- ከፈተና ይልቅ የትምህርት ሥርዓት ማሻሻያ ላይ ትኩረት እንዲሰጥ ተጠይቋል
የትምህርት ሚኒስቴር ሰሞኑን ይፋ ባደረገው የ12ተኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ከወሰዱ 845 ሺሕ ተማሪዎች መካከል 27 ሺሕ ተማሪዎች ብቻ ማለፋቸውን መናገሩ ቅሬታ አስነሳ፡፡ ሚኒስቴሩ በ2015 የትምህርት ዘመን የ12ተኛ ክፍል ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 3.2 በመቶዎች ብቻ የማለፊያ ነጥብ አምጥተዋል ማለቱ በተለያዩ ወገኖች የተለያየ ቅሬታ እያስነሳ ይገኛል፡፡ ለፈተናው ተማሪዎችን ካቀረቡ 3,106 ትምህርት ቤቶች መካከል 1,328 ትምህርት ቤቶች ብቻ የማለፊያ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ማስመዝገባቸውን ነው ትምህርት ሚኒስቴር የተናገረው፡፡
በሁለት ተከታታይ ዓመታት 1.7 ሚሊዮን ተማሪዎች ለ12ተኛ ክፍል ፈተና መቀመጣቸውን የገለጸው ትምህርት ሚኒስቴር፣ ከእነዚህ መካከል ግን 96.7 በመቶዎቹ ፈተናውን ማለፍ ሳይችሉ ወድቀዋል ብሏል፡፡ በዚሁ ጉዳይ ላይ በማኅበራዊ ትስስር ሚዲያዎችና በሌሎች መንገዶች አስተያየት የሰጡ ወገኖች ትምህርት ሚኒስቴር ሆን ብሎ ፈተናን በማክበድ ተማሪዎችን ለመጣል እየሠራ ስለመሆኑ በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡
ስለዚሁ ጉዳይ የተጠየቁት የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ‹‹ውጤቱ በተማሪዎች ምዘና ሥርዓት ላይ የተደረገው የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ስኬታማ መሆኑን ያሳያል፤›› ብለዋል፡፡ ብርሃኑ (ፕሮፌሰር) አክለውም የከዚህ ቀደሙ የፈተና ሒደት የውሸት እንደነበር ውጤቱ ማረጋገጡን ገልጸዋል፡፡ የፈተና አሰጣጡ ሒደት እንጂ በፈተና አወጣጡ ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ አለመደረጉን የተናገሩት ሚኒስትሩ የፈተና አዘገጃጀትም ሆነ አወጣጡ እስከ ዛሬ ከሚሠራበት የተለየ አለመሆኑን ተከራክረዋል፡፡
ይሁን እንጂ አንዳንድ ወገኖች ትምህርት ሚኒስቴር የሚሰጠውን ምላሽም ሆነ የፈተናውን ውጤት ተቃውመውታል፡፡ በኦሮሞ ፖለቲካዊ ጉዳዮች አስተያየት በመስጠት የሚታወቁት አቶ ግርማ ጉተማ ጉዳዩን ‹በትውልዱ ላይ የተቃጣ ጥቃት› ሲሉ ገልጸውታል፡፡ አቶ ግርማ ‹የ12ተኛ ክፍል ፈተና ውጤት የማይመስል ውጤት› ስለመሆኑ ነው የተናገሩት፡፡ ሌላኛው የብዙ ተማሪዎች በፈተናው መውደቅ ያልተዋጠላቸው አስተያየት ሰጪ በኢኮኖሚና በፖለቲካ ትንታኔዎቻቸው የሚታወቁት አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው ‹በመፃኢ ትውልድ ተስፋ ላይ መርዶ ነጋሪነት ይብቃ› ሲሉ ሂሳቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስነብበዋል፡፡
ስለዚህና የትምህርት ዘርፉ እያጋጠሙት ስላለው ቀውስ ሪፖርተር ያናገራቸው የትምህርት ጥናት ባለሙያ በላይ ሀጎስ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ግን አጠቃላይ የትምህርት ዘርፉ ሊሻሻል እንደሚገባ መክረዋል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተሩ እንደሚናገሩት የትምህርት ሥርዓቱ በራሱ ለተማሪዎች ውጤት መሻሻልና ማደግ ያለው አስተዋጽኦ ሲጀመር ደካማ ነው ይላሉ፡፡
‹‹የትምህርት ሥርዓቱ ሲገመገም ልጆችን የማብቃትና የማሻሻል፣ ክህሎትና ዕውቀት የማስጨበጥ አጠቃላይ ድክመት አለበት፡፡ በዓለም ባንክ የተደረገ ጥናት ለምሳሌ ስምንተኛ ክፍል የደረሱ የኢትዮጵያ ተማሪዎች የሚይዙት/የሚጨብጡት ዕውቀት የአራተኛ ክፍል መሆኑን ዓለም ባንክ ባደረገው ጥናት አረጋግጧል፡፡ ይህ ደግሞ አራት ዓመት ሙሉ ምንም ዕውቀት ሳይጨብጡ ነው ስምንተኛ ክፍል የሚደርሱት እንደማለት ነው፡፡ ስለዚህ አጠቃላይ የትምህርት ሥርዓቱ እንደ ሥርዓት ችግር አለበት፤›› ብለዋል፡፡
የአሁኑ የ 12ተኛ ክፍል ፈተና ውጤት የዚሁ ነፀብራቅ መሆኑን ያነሱት በላይ (ተባባሪ ፕሮፌሰር) ትምህርቱን የሚያስተዳድረው አካልም ሆነ የሚመለከተው ወገን የትምህርት ሥርዓቱን እንዲፈትሽ መክረዋል፡፡ ምሁሩ እንደሚናገሩት ከታች ጀምሮ መሠራት ያለባቸው የቤት ሥራዎች ያልተሠሩ መሆኑን ዕውቅና በመስጠት መምህራንን በማብቃት፣ የትምህርት ቁሳቁስ በማሟላትና የትምህርት አሰጣጡን አስቀድሞ መፈተሸ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
‹‹ፈተና አንድ ነገር ነው ነገር ግን መፈተን ብቻ በቂ አይደለም፡፡ መምህራን መሠልጠን አለባቸው፣ መማርያ መሣሪያዎች መቅረብ አለባቸው፣ ተማሪዎችን ከሥር ከሥር ማገዝና ማብቃት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ ደግሞ ሰፊ ክፍተት እንዳለ እየታየ ነው፤›› በማለት ሐሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡