል ብለው ይመክራሉ፡፡
ሌለው ሕጋዊ የገንዘብ እንቅስቃሴን ማጠናከርና በአጠቃላይ የብድር አገልግሎትን ለማቀላጠፍ ሁነኛ ሚና አለው ብለው የሚያምኑት ብሔራዊ መታወቂያ ነው፡፡ ብሔራዊ መታወቂያ ብሔራዊ መታወቂያ መኖር ብዙ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን፣ በተለይ የፋይናንስ ዘርፉን በእጅጉ የሚደግፍ ከመሆኑ አንፃር በፍጥነት አለመተግበሩ ትልቅ ተግዳሮት መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ አጠቃላይ የገንዘብ እንቅስቃሴውን በቀላሉ ከየት ወዴት እንደሚተላለፍ ሁሉ ማወቅ ያስችላል፡፡
በአንዳንድ አገሮች የስልክ መስመር ለማግኘት እንኳን ብሔራዊ መታወቂያ ይጠይቃል የሚሉት ባለሙያዎቹ ይህንን ባለማድረጋቸው ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በአገራችን እንደምናየው ብሔራዊ መታወቂያ አተገባበር አዝጋሚ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ የብሔራዊ መታወቂያ አተገባበር አዝጋሚ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ለብሔራዊ መታወቂያ ትግበራ የሚያስፈልገውን መሠረተ ልማት አሟልቶ አስገዳጅ ቢሆን ከገንዘብ እንቅስቃሴ ጋር ያሉትን ችግሮች መፍታት ይቻላል፡፡
ስለዚህ እኔ የሚያሳስበኝ ይላሉ እኚህ የባንክ ባለሙያ በገንዘብ ፖሊሲው የተጣለው የብድር ገደብ አስከተለ የሚባለው ችግር ብቻ ሳይሆን፣ በቀጣይ ብድር ለማቅረብ ባንኮች በቂ ገንዘብ እንዲኖራቸው እንዴት ይቻላል ለሚለው ጥያቄ በአግባቡ ምላሽ መስጠት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የጉዳዩ ዋነኛ ባለቤት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወቅታዊ ጉዳዮችን በመመልከት በጊዜያዊነትም ሆነ ዘላቂ ጠቀሜታ የሚኖረውን የተለያዩ አሠራሮችን እንዲተገብሩ ማድረግ ያስፈልገዋል፡፡ በተለይም በውጭ አለ የሚባልን ገንዘብ ማሰባሰብ በተለያዩ አሠራሮች መተግበር ያስፈልጋል በማለት ጠቁመዋል፡፡
ቆስጠንጢኖስ በበኩላቸው፣ ከባንክ ውጪ ያለን ገንዘብ እያደገ ስለመምጣቱ ምክንያት አንዳንድ ተወሰዱ የሚባሉ ዕርምጃዎችም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ‹‹የእከሌ አካውንት ተዘጋ፣ እንዳይንቀሳቀስ ተደረገ›› ሲባል አስቀማጮች ምን ሊመጣ ነው ብለው ገንዘብ ከባንክ ሊያወጡ ይችላሉ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በካሽ የምታንቀሳቀቅሰው ይህ ብቻ ነው ሲባል ወደ ባንክ ለምን አስገባለሁ በሚልም ከባንክ ውጪ ያለ ገንዘብ እንዲጨምር የሚያደርግ ሲሆን፣ መፍትሔ ሲፈለግም እንዲህ ያሉ ጉዳዮችንም ከግምት ማስገባት እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡ በተረፈ ግን የብድር ገደቡ ያስፈለገው በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን የገንዘብ እንቅስቃሴ ለመገደብና የዋጋ ንረቱን መቆጣጠር ስለሚያስችል እንደሆነ አመላክተዋል፡፡
ባደጉ አገሮች የዋጋ ንረትን የሚቆጣጠሩት የገንዘብ ፍሰቱን ነው፡፡ በኢትዮጵያም ሰው እጅ ላይ ያለው ገንዘብ እየቀነሰ ከሄደ የዋጋ ንረት ሊቆም ይችላል ከሚለው አቅጣጫ ተነስቶ ነው፡፡ የባንኮች የብድር ምጣኔ ዕድገት ከ14 በመቶ መብለጥ የለበትም ያለው ይህ መመርያ፣ ባንኮች የሚሰጡት ብድር ላይ ተፅዕኖ ያሳርፋል፡፡ ተበዳሪዎች ላይ ጫና ያሳድራል፡፡ ለብድሩ መጓተት መመርያው ብቻ ሳይሆን፣ ከባንክ ውጪ ያለ ገንዘብ እየበዛ መጥቷል ከተባለ ግን፣ ብሔራዊ ባንክ በቂ መረጃ ስላለው ይህንን መረጃ ይዞ ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ሊሰጥ ይችላል፡፡ እንደሚሰማውም ገንዘብ በጆንያ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚሄድ ከሆነ፣ ብሔራዊ ባንክ ይህንን ገንዘብ ወደ ባንክ የሚመለስበትን መንገድ መፈለግ አለበት፡፡
የገንዘብ ፖሊሲው መውጣት የዋጋ ንረቱን እየተቆጣጠርን ነው የሚለው ነገር ራሱ አጠያያቂ ነው የሚሉት የባንክ ባለሙያዎቹ በበኩላቸው፣ ወዲያው የዋጋ ንረቱ ወርዷል ተብሎ የተነገረው ነገር ላይም ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ የዋጋ ንረቱን ያመጣው የብድር ምጣኔው በመስፋቱ ብቻ ሳይሆን፣ የሰፕላይ ሳይዱ ችግር እንዲያውም የገዘፈ ነው ይላሉ፡፡
ትልልቅ ፕሮጀክት መሠረተ ልማት፣ ሎጂስቲክስና የነዳጅ መጨመር ለዋጋ ንረቱ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ በየቦታው የተቀመጠው ኬላና የምርት እጥረትና የመሳሰሉት በመሆናቸው፣ አሁን ያለውን የዋጋ ንረት ብድር በመገደብ ብቻ የሚመጣ ባለመሆኑ፣ በባንኮች ላይ ያለውን ጫና ለማቃለል መመርያው መፈተሽና ከባንክ ውጪ ያለውን ገንዘብ ለማሰበሰብ መሥራት ያስፈልጋል ይላሉ፡፡