የጀርመን መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት አማካይነት ለሚከናወነው የሰላም ግንባታ የሚውል 600 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጓን አስታወቀች፡፡
በአማራ፣ በትግራይና በአፋር ክልሎች ለሰላም ግንባታ ሒደት ይውላል የተባለውን የገንዘብ ድጋፍ በኢትዮጵያ የተመድ ልማት ድርጅት ተወካይ ቱርሃን ሳሌህና በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፋን ኡር፣ ጥቅምት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በጀርመን ኤምባሲ ቅጥር ግቢ ተፈራርመዋል፡፡
የተመድ የልማት ድርጅት በሦስቱ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 13 ወረዳዎች በጦርነት ለተጎዱ 1.2 ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የገለጹት ተወካዩ፣ የጀርመን መንግሥት የድጋፍ መጠኑን በእጥፍ ያስድገዋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአንድ በኩል በዘላቂ ዕድገትና በሰላም ግንባታ ሥራ ላይ መሆኗን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሥር የሰደደ የሰላም ዕጦትና ቀውስ ውስጥ እንደምትገኝ የተናገሩት የተመድ ተወካዩ፣ የሰላም ሁኔታው እንዲስተካከል ከተፈለገ ጦርነት ውስጥ የነበሩ ዜጎችን ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለሱ ማድረግ፣ የፈረሱ የአካባቢ መንግሥታዊ መዋቅሮች ወደ ሥራ እንዲገቡ ማገዝ፣ እንዲሁም የመሠረተ ልማት አቅርቦቱ እንዲስተካከል ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት ተወካዩ አክለው፣ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች አሁንም የሰላም ግንባታ ሥራው መቀጠሉንና ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የተላከ ቡድን መኖሩን ጠቅሰው፣ ‹‹ቡድኑ ሲመለስ በሥፍራቸው ያለውን መረጃ ይፋ እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን የገለጹት የተመድ ልማት ድርጅት ተወካይ፣ የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ማኅበረሰቡ ለመቀላቀል ሥራ በመጪዎቹ አራትና አምስት ዓመታት ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
በዚህ ሥራ ዋነኛው ጥያቄ የሰላም ሁኔታው ይመለሳል ወይ የሚለው ነው ያሉት ተወካዩ፣ ለኢትዮጵያ የሚደረገው ድጋፍ በሌሎች የዓለም ክፍሎችም የሚፈለግ በመሆኑ፣ ለጋሾች በእርግጥም ሰላም ይመለሳል የሚል ማረጋገጫ ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡ ‹‹በመሆኑም ከለጋሽ ድርጅቶች የሚገኘው ገንዘብ የኢትዮጵያ መንግሥት በተገቢው ቦታ መዋሉን በእርግጥ መናገር መቻል አለብን፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ አሁንም ጥያቄው ይቀጥላል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ዘላቂ ሰላም በመፍጠር አገሪቱ የምትፈልገውን የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት፣ ድጋፍ ከሚጠብቁ አገሮች ጋር በጥንካሬ መወዳደር መቻል አለባት ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፋን ኡር በበኩላቸው፣ የጀርመን መንግሥት በኢትዮጵያ ለሚታዩ ግጭቶችና አለመግባባት ውይይት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ የሰላምና የፀጥታ ሁኔታ ሊሟላ የሚችለው፣ የተረጋጋችና አንድ የሆነች ኢትዮጵያ ስትኖር ነው ብለዋል፡፡
ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት የሁሉንም ፍላጎት በሚያሟላ መንገድ ወደ ጠረጴዛ መጥተው ሊነጋገሩ እንደሚገባ አሳስበው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ግጭቶች እየተከሰቱ በመሆናቸው እዚህ ያለው ሰላም በአጭሩ ካልተመለሰ በረዥም ጊዜ በዚህ ሁኔታ መቆየት የማይቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
‹‹ለዚህም ይረዳ ዘንድ የጀርመን መንግሥት የሰላሙ ሁኔታ እንዲስተካከል ይፈልጋል፡፡ የምናደርገው ድጋፍ እያንዳንዱ ሳንቲም ለሚፈለገው ዓላማ መዋሉን ማወቅ እንፈልጋለን፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ይሁን እንጂ አጠንክሬ መናገር የምፈልግው ነገ በጦርነት የሚፈርስ ድልድይ ለመገንባት ገንዘብ መጠየቅ ከባድ ነው፡፡ ስለሆነም ሥራው ተሠርቶ ማየት እንፈልጋለን፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከረዥም ጊዜ በፊት ወደ ነበረችበት የሰላም ምድርነት እንድትመለስ የጀርመንም ሆነ የአውሮፓ ኅብረት ስትራቴጂካዊ ፍላጎት መሆኑን አምባሳደሩ አክለዋል፡፡