Monday, December 11, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በ151 ሚሊዮን ብር የተገነባው አቢሲኒያ ሲሚንቶ ፋብሪካ መሸጡ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በ300 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ማስፋፊያ እንደሚደረግለት ተጠቁሟል

ከ18 ዓመታት በፊት እ.ኤ.አ. በ2005 በተከፈለ ካፒታል በ151,000,000 ብር ተገንብቶ የነበረው አቢሲኒያ ሲሚንቶ ፋብሪካ፣ ከሰባት ወራት በፊት ሽርሽር ኢንቨስትመንት ግሩፕ ለሚባል ድርጅት መሸጡና በ300 ሚሊዮን ዶላር የማስፋፊያ ግንባታ ሊካሄድላት መሆኑ ታወቀ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በሱሉልታ ወረዳ ጫንጮ ቡኬ ቀበሌ የሚገኘው አቢሲኒያ ሲሚንቶ ፋብሪካ 8.2 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ቢሆንም፣ በቅርቡ በሚደረገው ማስፋፊያ ተጨማሪ አሥር ሔክታር መሬት ላይ ግንባታው እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡

ሽርሽር ኢንቨስትመንት ግሩፕ መስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም. እንዳስታወቀው የመኪና መገጣጠሚያና የምግብ ማቀነባበሪያን ጨምሮ የሲሚንቶ ፋብሪካ ማስፋፊያ ግንባታ ከሚከናውነው ሲኖሚ ኢንተርናሽናል ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ጋር የግንባታ ስምምነት አድርጓል፡፡

የሲሚንቶ ፋብሪካው ማስፋፊያ በ300 ሚሊዮን ዶላር የሚከናወን መሆኑን፣ የተቀሩት ሁለት ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በአጠቃላይ የአንድ ቢሊዮን ዶላር የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሙን የሽርሽር ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ በረከት ባይሳ ተናግረዋል፡፡

ፋብሪካው የተገዛው ከስድስት ወራት በፊት መሆኑን የገለጹት አቶ በረከት፣ ተጨማሪ ማስፋፊያው ያስፈለገው በዋናነት የማምረት አቅሙን ከፍ ለማድረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

 የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ፋብሪካው በቀን 10,000 ቶን ሲሚንቶ ማምረት የሚያስችል ግንባታ እንደሆነ፣ በቀጣይ ወራት ግንባታ እንደሚጀመርና ማስፋፊያው በሁለት ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል፡፡

ኢንቨስትመንት ግሩፑ ከሲኖማ ኢንተርናሽናል ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ጋር ያላቸው ትስስር በዋናነት ሦስቱን ፕሮጀክቶች የመገንባት ስምምነት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኩባንያው የተመረጠውም ዳንጎቴና ለሚ ሲሚንቶ ፋብሪካዎችን የገነባና በዘርፉ ልምድ ያለው በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን የምግብ ማቀነባበሪያ የመኪና መገጣጠሚያ ፕሮጀክቱ በቢሾፍቱ የሚገነቡ መሆናቸውን፣ ሁለቱም ፕሮጀክቶች የሚሠሩት በዚሁ ኩባንያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት በማዕድን ሚኒስቴር የማዕድን ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ኢዮብ በቀለ (ዶ/ር) የሲሚንቶ ፋብሪካውን ሽርሽር ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከወራት በፊት መግዛቱን አረጋግጠዋል፡፡

ፋብሪካው ከዚህ ቀደም የማምረት አቅሙ ዝቅተኛ መሆኑን የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው፣ ነገር ግን ማስፋፊያ ከተደረገለት የማመረት አቅሙ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

እንደ ኢዮብ (ዶ/ር) ገለጻ፣ ሁሉም የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የሚያመርቱት ተደምሮ ከ14 ሚሊዮን ቶን ያልበለጠ መሆኑን፣ በተለያዩ ችግሮች እያለ እየተመረተ ያለው ከስምንት ሚሊዮን ቶን እንደማይበልጥ ተናግረዋል፡፡

‹‹ሽርሽር ኢንቨስትመንት ግሩፕ ያቀደውን የሲሚንቶ ፋብሪካ ማስፋፊያ የሚያሳካ ከሆነ፣ ሲሚንቶን የማምረት አቅም በብዙ እጥፍ ከፍ እንደሚያደርግ አስረድተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአቢሲኒያ ሲሚንቶ ፋብሪካ 300 ሚሊዮን ብር መሸጡን ሪፖርተር ከምንጮቹ ሰምቷል፡፡

ይሁን እንጂ የሽያጭ ዝውውሩ ሙሉ በሙሉ ይለቅ አይለቅ የሰሙት ነገር እንደሌለ የገለጹት የሪፖርተር ምንጮች፣ ነገር ግን መሸጡን በእርግጠኝነት  ተናግረዋል፡፡

አቢሲኒያ ሲሚንቶ ፋብሪካ ለረዥም ዓመታት ሥራ አቁሞ እንደነበርና ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በማምረት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደነበር ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች