Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ለአኅጉሩ መሪነት ታጩ

የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ለአኅጉሩ መሪነት ታጩ

ቀን:

የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢያሱ ወሰን ለአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዕጩ ሆነው መቅረባቸው ተገለጸ፡፡

ፌዴሬሽንኑ ለስድስት ዓመታት የመሩት ባለሀብቱ የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ለመምራት ከሚወዳደሩት ዕጩዎች መካከል ከፍተኛ ግምት ማግኘታቸው ተነግሯል፡፡

የኦሞቲክ ቢዝነስ ግሩፕ ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ኢያሱ ኅዳር 8 ቀን 2016 ዓ.ም. በሚከናወነው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ ኢትዮጵያን ወክለው በዕጩነት የቀረቡ ሲሆን ከሞሮኮ፣ ከዑጋንዳ፣ ከካሜሮንና ከናይጄሪያ ዕጩዎች ጋር ይወዳደራሉ፡፡

የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ለአኅጉሩ መሪነት ታጩ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ለአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትነት የሚፎካከሩት አቶ ኢያሱ ወሰን

ኮንፌዴሬሽኑ ጥቅምት 2 ቀን በደርባን (ደቡብ አፍሪካ) ሊያከናውነው የነበረውን መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ወደ ኅዳር 8 ቀን ማስተላለፉን ያስታወቀ ሲሆን፣ የት እንደሚከናወን አልተገለጸም፡፡ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማዘጋጀት ፍላጎት ያላቸው አገሮች ካሉ መጠየቅ እንደሚችሉም አስታውቋል፡፡

በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማስተናገድ ጥያቄ ማቅረቧንና ምላሽ እየተጠባበቀች መሆኗን የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ስንታየው ማሩ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ጠቅላላ ጉባዔውን ብታዘጋጅ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው የሚያነሱት ኃላፊው፣ በተለይ ፕሬዚዳንት ማስመረጥ ከተቻለ የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን መቀመጫ በአዲስ አበባ ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡

ጠቅላላ ጉባዔውን ለማሰናዳት ከቪዛ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከኤምግሬሽንና ከዜግነት አገልግሎት ጋር ውይይት መደረጉ የተጠቀሰ ሲሆን፣ የኮንፌዴሬሽን ምላሽ ግን እየተጠበቀ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ በሆቴልና ቱሪዝም፣ እንዲሁም በተለያዩ የንግድ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው የሚገኙት ባለሀብቱ አቶ ኢያሱ፣ ምርጫውን የማሸነፍ ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው ሲሆን፣ ይህም በዓለም አቀፍ መድረክ ባተረፉት የሥራ ግንኙነት ስፖርቱን ለማሳደግ አቅም ይፈጥራሉ የሚል እምነት ተጥሎባቸዋል፡፡

ከግዙፍ የትጥቁ አምራቾች ጋር ባላቸው ቁርኝነት አማካይነት የስፖንሰርሺፕ ስምምነቶችን ወደ ቦክስ ፌዴሬሽኖች በማምጣት በፋይናንስ እጥረት እየተፈተነ ያለውን ስፖርት ለማሳደግ ዕቅድ እንዳላቸው ተጠቁሟል፡፡

ከዚህም በላይ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽንን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ፌዴሬሽኖች የቦክስ ስፖርትን እንዲያዘምኑና ፕሮፌሽናል መንገድ እንዲከተሉ ለማስቻል የተለያዩ ሥልጠናዎችንና የትምህርት ዕድሎችን ለማመቻቸት ዕቅድ አላቸው፡፡  

ፕሬዚዳንቱ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽንን መምራት ከጀመሩበት ወቅት አንስቶ ፌዴሬሽኑ የነበረበትን የፋይናንስ እጥረት ለመቅረፍ በግል ድርጅታቸው አማካይነት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸው ይነገራል፡፡

‹‹ፌዴሬሽኑ በዓመት ውስጥ ለሚያደርጋቸው ውድድሮች፣ እንዲሁም የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ፕሬዚዳንቱ በግል ድርጅቶቻቸው አማካይነት ድጋፍ ያደርጋሉ፤›› በማለት አቶ ስንታየሁ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በዚህም መሠረት ፌዴሬሽኑ በተለያዩ አኅጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮቸ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ማስቻሉ ተገልጿል፡፡

በቅርቡም ለፓሪስ ኦሊምፒክ ማጣሪያ በሴኔጋል በተደረገ ውድድር ኢትዮጵያ እስከ ፍፃሜ መድረስ የቻለችበት ውድድር እንደ ምሳሌነት ይነሳል፡፡

በአንፃሩ የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን የሚመሩ አመራሮች ከከፍተኛ የገንዘብ ማጭበርበርና ሙስና ጋር ስማቸው ይነሳል፡፡ ይህም አመራሮቹ ስፖርቱን ለማሳደግ ከዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን የሚለቀቁ ገንዘቦችን ለአባል ፌዴሬሽኖች እንደማይለቁና አመራሮቹ ለግል ጥቅም እንደሚያውሉት በተደጋጋሚ ይገለጻል፡፡

ከሙስና ጋር በተያያዘ ስማቸው ሲጠቀሱ ከነበሩት መካከል የዑጋንዳና የካሜሮን ቦክስ ፌዴሬሽኖች ፕሬዚዳንቶች ይገኙበታል፡፡ በተለይ የዑጋንዳው ሞሰሶ መሃንጊ በእስር የተቀጡና ከአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ታግደው እንደነበር ይወሳል፡፡

እነዚህ በሙስናና ሥልጣንን ያላግባብ በመጠቀም የሚተቹት የቀድሞ አመራሮች በዘንድሮው ምርጫም ዕጩ ሆነው መቅረባቸው ተጠቁሟል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...