Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሕዝብ ተወካዮች ውክልና የሚሻርበት መመርያ ገዥው ፓርቲ ተቀናቃኞቹን የሚበድልበት እንዳይሆን ተሠግቷል

የሕዝብ ተወካዮች ውክልና የሚሻርበት መመርያ ገዥው ፓርቲ ተቀናቃኞቹን የሚበድልበት እንዳይሆን ተሠግቷል

ቀን:

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፌዴራልና የክልል ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የመረጣቸው ሕዝቦች አመኔታ በሚያጡበት ጊዜ ውክልናቸው የሚሻርበትን ረቂቅ መመርያ፣ ገዥው ፓርቲ ተቀናቃኞቹን ከአባልነት ለማስወገድ የሚጠቀምበት እንዳይሆን ሥጋት እንዳላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሥጋታቸውን ገለጹ፡፡

ቦርዱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በመረጣቸው ሕዝብ አመኔታ በሚያጡበት ጊዜ ስለሚወሰድ ዕርምጃ ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 88/1989 ማስፈጸሚያ የሚሆን ረቂቅ መመርያ አውጥቷል፡፡

ለውይይት የቀረበው ረቂቅ መመርያ በፌዴራል የሕዝብ ተወካዮችና በክልል ምክር ቤቶች መራጩን ሕዝብ እንዲወክሉ በተመረጡ የምክር ቤት አባላት ላይ የሚፈጸም ነው፡፡

የወላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር አባል አቶ ጎበዜ ጎአን በሕዝብ የተመረጡ የፓርላማና የክልል ምክር ቤት አባላትን ለማነቃቃትና ተወካይ የሆኑ የምክር ቤት አባላትን ለማስወገድ መጠቀሚያ እንዳይሆን የተለየ ጠንካራ አሠራር ያስፈልጋል፣ በተጨማሪም በአገሪቱ ያለው ጠንካራ ያልሆነ የዴሞክራሲ ሥርዓት ምክንያት ተመርጦ ሥልጣን የያዘ ኃይል ጉልበትም ገንዘብም በእጁ ያለ በመሆኑ፣ የማይፈልገውን አካል ከምክር ቤት ለማስወጣት መመርያውን ተጠቅሞ ሕግ እንዳይጥስ ምርጫ ቦርድ የተለየ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ተወካዩ አቶ ማሙሸት አማረ በበኩላቸው፣ በዚህ ሕግ አማካይነት አንድ የተቃራኒ ፓርቲ የማይፈልገውን የሕዝብ ተመራጭ ለማውረድ ፊርማ ማሰባሰብ ቢቻልና ችግር ቢፈጥር በምን ይስተካከላል? የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ አክለውም ሐሳባቸውን በምክር ቤቶች ጎላ ብለው የሚናገሩ ተመራጮችን ገዥው ፓርቲ ‹‹አላሠራ ብሎኛል›› በሚል ሴራ እነዚህን ተወካዮች ከአባልነታቸው እንዲሰናበቱ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

ዮሐንስ ተሰማ የተባሉት ሌላኛው ተሳታፊ በሴራና በአላስፈላጊ ሽኩቻ የተነሳ መመርያው ለሌላ ነገር የሚያጋልጥ እንዳይሆን ጥርጣሬ የሚያጭር በመሆኑ ቦርዱ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርግበት አሳስበዋል፡፡

 የወለኔ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ መሐመድ ያሲን በመመርያው አፈጻጸም ላይ ሥጋታቸውን ሲገልጹ በሥልጣን ላይ ያለው አካል እንደ መሣሪያ ተጠቅሞ ተቀናቃኞችን ከምክር ቤት አባልነት ማስወገጃ እንዳያደርጋቸው ቦርዱ ሊወስዳቸው የሚገቡ ሕጋዊ ከለላዎች ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሶሻሊስት ዴሞክራሲ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) አባሏ ራሔል ባፌ (ዶ/ር) በበኩላቸው የሚነሳው የይነሳልኝ ጥያቄ በትክክል የመራጩ ሕዝብ ጥያቄ መሆኑን በምን ማረጋገጥ ይቻላል? የፖለቲካ ግፊት እንዳይሆን በምን ይረጋገጣል ሲሉ ቦርዱን ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ተጠባባቂ ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ፣ በአንድ ተወካይ ላይ የሚመጣ ተፅዕኖ ከገዥውም ይሁን ከተፎካካሪ ፓርቲ የሚመለከቱ ጉዳዮች ቦርዱ በጥብቅ የሚከታተለው ይሆናል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...