Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ድሮ ልጅ ሆኜ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ጣቢያ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ላይ ከሚተላለፉ የአገር ውስጥና የውጭ ዜናዎች መካከል፣ የእስራኤልና የፍልስጤም ጉዳይ ከፍተኛውን ሥፍራ ይይዝ ነበር፡፡ በተለይ በዓረቦችና በእስራኤል መካከል የስድስቱ ቀናት ጦርነት በተካሄደበት ጊዜ፣ የዜና ሽፋኑ በጣም ሰፊና በጥልቅ ትንታኔ የታጀበ ስለነበር ቤተሰቦቼ በከፍተኛ ጉጉት ሲከታተሉት አስታውሳለሁ፡፡ እናትና አባቴ ለምን እንደሆነ ባላውቅም ለእስራኤል ከፍተኛ ድጋፍ ሲኖራቸው፣ በተቃራኒው ሁለቱ ታላላቅ ወንድሞቼ (የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ነበሩ) ለፍልስጤማውያን የነበራቸው ድጋፍ ከፍተኛ ነበር፡፡ አባቴ ግን ዘወትር ወንድሞቼን ይነቅፍና ይገስፅ እንደነበረ አይረሳኝም፡፡

በስድስቱ ቀናት ጦርነት እስራኤል የግብፅን አየር ኃይል ምድር ላይ እንዳለ አውድማና ጦር ሠራዊቱን ደምስሳ ሲናይን ስትቆጣጠር የእናትና የአባቴ ደስታ ወደር አልነበረውም፡፡ ብዙዎቹ የዓረብ አገሮች ተሸንፈው ሲሸሹና የግብፅ ፕሬዚዳንት የነበሩት ገማል አብደልናስር፣ በሽንፈታቸው ሳቢያ ሥልጣናቸውን የመልቀቃቸው ዜና ሲሰማ ብዙዎች ኢትዮጵያውያን ደስተኛ መሆናቸው በስፋት ሲስተጋባ አስታውሳለሁ፡፡ ይህንን እውነታ ከጎረቤቶቻችን ስሜትም ተገንዝቤያለሁ፡፡ ወንድሞቼ ግን ከእስራኤላውያንና ከፍልስጤማውያን በላይ በደም የተሳሰረ ወንድማማች ሕዝብ እንደሌለ፣ በእንግሊዝና በአሜሪካ ሴራ ሁለቱ ወንድማማቾች በሰላም እንዳይኖሩ ተደርጎ ፍልስጤማውያን ከገዛ መሬታቸው መነቀላቸውን በምሬት ሲናገሩ እንደነበረም ትዝ ይለኛል፡፡

እኔ ከልጅነቴ እስከ አሁን ጎልማሳነት ዘመኔ ድረስ የእስራኤልና የፍልስጤም ጉዳይ አንድም ቀን ዜና ሳይሆን የቀረበት ጊዜ አልነበረም ማለት እችላለሁ፡፡ በወላጆቼና በታላላቅ ወንድሞቼ መካከል ለምን በዚህ ጉዳይ ልዩነት እንደተፈጠረ መመርመር የጀመርኩት፣ እኔም ወጉ ደርሶኝ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኜ ነበር፡፡ አባትና እናቴ እስራኤል ፈጣሪ የሚወዳትና ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደባት ምርጥ አገር እንደሆነች ሲያስቡ፣ ወንድሞቼ ግን ኢየሱስ ክርስቶስን ከሮማውያን ጋር ተባብረው የሰቀሉት አይሁዶች አሁን ደግሞ ፍልስጤማውያን ወንድምና እህቶቻቸውን እያሰቃዩ እንደሚገድሉ ነበር የሚሞግቱት፡፡ በእንግሊዝና በአሜሪካ ድጋፍ አይሁዶቹ የፍልስጤሞቹን መሬት ቀምተው ከፍተኛ ወንጀል የሚፈጽሙ አረመኔዎች እንደሆኑ በቁጭት ይናገሩ ነበር፡፡

እስራኤላውያን በአምላክ ቁጣ ከአገራቸው ከሺሕ ዓመታት በላይ ተበትነው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ሲሰባሰቡ፣ በኢምፔሪያሊስቶቹ ዕርዳታ የፍልስጤሞችን መሬት ከመቀማት አልፈው እንደ እንስሳ ሲገድሏቸው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሳይቀር እንደ ወንጀል አለመታየቱ በወቅቱ ተማሩ ለሚባሉ ኢትዮጵያውያን የሚዋጥ አልነበረም፡፡ ብዙዎቹ ተራማጅ ምሁራን ለፍልስጤማውያን ከፍተኛ ድጋፍ ሲሰጡ አብዛኞቹ ክርስቲያን አማኞች ደግሞ ለእስራኤላውያን ነበር የሚያግዙት፡፡ ሕዝበ ሙስሊሙ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ድጋፉ ለፍልስጤማውያን ነበር፣ አሁንም ነው፡፡ ይህ በኢትዮጵያ ውስጥ ይንፀባረቅ የነበረ ድጋፍና ተቃውሞ በመላው ዓለም የሚታይ ክስተት እንደሆነ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡

ከእነዚህ ሁሉ ዓመታት በኋላ ሰሞኑን ሐማስ በእስራኤል ላይ ድንገተኛና ያልተጠበቀ ጥቃት ፈጽሞ በርካቶች ሲያልቁ፣ እኔ በማውቃቸው ሰዎች ዘንድ የተፈጠረው ስሜት እንደ ወትሮው ሁሉ የተደበላለቀ ነበር፡፡ አንዱ ወገን የሐማስን ድንገተኛ ጥቃት እንደ አረመኔነት ሲፈርጀው፣ በሌላ በኩል ያለው ጎራ ደግሞ የተከማቸ በደል ውጤት መሆኑን ነበር ያስተጋባው፡፡ ኮሌጅ ለመግባት የሚዘጋጁ ሁለት የዘመድ ልጆችን ስሜታቸውን ስጠይቃቸው፣ የሁለቱን ወገኖች ታሪካዊ ዳራ ያን ያህል ስለማያውቁት ‹ከሚተላለቁ ይልቅ ሰላም ቢያሰፍኑ ይሻላቸዋል› የሚል ሾላ በድፍኑ ምላሽ ነበር የሰጡኝ፡፡ አዲሱ ትውልድ እንኳንስ የዓለምን ፖለቲካ ሊረዳ ቀርቶ፣ የሚማረው ትምህርት አልገባ ብሎት እያገኘ ያለውን አሳዛኝ ውጤት እያየነው ስለሆነ በዚህ ልለፈው፡፡

በቀደም ዕለት ቢሮዬ አጠገብ ንፁህና ፅዱ የሆነች አነስተኛ ኪዮስክ ውስጥ ምርጥ ቁርስና ጁስ የምታዘጋጅ አንዲት ወጣት፣ ከዚህ ቀደም ሊባኖስ ዋና ከተማ በቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ ለአምስት ዓመታት መሥራቷን እየነገረችኝ ነበር፡፡ እኔ አንዳንዴ ጎራ ብዬ ቁርስና ጁስ ከመጠቀም ውጪ ብዙም ስለሕይወቷ ተነጋግረን አናውቅም፡፡ እሷ ቤይሩት የምትሠራበት ቤተሰብ የጀርመኖች እንደሆነ፣ ብዙ ጊዜ የውጭ ዜጎች በእንግድነት እየመጡ ሲነጋገሩ በአለፍ ገደም አንዳንድ ነገሮችን እንደምትሰማና የእስራኤልና የፍልስጤሞች ጉዳይ ሲነሳ እንደሚጨቃጨቁ ነገረችኝ፡፡ የጭቅጭቃቸው ምክንያት እንግሊዞችና አሜሪካኖች ሰላም እንዳይሰፍን ስለሚፈልጉ ብቻ፣ ሁለቱ ወንድማማቾች እየተገዳደሉ እንዲኖሩ እያደረጉ እንደሆነ፣ ምክንያቱ ደግሞ የመካከለኛው ምሥራቅን ለመቆጣጠር እንደሆነ ያወሩ ነበር አለችኝ፡፡

‹‹ለመሆኑ በምን ዓይነት ቋንቋ ሲነጋገሩ የሰማሽው?›› በማለት ጥያቄ ሳቀርብላት ብዙ ጊዜ በእንግሊዝኛ ሲያወሩ ያን ያህል ባይገባትም፣ በዓረብኛ ጭምር የሚነጋገሩ ስላሉ ሁለቱን እየገጣጠመች በተደጋጋሚ ስለምትሰማና ቤት ውስጥ ደግሞ ወጣት ሴቶች ከጓደኞቻቸው ጋር ሲያወሩ መገንዘቧን ነገረችኝ፡፡ ይህች ከሁለተኛ ደረጃ ያልዘለለ ትምህርት የሌላት ወጣት ነጋዴ፣ ‹‹ጋሼ መቼም እኛ አማኝ የምንባል ሕዝብ ነን፡፡ ለተበደለ ማዘንና ፈጣሪ እንዲያግዘው መማፀንም ይገባናል፡፡ በቀደም የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ለጋዛ ሁለት ሚሊዮን ሕዝብ ውኃ፣ ምግብ፣ ኤሌክትሪክና መድኃኒት እንዳይገባ እንደማይደረግና የሚዋጉት ሰብዓዊ ፍጡራን ከሚመስሉ እንስሳት ጋር ነው ሲል ልቤ ነበር የተሰበረው…›› ብላ ሳግ ያዛት፡፡

‹‹ጋሼ ከዚህ በላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል አለ ወይ? አንድ ቀን ጀርመናዊው የእኛ ቤት አባወራ በዓረብኛ እነ ኔታንያሁ ቢችሉ ፍልስጤማውያንን ከምድር ገጽ ቢያጠፉ ደስታቸው ነው፡፡ አሜሪካኖችም የሚከፉ አይመስለኝም ሲል ሰምቼው ነበር፡፡ ይኸው የእውነታውን ምልክት በሚገባ እያሳዩን ነው፡፡ ሐማሶች በንፁኃን እስራኤላውያን ላይ የፈጸሙት ወንጀልም ሊወገዝ ይገባዋል፡፡ የትም ሆነ የትም በንፁኃን ላይ የሚፈጸምን ግፍ ማውገዝ አለብን፡፡ እኛ እንዲህ ሚዛናዊ ስንሆን ነው ፈጣሪ ደስ የሚለው…›› ብላ ዕንባዋ ዓይኖቿ ላይ አቀረረ፡፡

(ዘኪዎስ መሐረነ፣ ከጃክሮስ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...