Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበአማራ ክልል የግሪሳ ወፍ መንጋ በሰብል ላይ ከፍተኛ ውድመት እያደረሰ መሆኑ ተገለጸ

በአማራ ክልል የግሪሳ ወፍ መንጋ በሰብል ላይ ከፍተኛ ውድመት እያደረሰ መሆኑ ተገለጸ

ቀን:

በአማራ ክልል ባሉ አራት ዞኖች የተከሰተውን የግሪሳ ወፍ ለማጥፋት ተጀምሮ የነበረው በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት በመቋረጡ፣ በሰብል ላይ ከፍተኛ ውድመት እየደረሰ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

በሰሜን ሸዋ፣ ደቡብ ወሎና ሰሜን ወሎ እንዲሁም በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ባሉ 12 ወረዳዎች፣ ከነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ የተከሰተውን የግሪሳ ወፍ ለማጥፋት መስከረም 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ተጀምሮ የነበረው የኬሚካል ርጭት ባለው የአውሮፕላን እጥረት ሙሉ ለሙሉ መቋረጡ፣ በደረሱ ሰብሎች ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን የክልሉ ግብርና ቢሮ የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ አግደው ሞላ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በተጠቀሱት አካባቢዎች ግሪሳን ጨምሮ የተለያዩ ድንበር ተሻጋሪ የሰብል ተባዮች ተከስተው እንደነበር ያስታወሱት አቶ አግደው፣ የተምችና የአንበጣ መንጋ በባህላዊ መንገድ ጉዳት ሳያደርስ መከላከል ቢቻልም የግሪሳ ወፍ ግን ከአቅማቸው በላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የወፍ መንጋው ምን ያህል ሔክታር መሬትን እንዳካለለ ማወቅ አይቻልም ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ነገር ግን በ265 ሊትር ኬሚካል 132.5 ሔክታር መሬት ላይ በሚገኝ ሰብል ርጭት ተደርጓል ብለዋል፡፡

በምሥራቅ አማራ በአጠቃላይ በተደረገ ድግግሞሽ ቆጠራ ‹‹ከ56 ሚሊዮን የሚልቅ የግሪሳ ወፍ መኖሩን ለማወቅ ተችሏል፤›› ብለዋል፡፡

እንደ አገር ‹‹ያለችው አንዲት አውሮፕላን በመሆኗ ሁሉንም አካባቢ ለማዳረስ አዳጋች ነው›› ያሉት አቶ አግደው፣ በሌላ የአገሪቱ ክፍል የግሪሳ መንጋ ተከስቷል መባሉን ተከትሎ አውሮፕላኗ በመዛወሯ ርጭቱ ተቋርጧል ብለዋል፡፡

ለሦስት ቀን በሰሜን ሸዋና በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች በአራት የመንጋው ማደሪያዎች ላይ ርጭት የተደረገ ቢሆንም፣ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አልቻለም ያሉት ደግሞ የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ የሆኑት አቶ አበበ ጌታቸው ናቸው፡፡

በዞኑ ባለው 23 የወፍ መንጋ ማደሪያ 33 ሚሊዮን ወፍ መኖሩን ለግብርና ሚኒስቴር ካሳወቁ በኋላ፣ በ45 ሔክታር መሬት ላይ በአውሮፕላን ታግዞ በተደረገ የኬሚካል ርጭት፣ አንድ ሚሊዮን የሚሆን የወፍ መንጋ መወገዱን አቶ አበበ ተናግረዋል፡፡

ከፍተኛ የሆነ የወፍ መንጋ መኖሩ እየታወቀ አውሮፕላኑ ወደ ሌላ አካባቢ መወሰዱ ቅሬታ እንደፈጠረባቸውም አቶ አበበ አክለዋል፡፡

ይህ በመሆነም በተለይም ምንም ዓይነት እርጭት ያልተደረገበት የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የማሽላ ሰብል ሙሉ በሙሉ መውደሙን የገለጹት አቶ አበበ፣ ማሽላው ከጥቅም ውጭ በመሆኑ መንጋው ወደ ስንዴና ጤፍ መዞሩን አብራርተዋል፡፡

የተጀመረው የአውሮፕላን ላይ ርጭት በፍጥነት ካልተመለሰ እንደ ዞንም ሆነ እንደ ክልል በምርት ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱ አይቀርም ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ እየታየ ካለው ድርቅ እንዲሁም የተለያዩ የሰብል ተባዮችና ከፀጥታ ሁኔታ አንፃር በ2015 እና 2016 የመኸር ወቅት 160 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንዴት ሊጠበቅ ይችላል? በማለት ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ዕቅዱ ቀደም ሲል የወጣ የቅድመ ምርት ትንበያ እንጂ ድርቁና የወፍ መንጋው ከተከሰተ በኋላ የተገመተ አይደለም ሲሉ የግብርና ቢሮ የሰብል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አግደው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በክልሉ የሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ችግሮች በተበራከቱበት ሁኔታ ይህን ያህል ምርት ይገኛል ብሎ መተንበይ አስቸጋሪ ነው ሲሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...