በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አስተዳደርና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችን ከአስፈጻሚው አካል ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ቁጥጥር የማስወጣት ተግባር በተያዘው ዓመት እንደሚጀመር ተገለጸ፡፡
ሁሉም የፍርድ ቤት ሠራተኞችንና ክንውኖችን ከአስፈጻሚው አካል ለማውጣት በማለም ላለፉት ጥቂት ዓመታት የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎችን ማሻሻያ ሲከናወን የነበረ ሲሆን፣ የፍርድ ቤት አስተዳደርና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችን ቅጥርና ዝውውር የመሳሰሉ ተግባራትንም ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አስወጥቶ በፍርድ ቤት ብቻ እንዲከናወኑ የሕግ ማዕቀፎች ሲዘጋጁ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
በዚህም መሠረት የአስተዳደር ሠራተኞች መተዳደሪያ ደንብ ከረዥም ጊዜ ዝግጅትና ቆይታ በኋላ፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት መገባደጃ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፅደቁ አይዘነጋም፡፡ በዚህ ዓመትም ደንቡን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጀመር፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምሕረት ገልጸዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ይህንን የገለጹት፣ የ2016 ዓ.ም. የዳኝነት ሥራ ዘመን መጀመርንና የፍርድ ቤቶች ሙሉ ለሙሉ መከፈትን አስመልክቶ በጽሕፈት ቤታቸው ሐሙስ ጥቅምት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡
‹‹በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ መውጣቱን ነው የምንጠባበቀው፣ ታትሞ እንደወጣም ተግባራዊ የማድረግ ሥራ እንጀምራለን፤›› ሲሉ የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ፣ ከተግባራዊነቱ በኋላ ፍርድ ቤቶች የሚገጥማቸው የሰው ኃይል ችግር እንደሚቀረፍ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡
የአስተዳደርና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሥር እንደቆዩ፣ ባለፈው ዓመትም የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ይከተለው በነበረው አሠራር ምክንያት አዳዲስ የሰው ኃይል የመቅጠርና የሠራተኞች ዝውውርን የማካሄድ ዓይነት ተግባራት ተግዳሮቶች ገጥመዋቸው እንደነበረ ነው ፕሬዚዳንቱ ያስረዱት፡፡ ‹‹ሠራተኞቹን የማስተዳደር ሥራ የሚከናወነው በአስፈጻሚው ነው፤›› ብለዋል፡፡
የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ይገጥሟቸው ስለነበሩት ችግሮች ተጠይቀው ማብራሪያ የሰጡት ፕሬዚዳንቱ፣ በርካታ ችግሮች እንደሚገጥሟቸውና አንደኛውና የመጀመሪያው ችግር ከበጀት ጋር የተያያዘ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በ2013 ዓ.ም. በተደረገ ማሻሻያ ፍርድ ቤቱ የበጀት ጥያቄዎቹን የሚያቀርበውና ፈቃድ የሚያገኘው ሙሉ ለሙሉ ከተወካዮች ምክር ቤት መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፣ በዚህም ፍርድ ቤቶች ነፃ ሆነው እንዲሠሩ በጀታቸው ከአስፈጻሚው አካል ውሳኔ ውጪ መደረጉ ይታወሳል፡፡ በቀጣይ መሻሻል ካለባቸው ነገሮች አንደኛው የበጀቱ በቂነት እንደሆነ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡
‹‹በእርግጥ የተጨማሪ በጀት ጥያቄያችን በአግባቡ ምላሽ ያገኛል እንጂ፣ በጀቱ በቂ ባለመሆኑ ብዙ ሥራዎች ይጓተቱ ነበር፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ፍርድ ቤቶች አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች መሥራት የለባቸውም፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ፍርድ ቤቶች መሥራት የሚችሉት ነፃነት ካላቸው ብቻ ነው፡፡ ይህንንም ለማሳካት የራሳቸውን ሠራተኞች በራሳቸው ለማስተዳደር መቻል አለባቸው፤›› ሲሉ ከበጀት በተጨማሪ ሠራተኞችን የማስተዳደር ነፃነትን አስፈላጊነት ገልጸዋል፡፡
ከነሐሴ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ መስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም. የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ዝግ ሆነው መቆየታቸው ይታወሳል፡፡ ሁሉም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶችና ከፍተኛ ኃላፊዎች ሐሙስ ጥቅምት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. የዓመቱን ሥራ መጀመር አስመልክተው በጠቅላይ ፍርድ ቤት የማስጀመርያ መርሐ ግብር አካሂደዋል፡፡
የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቴዎድሮስ በመርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ፍርድ ቤቶች የዳኝነት አገልግሎቱ የተሻለ እንዲሆን መሠረት ሊሆኑ የሚችሉ ተግባራትን እንዳከናወኑ ገልጸዋል፡፡
በጠቅላይ፣ በከፍተኛና በመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች የሚገኙ ዳኞች በ2015 ዓ.ም. ከቀረቡላቸው 213,116 መዛግብት ውስጥ ለ184,467 መዛግብት ዕልባት መስጠታቸው ተገልጿል፡፡