የቀበሌና የአካባቢ ምርጫ በኢትዮጵያ ከተካሄደ አሥር ዓመታት የተቆጠረ ቢሆንም፣ ገዥው ፓርቲ ብልፅግና ግን አካባቢያዊና የቀበሌ ምርጫ ለማካሄድ ፍላጎት እንደሌለው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ኅብረት (ኢሰመድህ) ተናገረ፡፡
ገዥው ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አካባቢያዊ ምርጫን የማድረግ ፍላጎታቸው ዝቅተኛ ስለሆነ፣ የክልልና አገራዊ የምርጫ ሁኔታ ጤናማ እንዳይሆን ምክንያት መሆኑን፣ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ መስዑድ ገበየሁ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ኅብረት (ኢሰመድህ) ዋና ዳይሬክተር ይህንን የተናገሩት፣ ዓርብ ጥቅምት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በአካባቢያዊ ምርጫ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ በሚመለከት ያደረገውን የጥናት ግኝት አስመልክቶ በዘሐብ ሆቴል ውይይት በተደረገበት ወቅት ነው፡፡
ለተለያዩ ተቋማቶች ጥናቱ ሲቀርብ ከተነሳው ሐሳብ መካከል ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለአካባቢያዊ ምርጫ የሚሰጡት ትኩረት ዝቅተኛ ከመሆኑ የተነሳ፣ በወረዳም ሆነ በቀበሌ ደረጃ ምክር ቤቶች ላይ ለመወዳደር፣ እንዲሁም ዕጩዎቻቸውን ለማስቀመጥ ሲቀሰቅሱ አይታይም የሚል እንዳለበት ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
በዚህም መሠረት እነዚህ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የነቃ ተሳትፎ ካደረጉና እውነተኛ የሆነ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ካላሠፈኑ አገሪቱ በመልካም አስተዳደር ችግር የምትዋጥ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ የዴሞክራሲ ባህል በአካባቢያዊ ምርጫ የታገዘ ባለመሆኑ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ የሚፈጠሩ ግጭቶችንም ሆነ ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ለመፍታት ውስብስብ እንዳደረገው ጠቁመዋል፡፡
የአካባቢያዊና የቀበሌ ምርጫዎችን ለማዳበር የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ ይህንንም አሠራር ለማስፈን በአሁኑ ወቅት ያለው የሕግ ሥርዓት የሚደግፋቸው መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የመልካም አስተዳደር፣ እንዲሁም ፖለቲካዊ ወለድ ችግሮችን ለመፍታት የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ማኅበረሰቡ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግና የሚኖርበትን ወረዳም ሆነ ቀበሌ ላይ መቀመጫ ያገኘው ተወዳዳሪ ማን እንደሆነ እንዲያውቅ መወትወት እንደሚኖርበት ተናግረዋል፡፡
በወረዳና በቀበሌ ላይ የሚደረጉ ምርጫዎች ቀጥተኛ ዴሞክራሲ የሚታይባቸው ቦታዎች መሆናቸውን፣ እነዚህም ቦታዎች ላይ ያሉትን ችግሮች መፍታት ከተቻለ በዞን፣ በክልልና በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱ ምርጫዎች የተስተካከሉ እንደሚሆኑ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
‹‹በዚህ መሠረት አሁን ያለው የሕግ ማዕቀፍ ምን ያህል አስቻይ ነው? የፖለቲካ ምኅዳሩ ምን ይመስላል?›› የሚለውን ግምገማ በማድረግ ጥናቱ በቀጣይ የሚቀርብ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
እነዚህም ግብዓቶች ተሰብስበው በጥናቱ ላይ ከተካተቱ በኋላ፣ ከሁሉም ክልል የተውጣጡ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶችን ጨምሮ ሌሎች ተቋማቶች የሚገኙበት አገራዊ ኮንፈረንስ የሚካሄድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አካባቢዊና የቀበሌ ምርጫዎች ባለመካሄዳቸው የተነሳ በየወረዳውም ሆነ በየቀበሌው የሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከማኅበረሰሰቡ በኩል ተቀባይነትን እያገኙ አለመሆኑን፣ የድርጅቱ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ በሬሳ አበራ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች፣ መንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት፣ በአካባቢያዊ ምርጫ ላይ አፅንኦት ሰጥተው እንዲሠሩበት ጥናት መደረጉን አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶችንና የመብት ጥሰቶችን ለመቅረፍ አካባቢያዊና የቀበሌ ምርጫዎችን ማከናወን እንደሚያስፈልግ አብረርተዋል፡፡
በተለይ የሕግ መሠረት የሌላቸው ባለሥልጣናት በየቦታው የሚቀመጡ ከሆነ፣ እንዲሁም ማኅበረሰቡ ያልመረጠው ምክር ቤት በየቦታው የሚዋቀርበት አጋጣሚ ከተፈጠረ አላስፈላጊ ግጭቶች በየቦታው ሊከሰት እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ የዴሞክራሲ ልምምድ እንዳይዳብር ምክንያት እንደሚሆን የገለጹት አስተባባሪው፣ ይህንንም ችግር ለመፍታትና ትክክለኛ የሆነ ምርጫ ለማከናወን የአካባቢያዊ ምርጫ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስታውሰዋል፡፡