Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትበእስረኝነት መሰቃየትና ለመፈታት አለመዘጋጀት ይግባባሉ?

በእስረኝነት መሰቃየትና ለመፈታት አለመዘጋጀት ይግባባሉ?

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

‹‹ቤት ልታከራየኝ ካልክ በኋላ በትግርኛ መናገሬን ስትስማ ሐሳብህን የቀየርከው ለምን ነበር?››

‹‹እዚያ ውስጥ መግባት አስፈላጊያችን ነው?››

‹‹ሌላ ጥያቄ መለጠፉን ትተህ እውነቱን ተናገር፡፡››

‹‹ግልጽ አደል፡፡ ሁሉም ሰው ትግርኛ የሚናገርን ሰው ሕወሓት ቢሆንስ ብሎ ይሠጋል፡፡››

‹‹ትግርኛ ስናገር ባትሰማም፣ አማርኛዬ የትግሪኛ ቃና ኖሮት ቢሆንም፣ ወይ ግንባሬና የዓይኔ ቆብ ላይ ሽንትሮች ብታይም ኖሮ ወዲያውኑ የሚከራይ የለም ተይዟል ብለህ ትሸኘኝ ነበር አደል?››

በግንባሩ አዎ አለ እየሳቀ፡፡

‹‹ያን ቀን በስልክ ትግርኛ ሳላወራ አከራይተኸኝ ቢሆንና ውሎ ሲያድር ትግርኛ ተናጋሪ መሆኔን ብታቅውም፣ ይህንን ሰው በምን ሰበብ እናስወጣ እያላችሁ ዘዴ ትፍልጉ ነበር፡፡››

ተንከተከተ፡፡

‹‹እወቅ! እኔም ሆንኩ ሌላ ትግሬ ‹‹ሕወሓት ቢሆንስ?›› ተብለን የምንጠረጠረው ደጋፊ መሆናችን ሳይታወቅ በደፈናው በትግሬነታችን ብቻ ነው፡፡ ለምን ትግሬነታችን የፖለቲካ መጠርጠሪያ ሆነብን? ገዥዎቻችን ትግሬነትን ፖለቲካ ስላደረጉትና በትግሬነት ስለተደራጁ፡፡ የዚህ ሁኔታ ጉዳቱ መንታ ነው፡፡ ባለሽንትር ሆኜ ወይም ትግርኛ እየተናገርኩ ታክሲ ውስጥና ቡና ቤት ስገባ ወይ አውቶብስ መሳፈሪያ ጋ ስቀመጥ ወሬ ቆማጭ እንደምሆን ተሰምቶኝ እንደምሳቀቅ ሁሉ፣ እንደ ልቡ ያወራ የነበረም ሰው እኔን ፈርቶ አፉን ይቆጣጠራል፣ ራሱን ያፍናል፡፡ የትግሬ አዛዥና ናዛዥነት ከአናትህ ባይኖር ኖሮ አንተም ይህ ኮሳሳ ጎረቤትህ ይህን ሁሉ ሲያደርግ አትታገስም ነበር፡፡ መንገድ ስታቋርጥ ፈጣን መኪና ሲጢጥ ቢያደርግብህና ‹‹ቀስ እያልክ አትነዳም!›› ብለህ ብትቆጣ፣ የመኪና ነጂው ቁጣ ከአንተ ብሶ በትግርኛ እየተሳደበ በጥፊ ቢያጋይህ አንተም መንገደኛውም ትንፍሽ የምትሉ አይመስለኝም፡፡ ታርጋ ይዘህ ፖሊስ ጣቢያ እከስሰው ነበር ብትለኝ አላምንህም፤ በዚህ ትከራከራለህ?››

‹‹በፍፁም፡፡››

‹‹ይህ ምን ማለት ነው? በየብሔር የተሰባሰበ አፋኝ ገዥ እንዳሻው ልፈንጭ እንደሚል ሁሉ፣ ገዥነት የሌለው የዚያ ብሔር ሰው (ዱርዬው ጭምር) ገዥነት ያለው አስመስሎ ዕብሪትና በደል ለመሥራት ሰፊ ቀዳዳ አለው ማለት ነው፡፡ የሁለቱም ዕብሪትና በደል የሚያመነጨው ቅሬታና ምሬት ደግሞ ማረፊያው ድፍን ብሔሩ ላይ ነው፡፡ ያን ብሔር ወደ መጥላት ይወስዳል፡፡                       

‹‹የበላይ ገዥዎቻችን አድራጊ ፈጣሪነት በብሔር ላይ ያልተመሠረተ ቢሆን ኖሮስ? በሚናገረው ቋንቋም በግንባር ምልክትም ብሔሬ ከዚህ ነው ቢልህም ልትፈራና ልትጠረጥር የምትችልበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ ለመፍራት ቢያንስ ሰውየው በመንግሥት ላይ ያለውን አቋም ወይም ከመንግሥት ሹሞች ጋር ያለውን ቅርበት ማወቅ ይኖርብሃል፡፡ ያንን እስካላወቅህ ድረስ ሜዳ ለሜዳ ልዳፈርህ ባለ ሰው ላይ ቡፍ ለማለት ትደፍራለህ፡፡ ብሔር ለመጥላትና በብሔር ለመከፋፈል አትጋለጥም፡፡ የእኔ ምክንያት ከዚህ ዓይነት እውነት የሚነሳ ነው፡፡ ይህ ነው የሚባል ልዩነት እንደማላመጣ አቀዋለሁ፡፡ ግን የእኔ ዓይነት ሰዎች ኅብረ ብሔራዊ ፖለቲካ ውስጥ መግባታቸው እየበረከተ ሲሄድ ትግሬ ሁሉ ሕወሓት ነው የሚል ግምት እየተናጋ እንደሚሄድ አልጠራጠርም፡፡ አሁንም ምክንያቴ ትንሽ ሆኖ ነው የሚታይህ?››

ፋሪስ ስሜቱ ተነክቷል፡፡ ቃል ሳይናገር ተነስቶ እጄን ጨብጦ እየወዘወዘው ለሰከንዶች ያህል ቆየ፡፡ ሲቀመጥ ‹‹አመሠግንሃለሁ‹‹ አለ፣ የቢራ ብርጭቆ አጋጨን፡፡

(‹‹ጨለምለምታና ወገግታ ተጋቡና›› ከተሰኘ ያልታተመ ፖለቲካዊ ልብ ወለድ የተቀነጨበ)፡፡

1) በየብሔር የሚያስብና ተሰባስቦ የሚንቀሳቀስ ፖለቲካ ውስጥ የሚኖር ኅብረተሰብ በደፈናው የብሔርተኛ ፖለቲካ እስረኛና ጎስቋላ ከመሆን አያመልጥም፡፡ ጣጣው ሥልጣን ላይ ያለው ገዥ ቡድን/ፓርቲ ከራስ ብሔር የወጣ ነው ወይስ ከሌላ ብሔር ከሚል ነገር ጋር የተያያዘ አይደለም፡፡ የብሔርተኛ ፖለቲካ ባለበት ካቴናውም ጉስቁልናውም አብሮ ይኖራል፡፡ ሕወሓት ቁንጮ በነበረበት የብሔርተኞች ገዥነት ጉስቁልና በብሔር መንጓለልና ማንጓለል ያልደረሰበት አካባቢ አልነበረም፡፡ የትግራይ ሰዎች ራሳቸው ትግራዊ ቡድን የበላይ አዣዥ ናዛዥ በመሆኑ ምክንያት ሁለት ዓይነት ካቴና ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ ገዥነቱ የእኛ ነው በሚል ግንዛቤ የተሟሟቁት የበደል/የአድልኦ ጥቅመኝነት፣ ተቀጢላና አጫፋሪ ወደ መሆን ተስበዋል፡፡ ከዚያ ውጪ የነበሩት ደግሞ ሥርዓቱን ከአናት ይዘውር የነበረው ቡድን በትግራዊነት የተሰባሰበ በመሆኑ ብቻ የገዥው ደጋፊና ወሬ አቀባይ ቢሆኑስ በሚል ፍራቻ ሌላው ኅብረተሰብ አንጓሏቸዋል (የሆዱን ደብቋቸዋል)፡፡ ሕወሓት ተንሸራትቶ የአገር ብተና ወረራ በከፈተ ጊዜም በብዙ አካባቢ ከትግራይ የሆኑ ሰዎች በጥርጣሬ ዓይን ውስጥ የወደቁት፣ የቤት ፍተሻ፣ የንግድ ቤት ፍተሻ የተደረገውና በርከት ያሉ ሰዎች እስር የደረሰባቸው የወረራ እንቅስቃሴው ትግራዊነትን መሠረት ያደረገና የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ውስጥ የነበሩ ሰዎችን እስከ ማሸፈት ድረስ የዘለቀ ስለነበር ነው፡፡ የኦነግ ሸኔ ተኳሾች የፀጥታ ኃይሎች መሳሳትን ወይም ወደ ሌላ ቦታ መንቀሳቀስን እያወቁ ጥቃት ሲያደርሱ የኖሩት ከኅብረተሰቡና ከአስተዳዳሩ ውስጥ መረጃ አቀባይ ስለነበራቸው ነበር፡፡ መንግሥት ከፓርቲና ከአስተዳደር መዋቅር አንስቶ ደህነኛውንና ሠርጎ ገቡን መለየት ትልቅ ራስ ምታቱ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ሸኔዎች ኦሮሞዎችን ያጠቁት የእነሱ ተቃዋሚና የመንግሥት ደጋፊ መሆንን መመዘኛ አድርገው ብቻ አልነበረም፣ ከአማራም የተዛመዱና የተዋለዱ ግን ፖለቲካ ውስጥ የሌሉበት ለጥቃት ተዳርገዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ተሬ ብዙኃን ያለ ኃጢያታቸው ተጠቂ ለመሆን ከመጋለጣቸው አኳያ የብሔር ፖለቲካ እስረኞች ናቸው፡፡

ሸኔዎች ከሕፃናት እስከ አዛውንት አማሮችን ያጠቁት የፖለቲካ አቋም እያዩ ሳይሆን፣ ማኅበረሰባዊ ማንነታቸውን እያሰቡ ነበር፡፡ ከአማሮች ጥቃት ጀርባ ያለው ብሔርተኛ ትርክት ምን እንደሆነም በ‹ሻይ ቡና› ላይ የሰማነው የኦነግ ሰው ነግሮናል፡፡ የኦነጉ ሰው የምኒልክን ‹‹የቅኝ ገዥነት›› ግፍ የዛሬ አማሮች ይክፈሉ አይደለም እየተባለ ያለው፣ ቢልም ልሙጥ ገበሬ አማሮች ከእነ ሕፃናቶቻቸው በምኒልክ ዓይን እየታዩ የሚገደሉበትን እንቆቅልሽ አልፈታልንም፡፡ የብልፅግና ፓርቲ በኢብሔርተኛ ኅብራዊ አስተሳሰብ እጅግም መራመድ ያልቻለው አገሪቱ ውስጥ ብሔርተኛና ጎጠኛ እንቅስቃሴ ገና እንደ ልብ ስለሆነና ፓርቲው ራሱ በብሔር ላይ የተመሠረቱ ቅርንጫፎች ድምር ስለሆነ ነው፡፡ የብሔርተኛ ፖለቲካ አሳሪነት ሰብዕናንና የፖለቲካ አቋምን ምላስና አድራጎት ሁለት ቦታ ፈንክቶ እስከ ማቃረን ይዘልቃል፡፡ ‹‹ብሔርተኛ አይደለንም/ብሔርተኝነት ከኢትዮጵያ መነቀል አለበት›› እያሉ ስለ ‹ሀ› ወይም ስለ ‹ለ› ብሔረሰብ ጥቃት አዘውትረው የሚጮሁ ፓርቲዎችንና ጋዜጠኞችን ጠለቅ ብለን ጩኸታቸውን ስንገልጥም ብዙዎቹን ከውስጥ የሚያንተከትካቸው ብሔርተኝነት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

የለውጥ ድባብ ያመጣውን በፌዴራል አውታራት ውስጥ የኦሮሞዎች ሱታፌን መበራከት በአግባብነት መረዳትና ዕድሉን በተረኛነት አባዜ ሀብት ለማግበስበስ የሚሹለከለኩበትን መልቲዎች መንግሥት እንዲያስተውል ማገዝ/አልፎም እንዲቃለሉ ከመንግሥት ጋር መሥራት አይጣሉም፡፡ የአሁኑን መንግሥት በደፈናው በብሔርተኛ ተረኛነት መፈረጅ ግን ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን ፍረጃ አንግበው ‹‹ተረኝነትን እንቃወማለን›› የሚሉ ሰዎች፣ የራሳቸው ዓይንና አዕምሮም በብሔርተኛነት ፖለቲካ የሚያሠላና የሚብከነከን መሆኑን ነው ሳይታወቃቸው የሚገልጡት፡፡ ‹‹የእናንተም ህሊና የሚያስበው ‹በሚነቅፈው› ብሔርተኝነት ሥውር ሙሽት ውስጥ ሆኖ ነው›› ቢባሉም ለመገንዘብ ይቸግራቸዋል፡፡ ድፍን ቅል ፍረጃቸው ወደ ተረኝነት መዝቀጥን የሚቀሰቅስ (ተረኝነትን የማይታገል) መሆኑማ በየት ገብቷቸው!!! የብሔርተኛ ፖለቲካ እስር፣ ሰዎች ላይ የሚፈጥረው የሰብዕና መፋለስ (ዳይኮቶሚ) ይህንን ያህል ጥልቅ ነው፡፡

ከብሔርተኝነት ነፃ መውጣት የግል ምርጫ ጉዳይ አይደለም፣ ‹‹ብሔርተኛ አይደለሁም/እቃወመዋለሁ›› የማለት ጉዳይ አይደለም፡፡ ‹‹እኔ ብሔርተኝነት አያባዝተኝም፤ ብሔሬ/ጎጤ እያሉ መብስክሰክ በውስጤ የለም፡፡ ከኢትዮጵያዊነትም በላይ አፍሪካዊነት ትርታዬ ነው›› የምንል ሰዎች፣ ‹‹ከየትኛውም ፖለቲካ ሩቅ የሆንን የሙያ ሰዎች ነን›› የምንል ኢትዮጵያውንም በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ እስካለን ድረስ ወይም አካላችን የትም አገር ሆኖ አዕምሮና ልባችን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር እስከሆነ ድረስ፣ ከብሔርተኛ እስረኝነት አናመልጥም፡፡ በብሔር የመቁሰል አደጋ ተከትሎን ይኖራል፡፡ በብሔር ታርጋ የመፈረጅ፣ የመጠላትና የመንጓለል የመጠርጠር ድፍን ዕድል አብሮን ይዞራል (ከዓመት በፊት ወደ ሰሜን አሜሪካ የሄደ ብሔርተኛ ያልሆነ አንድ ዘመድ፣ እዚያ ካገኛቸው የኢትዮጵያ ተወላጆች ጋር የሞካከረው ትውውቅ የግለሰባዊ ባህርይ ትውውቅ አልሆነለትም፡፡ በዚህም በዚያ ብሎ የብሔር ‹‹ታርጋን›› አውቆ በታርጋ መሠረት ሰብዕናን መለካት/ግንኙነትን ማቅረብና ማራቅ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ካየው ይበልጥ እዚያ የሚኮሰኩስ ሆኖ አግኝቶታል)፡፡ በብሔር የምናስብ ሆንንም አልሆንም፣ የበቀልንበትን ብሔር መሠረት ያደረገ ጥቃት ሲመጣ ጥቃቱ እንደ መርፌ ጠቅ ያደርገናል፡፡ ብሔራችንን መቧደኛውና መንቀሳቀሻው ያደረገ ተቃውሞ በመንግሥት ላይ ሲነሳም፣ በድፍኑ አብሮን የቆየው የመጠርጠርና የመሳደድ ዕድል ይከፋፈታል፡፡

የአማራ ሕዝብ ውስጥ ‹‹ግድያ ይብቃን፣ ጥያቄዎቻችን ይመለሱ›› የሚል የፋኖ ተኳሽነት ሲጀማመር አማሮች በደፈናው ጥርጣሬ ውስጥ የወደቁት ፋኖአዊ የድጋፍ አጀቡ እስከ ወጣት ተማሪ/ባጃጅ ነጂና በግ ነጋዴ ድረስ የሰፋ ስለነበር ነው፡፡ ዓውራ መንገድ መዝጋት፣ መንገደኞችን ማገትና መፈተሽ ሁሉ የመጣው መንግሥት አማራዎችን በማሰቃየት ፍላጎት ተጠምዶ ስለነበር አልነበረም፡፡ መንግሥትም ኅብረተሰቡም በሞላ ከብሔርተኝነት እስረኝነት ውጪ አልነበሩም፡፡ በብሔርተኛ ፖለቲካ አዙሪት ውስጥ ለመውደቅ እያንዳንዳችን ብሔርተኛ መሆን አይጠበቅብንም፡፡ መንግሥትም ብሔርተኛ ፖለቲካ የሚያራምድ መሆን አይጠበቅበትም፡፡ በብሔር መሥፈርት ተሰባስበው ብሔርተኝነትን የሚቦተልኩ ቡድኖች እስካሉ ድረስ፣ የዚህ ዓይነት ቡድኖች ጠመንጃ እየተኮሱ ሕዝብን የሚያምሱበት እንቅስቃሴ በውስጣችን እስካለ ድረስ፣ ዜጎችም መንግሥትም በብሔርተኛ አዙሪት ከመጠለፍ አናመልጥም፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ (ብሔርተኛ ያልሆነና ብሔርተኛነት ምን እንደሆነ ያልገባው ጭምር) የብሔርተኝነት እስር ያገኘዋል፡፡ መንግሥትም እያቃረውም ቢሆን የአደጋዎችን ዕድሎች ከብሔር ማንነትጋር አያይዞ ከመጠርጠር ማምለጥ አይቻለውም፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የአማራ ክልል አስተዳደርን እንዲተካ በይፋ በተወሰነበት ጊዜ አካባቢ፣ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ዓይናችን ሥር፣ በግ ነጋዴና አናፂ ድረስ የአፈሳ እስር ተካሂዶ ትምህርት ቤቶች ማጎሪያ የሆኑት፣ የትምህርት ቤቶች የእስረኛ ማጎረያነት ወሬ እየተባዛ በመጣበትና የአስቸኳይ ጊዜ መርማሪ ቦርድ ተቋቁሞ እርግጡን ሊያጣራ በተሰናዳበት ጊዜ፣ የተወሰኑት እስረኞች ተፈትተው ቀሪዎቹ ወደ ሌላ ቦታ የተዛወሩበትን፣ መርማሪው ቦርድም ትምህርት ቤቶችን ተዘዋውሮ ዓይቶ ‹‹እስረኛ የለም›› ሊል የቻለበትን የድብቅብቆሽ ጨዋታ እንድናይ ያደረገንም የሚጫወትብን ብሔርተኝነት ነው፡፡

በብሔርተኝነት አዙሪት ውስጥ እስከኖርን ድረስ በጥቅሉ ሕጋዊ ሆኖ ሕግና ሥርዓት ማስከበር ይፋለስብናል፡፡ በሕጋዊነት ሁሉን ነገር ማድረግ የማያስችሉ ፈተናዎች ይመላለሱብናል፡፡ ብሔርተኛ እንቅስቃሴዎች ልብን ያሸፍታሉ፣ ወደ ጥላቻና ወደ ጠባብ/አድሎኛ ዓላማ ይጎትታሉ፣ አገራዊ ጥቅምንና አገራዊ ኃላፊነትን እስከ መርሳት/እስከ ማጥቃት ድረስ ይወስዳሉ፡፡ ብሔርተኝነት የሠፈርን ጥቅም የአገራዊ አካል አድርጎ የማየት አቅምን ያደክማል፣ አርቆ የሚያይ ዓይንን ይነሳል፡፡ ነባራዊና ዕውናዊ ዕይታን ያደበዝዛል፡፡ ፍትሐዊና ሚዛናዊ አስተሳሰብን ያናጋል፡፡ ከስንት መከራ በኋላ በኢትዮጵያ ሕዝቦች የአርበኝነት ተጋድሎና ደም በቅርቡ የታነፀውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ‹‹የዓብይ ጦር››፣ ‹‹የአንድ ብሔር ጦር››፣ ወዘተ. እያሉ መፈረጅ፣ በስድ ስድብ ማብጠልጠል፣ በብሔረሰቦች ላይ ነውረኛ ስድቦች መልቀቅ ሁሉ የዚህ ዓይነት የህሊና ማጣት ውጤቶች ናቸው፡፡ በብሔርተኝነት እስረኝነትና አማሽነት ውስጥ ፓርቲዎች በዴሞክራሲያዊና ዕውናዊ አስተሳሰብ መጎልበት ይቸግራቸዋል፡፡ አገረ መንግሥታችንም የፈለገውን ያህል ለዴሞክራሲ ለመጣር ቢሻ ዴሞክራሲን ለመገንባት ይቸገራል፣ የብሔርተኛ ካቴና እየጎተተ ያስፎርሸዋል፣ ሐሳቦችንና ድርጊቶችን በብሔር ቧንቧ እያሰማራ ሰዎችን በሐሳባቸውና በድርጊታቸው ብቻ ከመመዘን ያሰናክለዋል፡፡

ነፃነትንና አኩልነትን፣ ሕግን አክብሮ የሚያስተዳድር ሥርዓተ መንግሥት መገንባት ከፈለግን ከብሔርተኝነት አዙሪት መውጣት ግድ ይለናል፡፡ ከብሔርተኝነት ነፃ መውጣት በግል ውሳኔ የሚከናወን አይደለም፡፡ ነፃ መውጣት የምንችለው እንደ ኅብረተሰብ፣ እንደ አገር ነፃ ለመውጣት ከቆረጥን ነው፡፡ የቁርጥ ክንዋኔው በሁለት መንገድ ሊካሄድ ይችላል፡፡ አገራዊ መግባባቱ የሁላችን ያህል ሆኖ ሕገ መንግሥት በማሻሻልና በኢብሔርተኛ ተግባቦት ክፍልፋይ ብሔርተኝነትን የመሸኘት ተግባር ውስጥ መግባት አንድ መንገድ ነው፡፡ ሌላው መንገድ፣ ፖለቲካን በብሔር የማደራጀትን ተግባር በሕግ ከመሻር በፊት፣ አገራዊ መግባባታችን ኢብሔርተኛ በሆነ የአቋም ትመት የብሔርተኛ ፖለቲካ ድጋፍንና የፓርቲ አባልነትን አራቁቶ፣ ብሔርተኛ ፖለቲካን በቀፎው ወደ መቅረት ጠርዝ አድርሶ ሕገ መንግሥት ወደ ማሻሻል በማምራት ማጠናቀቅ ነው፡፡

2) የአገራችንን እውነታና ጉዞ ቢያንስ ከ1983 ዓ.ም. እስካሁን ድረስ በደንብ ገምግመን በየትኛውም መንገድ ለመሄድ የሚያግዙ፣ እንዴትና ምን አድርገን ብሔርተኝነትን ማሰናበት እንደምንችንል የሚያዋዩ ናሙናዎች ፊታችን ተገሽረዋል፡፡

በድሬዳዋ እያየነው ያለው የብሔረሰቦችና የሃይማኖቶች መከባበር መተሳሰብና መተሳሰር ብቸኛ ባይሆንም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ሥፍራዎች ተወዳዳሪ የለውም፡፡ በድሬ ልጅነት መኩራትና መፋቀሩ ያስቀናል፡፡ በድሬዳዋ ውስጥ ከሁሉም የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች የተገኙ ሰዎች በድሬዳዋ ልጅነት አምባር ተቃቅፈዋል፡፡ ኦሮሞነት፣ ሶማሌነት፣ ጉራጌነት፣ አማራነት፣ ወዘተ የድሬዳዋ ልጅነትን አይተረትርም፤ አይበጠብጥም፡፡ አንዱ ሃይማኖት ሌላውን አይተናኮልም፣ አንዱ የብሔረሰብ አባል ሌላውን/አንዱ የሃይማኖት አባል ሌላውን ‹‹የእኔ የራሴ/ወገኔ›› ብሎ ነው የሚያየው፡፡ የአንዱን ቋንቋ ሌላው ይናገረዋል፡፡ ብዙ ቋንቋ ተናጋሪነት የፍቅራቸውና የአንድነት ትንፋሻቸው ነው፡፡ የአንዱን በዓልና ባህል ሌላው ይጋራል፣ ይቋደሳል፡፡ ተቋድሷቸው የአንዱን ፆም እስከ መፆምና የፆም መፍቻ እስከ ማዘጋጀት ሁሉ ይሄዳል፡፡ በዚህ ሁሉ የድሬዳዋ ሰዎች ትቅቅፍ ዘንድ፣ የድሬ ልጅነትና ኢትዮጵያዊነት ‹‹እኩያዊ›› በሚባል ሚዛን የተደናበረ አይደለም፡፡ ለድሬዳዋዎች የድሬ ልጅነት ቤትና ጥላቸው ኢትዮጵያ ነች፡፡ ለድሬዳዋ ልጅነት፣ ኢትዮጵያዊነት ህልውናዬ ሰላሜ ጥንካሬዬ ትልቅነቴ የሚል ግንዛቤ እስትንፋሱ ነው፡፡ በየቀኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙርን በያሉበት ቆመው ማክበራቸው የዚህ መገለጫ ነው፡፡ ይህ ተግባራቸው ለታዳጊዎቻቸው ኢትዮጵያዊ አቀራረፅ የሚሰጠው አርዓያዊ ትሩፋት ኃያል ነው፡፡

ድሬዳዋ እዚህ ላይ የደረሰችው የካድሬ ሰባኪ ክትባት ከትቧት አይደለም፡፡ ድሬዳዋ ድሮም በፍቅር ከተማነት ትታወቅ ነበር፡፡ ዛሬ እየኖረች ያለችበትን አኗኗር ትናንትናም ትኖረው ነበር ሊባል ግን አይችልም፡፡ በአንዱ ሃይማኖት በዓል ላይ ሌላው የአደባባይ አስተናጋጅና አጉራሽ የሚሆንበት ትስስብ አዲስ ነው፡፡ ትስስቡና የአገር ፍቅሩ ከበፊቱ ልቋል፣ ሁሉን አቀፍነቱ ሰፍቷል፣ ጠንክሯል፡፡ ድሬዳዋ እዚህ አዲስ ጥንካሬ ላይ የደረሰችው በብላሽ አይደለም፡፡ በክፍልፋይ ብሔርተኝነት መዛመት ነባር ፍቅሯንና መተሳሰቧን ተነጥቃ፣ በመባላትና በመገዳደል መከራ ጠብሳ፣ ሞት እያሸተቱ ውሎ ማደርን ቀምሳና ይህን ክፉ ልምድ በቃኝ ብላ ለመናቆርና ደም ለመቃባት ያበቃትን ክፍልፋይ ብሔርተኝነት እንቢ ብላ ነው፡፡ ብሔረ ብዙነት የሃይማኖት ብዙነት፣ በዓለ ብዙነት፣ ልሳነ ብዙነት፣ ሁሉ ለሁሉ መሆን፣ አለሁልህ/አለህልኝ መባባል ከመዳብ የማይቆጠር ውድ የሰላም የደኅንነትና የህልውና ሀብቷ መሆኑን ከመከራ ተምራ ነው፡፡ እናም የዛሬው የድሬዎች ፍቅርና ትስስብ ከትናንትና ይበልጥ የነቃ ነው፡፡ ብሔርተኛ ወፈፌነት ግርሻ እንዳይሆንበት የሚጠነቀቅና የሚተጋ ነው፡፡ አሁን ‹ሳተናው› ፓርቲ ነኝ ምንትሴ ነኝ የሚል ቡድን፣ ለሶማሌ ለኦሮሞ ለሐረሪ፣ ወዘተ የቆምኩ ነኝ የሚሉ ቡድን፣ ቡድኖች የድሬዳዋን ሕዝብ ትስስብ ለመበጫጨቅ አቅም የላቸውም፡፡ ድሬዎች ኢትዮጵያን ማዕቀፉ ባደረገ የድሬዳዋ ልጅነት አንድ ላይ መቆም እንደሚበጃቸው ዛሬ ነጋሪ አያስፈልጋቸውም፡፡

ድሬዎች የሚያከብሯት፣ የሚዘምሩላት ኢትዮጵያ ድሬ ላይ በተምኔት የተፈጠረች አይደለችም፡፡ የዘመናት መወራረስና የመስዋዕትነት ቅብብል ውጤት ከመሆንም ባሻገር፣ ትኩስና ሁሉን ያነቃነቀ የአገር መውደድና የአርበኝነት ተጋድሎ የተመመባት፣ በሁሉም ማኅበረሰቦች መስዋዕትነት የፀናች፣ ሁሉም በተመመበት ጥንቅር ፌዴራላዊ የፀጥታና የመከላከያ አውታሯን ያደሰች ኢትዮጵያ ነች፡፡ ይህች ትኩስ መስዋዕትነት የተከፈለላትና ሁሉም ለሁሉ ዘብ ለመቆም የተደራጀባት አገር፣ ድሬዳዎች ብቻ የሚሳሱላት አገር አይደለችም፡፡ ኢትዮጵያ ለድሬዳዋ ብቻ ሳይሆን ለሁላችንም ታስፈልገናለችና እንደ ድሬዎች ልንሳሳላት፣ ልናከብራት ይገባናል፡፡ በሌሎች ቦታዎች የታየው የመከራ ልምድ ድሬዳዋ ካየችው ይበልጥ እንደሆን እንጂ አያንስም፡፡ መከራ ከ30 ዓመታት በላይ መክሮናል፡፡ የመከራ ምክር ያነጠራቸው ዓውራ ምክሮች በየሚዲያውና በየሰው አፍ ይስተጋባሉ፡፡ ‹‹ፖለቲከኞች ወደ ሐሳብና ወደ ውይይት! ወደ ሐሳብ ውድድር! ‹‹የጠመንጃ ትጥቅ ደግሞ ወደ አገረ መንግሥታዊ አውታር!‹‹ እየተባለ ነው፡፡ ይህንን አንኳር ትምህርት በተግባር መቀበል ተስኖን ኢትዮጵያን በባሩድ እያመስን፣ ባለአገር ሆኖ መዝለቅ የሚቻል አይደለም፡፡ ድሬዳዋም ብቻዋን የሰላምና የፍቅር ደሴት ሆና አትዘልቅም፡፡ መተራመስ ተንሰራፍቶ ከቀጠለ፣ ድሬዳዋም መደፍረስ አንድ ቀን አይቀርላትም፡፡ የድሬዳዋ ፍቅርነት ሊፀና የሚችለው የድሬዳዋ ከልምድ መታረም፣ በሌሎች ሥፍራዎች ሲባዛ ነው፡፡ ኢትዮጵያ መጎልበትና መቀጠል የምትችለው የድሬዳዋ ቆሌ በሁሉም ሥፍራ መባዛት ሲችል ነው፡፡

የድሬዳዋ ቆሌ ብቻውን አይደለም፡፡ የድሬዳዋን ቆሌ የምናገኘው ድሬዳዋ ድረስ ሄደን አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ድምር፣ የመከራ ልምድ፣ ድምር ትምህርት አንጥሮልናል፡፡ ይህ ትምህርት በኢትዮጵያ የግጭትና የጉስቁልና አዙሪት ውስጥ ጆሮ ለማግኘት አነሰም በዛ ድምፁን ሲያሰማ ቆይቷል፡፡ በዓብይ አህመድ የመደመር ትውልድ ላይ ነጥረው የተቀመጡት የአዲሲቷ ኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያ ያስተናነፅ መርሆች በዋዛ የሚታዩ አይደሉም፡፡ የአካባቢ ለአካባቢ ትስስርና የተወራረሰ ዝምድና የሰጠንን ብዙ ቋንቋ ተናጋሪነትን፣ ባህለ ብዙነትንና የአንድ አገር ልጅነትን (ወንድማማችነት/ እህትማማችነትን) በውድ ሀብትነት መንከባከብና ማጎልበት እንድንችል፣ ለሰው ልጅ አክብሮት መስጠትን፣ በጎነትን፣ በዕውቀትና በምክንያት መመራትን፣ ስሜተ ሥልጡንነትን፣ ሌላውን ለማመንና ለሌላው ለመታመን መቻልን የመኗኗሪያ እሴቶቻችን (የጋራ ማንነታችን) እንዲሆኑ የሚያስችል ለውጥ እንዲሰምርልን የወጡ ትልሞች ናቸው፡፡

እንደ ድሬ የልሳነ ብዙነት የማኅበረሰባዊና የባህል ብዝኃነት ስብጥር ቅርስ ያላቸው ከተሞች እነዚህን ትልሞች የነዋሪዎቻቸውና የታዳጊዎቻቸው የጋራ ግንዛቤና የተግባር እሴቶች እንዲሆኑ በተጋ እንቅስቃሴ ለየዙሪያ አካባቢዎቻቸው የአርዓያነት ችቦዎች መሆን ይችላሉ፡፡ ይህንን ለማድረግ ብርቱ ፍላጎቱ ካለ ማሳካቱ ከባድ አይደለም፡፡ እነዚህን ትልሞች ለመጨበጥ የሚካሄድ የለውጥ ጥረት በኢትዮጵያ የትምህርት አውታራት ውስጥ መላወስ ጀምሯል፡፡ ከተጠቀሱት ትልሞች ጋር የሚመጋገቡ አዲስ የተግባር ልምምዶች ትንፋሻቸው በዙሪያችን እየተነሰነሰ ይገኛል፡፡ የብሔረሰብ ሠፈርንና የሃይማኖት ሠፈርን ተሻግረው ሰውነትንና የአገር ልጅነትን ዝምድና ብቻ የሚመለከቱ የበጎ ሥራ ተግባሮች (የመንግሥት፣ የተቋማት፣ የግል ባለሀብቶች፣ የወጣቶችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፎ የሚታይባቸው)፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ወጣቶች የሚነቃነቁባቸው አካባቢ ዘለል የክረምት በጎ ሥራ ዘመቻዎች፣ የሕክምና ተቋማት የጀማመሯው ነፃ የጤና ምርመራና ሕክምና የመስጠት ልዩና ብርቅ መርሐ ግብሮች፤ ኢቢኤስ ቴሌቪዥን ምሳሌ የሆነበትና ሌሌችም እየተሳቡ የመጡበት፣ የተቸገሩትን የመርዳትና ከረጂ ጋር የማገናኘት በጎ ሥራ፣ ወዘተ ሁሉ ከላይ ለጠቃቀስናቸው እሴቶች ግንባታ ጡቦች የሚያዋጡ ናቸው፡፡

እነዚህን እሴቶች ‹‹የአለህልኝ የአለሁልህ›› ዝምድና መገንቢያና መተማመኛ የማድረግ ሥራ ከሁሉ በፊት ነፃ ፍላጎትን፣ ቁርጠኝነትንና የተግባር ጥረትን ይጠይቃል፡፡ ጥረቶቹ ከወረት ያለፈ ዕድሜ ለማግኘት በመቻላቸው ነገር ውስጥ የመከራ ምክርና ፀፀት የሚያዋጡት ጉልበት ቀላል አይደለም፡፡

በደቡብ ሕዝቦች ውስጥ የነበሩ አዲሶቹ አካባቢያዊ የራስ በራስ አስተዳደሮች በብዙ ነገሮች የተያያዙ ናቸው፡፡ መጪ ልማታቸው በየሠፈር ከማሰብ ይልቅ በጋራ ማቀድና መንቀሳቀስን የሚጠይቅ ነው፡፡ ብሔርተኛ ሽኩቻ ምን ያህል ሰላም እየነሳ እያፈናቀለና ደም እያፋሰሰ አሳር እንደሚያስቆጥርም በውስጣቸው ዓይተውታል፡፡ ማኅበረሰባዊ ብዙነታቸውንና በውስን የምድር ስፋት ውስጥ ባሉ ድንግል ሀብቶች መከበባቸውን በዕውናዊ ዓይን ያጤነ አዕምሮ፣ ግስጋሴያቸው አብሮ የተመመ የልማት ትጋትን የሚጠይቅ እንጂ በየጎሬዬ ለማለት የማይመች፣ በዚያ መንገድም የማይጨበጥ መሆኑን ለመረዳት አይከብደውም፡፡ ይህንን እውነታ ለማስተዋል መቻል፣ የድሬዳዋን ቆሌ ለመጎናፀፍ ቅርብ ያደርጋል፡፡ አሁን ያሉት አዲስ አስተዳደሮች በዚህ ጎዳና ውስጥ ናቸው? ለቁልፍ ከተሞች ልማት ሥፍራዎች የመረጡበት መሥፈርት ጠባብ ሩጫዎችን ከመሸንገል የራቀ ነበር? ዕውን የጋራ ግስጋሴ ጥቅሞችን ተመርኩዞ የደን፣ የግብርና፣ የማዕድንና የቱሪዝም የኢንዱስትሪ ልማት ምርጥ አካባቢዎችን ለይቶ የእነዚያን አካባቢዎች የተሳሰረ/የተመጋገበ ግስጋሴ፣ የንግድ መስተጋብርና የአስተዳደር ቅልጥፍና ለማቃናት የተመቹ ማዕከላትን የመምረጥ ጉዳይ ነበር? የዓውራ ከተሞች ዕጩነት ላይ ተነስተው የነበሩት ቅሬታዎችስ የጠባብ ፍላጎቶችን ልፊያ ያንፀባረቁ አልነበሩም? የእነዚህ ጥያቄዎች መልሶች አዎንታዊ ከሆነ/ወይም እንቅስቃሴያቸው አዎንታዊ ፈር ውስጥ ከገባ አዲሶቹ ክልሎችም በድሬዳዋ መሰል ቆሌ ውስጥ መጓዝን አውቀውበታል ያሰኛል፡፡

በኅብራዊ ፌዴራላዊ አገረ መንግሥት ውስጥ የአንድ ብሔረሰብ ሰፊ ክምችት ያለበት አካባቢ የፌዴሬሽኑ አባል ሆኖ መገኘት በራሱ፣ ለብሔርተኛነት አመቻችቶ ይሰጣል ማለት አይደለም፡፡ አፋርነቱን በኢትዮጵያዊነት ውስጥ የሚረዳው የአፋር ሕዝብ አንድ አብነት ነው፡፡ የአፋር ተጋድሎ የነፃ አውጪነት እንቅስቃሴን ለኢትዮጵያዊነቱ እስከ መጠቀም ታሪክ ያለው ነው፡፡ ከጊዜ ጊዜ እንደ ወርቅ እየተወለወለና እያበራ የሚመጣ ኢትዮጵያዊ ታሪኩና ገድሉም ገና በአግባቡ አልተጻፈለትም፡፡ ተጋድሎውን፣ የታሪክና የተፈጥሮ ዝንጉርጉር ሀብቱን የሚመጥን ልማትም ገና ብዙ ይቀረዋል፡፡ አዋሽ ወንዝን እንኳ ከጥፋት የታረመ ሥልጡን አገልጋይ የማድረጉ ሥራ ገና በአግባቡ አልተከናወነም፡፡

ሌላው በድንቅ አብነት የሚጠቀስ ሕዝባችን ሶማሌ ነው፡፡ የሶማሌ ሕዝብ በቅርብ ታሪኩ፣ በተለይም በዓብዲ ዒሌ ዘመን ለተፈራረቀበት መከራ የሰጠው ምላሽ ኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝቧን በትክክል ተረድታው እንዳልነበረ የሚጠቁም ነው፡፡ አሁን ያለው ሶማሌ ከጠቀስነው ሲዖላዊ ግፍ የራቀው በአምስት ዓመት ብቻ ነው፡፡ የጊዜው ግፈኛ ገዥያቸው በበላይነት በማን ይዘወር እንደነበርም ለሶማሌ ሕዝብ የተሰወረ አልነበረም፡፡ በጊዜው ኦጋዴን ውስጥ የሚንቀሳቀስ ነፃ አውጪ ቡድን ነበር፡፡ ሶማሌዎች ላይ ይወርድ የነበረው ግፍም ብዙ ጊዜ ከዚህ ቡድን ጋር ጉዳይ አላችሁ ከሚል ሰበብ ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ ያ ሁሉ ግፍም የእኛኑ ተወላጅ መሣሪያ አድርጎ በባዕድ ኃይል የተፈጸመ ብሎ ለመተርጎምና በኢትዮጵያ የተከፋ ቁጣ ማስነሻ ለማድረግ የተመቸ ነበር፡፡ ነባሩን ግፍና የነበረውን የታጠቀ የነፃነት ትግል አንድ ላይ ይዘን መጨረሻ ላይ ዓብዲ ዒሌ አራጆች አሰማርቶ ሶማሌ ባልሆኑ ወገኖች ላይ ያስፈጸመውን ነውር ስንጨምርበት ከዚህ ወዲያማ ምኑን ተኗኗርነው የሚያሰኝ ሆኖ ሊተረጎም ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ሰበዞች ሶማሌን ከኢትዮጵያ ለመቁረጥ ከሞከረ ምክር ቤታዊ ‹‹ውሳኔ›› ጋር ተገናኝተው ሶማሌዎችን ለመነጠል አላማለሏቸውም፡፡ የቀጣይ ሕይወታቸውን ዕጣ ብሩህ ተስፋ በኢትዮጵያ ግቢ ውስጥ ነበር ያስተዋሉት፡፡ ይህም ከግፈኛው ገዥያቸው ጋር ጊዜያዊ እልህ በመጋባት ወይም ከኢትዮጵያ ውጪና ውስጥ የሚኖር የጥቅም ብልጫን ባሠላ ፖለቲካ ተቃሎ የሚብራራ አይደለም፡፡ ግፈኛው አስተዳደር ተወግዶ ሶማሌዎች ያለ ሞግዚት መተዳደር ከጀመሩ ወዲያ ሲሆን የታየውና እየሆነ ያለው፣ ሶማሌ ሕዝብን ስናይ የቆየንበትን አሮጌ መነፅር እንድንጥል ያስገደደ ነበር፡፡

መሣሪያ አንስቶ ከኢትዮጵያ ለመለየት ሲታገል የነበረው ቡድን ከሞላ ጎደል በኢትዮጵያ ግቢ ውስጥ ባለ ፖለቲካ ውስጥ ለመሰማራት ፈቀደ፡፡ የሶማሌ ሕዝብ ስለኢትዮጵያዊነቱ ሞግዚት እንደማይሻ፣ ማንንም ለማሳመን ጎንበስ ቀና የማይልበት የራሱ ታሪካዊና ህልውናዊ ጉዳዩ እንደሆነ፣ ከጊዜ ጊዜ በተግባሩ እያሳየ ይገኛል፡፡ ሶማሌ ያልተሳተፈበት የቅርብ የአርበኝነት ተጋድሎ የቱ ነው? ለኢትዮጵያ ምሥራቃዊ ደቡብ ሕዝባዊ አጥርና መከታ ሆኖ ያለው ማን ነው? ከቅርብ ጊዜ በፊት የመነጠል ትግል በውስጡ የነበረበት የሶማሌ ሕዝብ፣ የልሂቅና የሕዝብ ተሳልቶ ለሰላምና ለልማት መትጋት እንዴት እንደሆነም ለሌሎች እያስተማረን ነው፡፡ ብዙኃን በሆነ ብሔረሰብ ውስጥ ንዑስ ሆኖ መገኘት ወይም አዲስ መጥ መሆን፣ በመብቶች የመንጓለል/ከልዩ ልዩ ዕድሎች የመገፋት ኦቶማቲክ ማረጋገጫ አይደለም፡፡ በቁጥር ማነስንም ሆነ ከሌላ አካባቢ መምጣትን ለጭቆና የሚያውለው የቁጥር ብልጫ ሳይሆን አንጓላይ አስተሳሰብ፣ አንጓላይ የፓርቲ ስብስብና በአድልኦ የሚመራ አስተዳደር ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ለመሆን በመጣጣር ረገድም የሶማሌ አስተዳደር ተወዳጅና ከዓይን የሚገባ ነው፡፡ አስተዳደራዊ አያያዙ የንዑሳንንና የግለሰቦችን የእኩል ዕድል መብቶች በማክበር ረገድ ጥረቱ ጎልብቶ ተቀዳሚ ሥፍራ ይይዛል/ለሌሎችም አስተማሪ ይሆናል ብሎ ለመጠበቅ የሚያስመካ ነው፡፡

አንድ የቅርብ ጊዜ ውይይት ላይ፣ አንድ ሶማሌ አባት የሶማሌ ሕዝብ ታሪክ በአግባቡ ተጽፎ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እንዲካተት ጠይቀው ነበር፡፡ ትክክለኛ ጥያቄ! ትክክልነቱ ለሶማሌ ወገናችን ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎቻችንም አላዋቂ ግንዛቤያችንን አራግፈን ሶማሌ ወገኖቻችንን በአግባቡ እንድናውቅ አስፈላጊያችን ነው፡፡

እስካሁን ያነሳሳናቸው አዎንታዊ ጉዞዎች እየተስፋፉ መሄድ ያለ ጥርጥር የብሔርተኛ ካቴናን መሰባበር፣ ግርሻ በማይኖረው አኳኋን ለማረጋገጥ ድርሻ ያዋጣሉ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...