- የባርሴሎና ኦሊምፒክ የብር ሜዳሊያ ተሸላሚዋ ኤለና ማየር በክብር እንግድነት ትገኛለች
በዘንድሮ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የጎዳና ሩጫ ከተለያዩ አገሮች የተወጣጡ የውጭ አገር ተወዳዳሪዎች እንደሚካፈሉ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አስታውቋል፡፡
የ2016 ዓ.ም. ሶፊማልት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ፣ ዓለም አቀፍ የ10 ኪሎ ሜትር ውድድር ከ10 በላይ አገሮች የሚመጡ ተሳታፊዎች ምዝገባቸውን ማጠናቀቃቸው ተጠቁሟል፡፡

በዓመታዊ ውድድሩ ህንድ፣ ብራዚል፣ ኬንያ፣ ዑጋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ስዊዘርላንድ፣ አውስትራሊያ፣ ስዊድን፣ ኖርዌይ፣ ጀርመን፣ አየርላንድ፣ እንግሊዝና አሜሪካ እንደሚሳተፉ ተገልጿል፡፡
ከተሳታፊዎቹ መካከልም በዕድሜ ትንሹ ተሳታፊ ከአሜሪካ የሚመጣው የ20 ዓመቱ ማይክ ዴሪክ ሲሆን፣ በዕድሜ ትልቁ ተሳታፊ ደግሞ የ72 ዓመቱ ዶን ብራድሊ ከማንችስተር እንግሊዝ የሚመጣ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የጎዳና ሩጫ ሁሉንም ዕድሜ ክልል የሚያሳትፍ እንደሆነና ለዚህም በአብዛኛው አትሌቲክስ ወዳጅ ዘንድ ተመራጭ እንዳደረገው ተጠቁሟል፡፡
ከውጪ ተሳታፊዎች ውስጥ ሁለት የኖርዌይ ተሳታፊዎች ሱዳን ከሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች ሲሆኑ፣ ለመጀመሪያ ጊዜም ከህንድ የሚመጡ ተሳታፊዎች ይኖሩታል፡፡
‹‹ከ10 በላይ አገሮችን ወክለው ለሚመጡት ተሳታፊዎች ኢትዮጵያ ያላትን የሩጫ ባህልና በጎ ጎኑን ለማሳየት ጥሩ አጋጣሚም ነው፤›› በማለት የታላቁ ሩጫ የኦፕሬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ዳግም ተሾመ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ደቡብ አፍሪካዊቷ ታዋቂ የረዥም ርቀት አትሌት ኤለና ሜየር የ2016 ዓ.ም. ሶፊማልት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የክብር እንግዳ መሆኗ ታውቋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1992 በባርሴሎና በተካሄደው ኦሊምፒክ ከደራርቱ ቱሉ ጋር ባደረገችው ትንቅንቅ የምትታወሰው ኤለና፣ በውድድሩ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ ማግኘቷ ይታወሳል፡፡
ኤለና ሜየር በተጨማሪም በ1994 የዓለም ግማሽ ማራቶን ሻምፒዮን የሆነች ሲሆን፣ በተለያዩ ውድድሮች የዓለም ክብረ ወሰን መጨበጥ ችላለች፡፡ አትሌቷ በ1999 ግማሽ ማራቶን 1፡06፡44 የገባችበት የምንጊዜም ፈጣን ሰዓቷ ነው፡፡
የ2016 ሶፊማልት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ 10 ኪሎ ሜትር ኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ‹‹ክትባት ለሁሉም ሕፃናት›› በሚል መርህ ይካሄዳል፡፡