Wednesday, December 6, 2023

የእስራኤልና የሐማስ ጦርነት ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖው

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

እ.ኤ.አ. 1947 የመካከለኛው ምሥራቅ ይገባኛል ጭቅጭቅን ለመዳኘት የዓለም አገሮች ድምፅ እንዲሰጡበት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ውሳኔ ቁጥር 181 ወይም ‹‹ፓርትሽን ፕላን›› የተባለውን የውሳኔ ሐሳብ ለጠቅላላ ጉባዔ አቀረበ፡፡ ይህ የውሳኔ ሐሳብ በ33 በአገሮች ድጋፍ፣ በ13 አገሮች ተቃውሞና በአሥር አገሮች ድምፀ ተዓቅቦ መፅደቁ ይነገራል፡፡ ይህ የውሳኔ ሐሳብ እስራኤል የተባለች አገር በመካከለኛው ምሥራቅ እንድትወለድ መሠረት መጣሉ ይነገራል፡፡

በጊዜው ኢትዮጵያ ድምፀ ተዓቅቦ ካደረጉ ጥቂት አገሮች አንዷ ነበረች፡፡ ቻይናና ሶቭየት ኅብረትን ጨምሮ ከእነ አሜሪካ ጎን ሆነው በመካከለኛው ምሥራቅ የሁለት አገሮች መመሥረት ዕቅድን ድጋፍ ሲሰጡ፣ ኢትዮጵያ ግን ድምፀ ተዓቅቦ በማድረግ ነበር ሚዛናዊ አቋም ለመያዝ ጥረት ያደገችው ተብሎ በታሪክ ይወሳል፡፡

ይህን የውሳኔ ሐሳብ ተከትሎ እስራኤል የዛሬ 75 ዓመታት እ.ኤ.አ. 1948 ተመሠረተች፡፡ ወዲያው ግን የዓረብ አገሮች ተባብረው ጦርነት ከፈቱባት፡፡ ጦርነቱ ከሁለቱም ወገን 15 ሺሕ ሰዎች ተገደሉ፡፡ ከ750 ሺሕ በላይ ፍልስጤማዊያንን አፈናቀለ፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ ጦርነቱ አካባቢውን እስራኤል፣ ዌስት ባንክና ጋዛ በማለት ለሦስት ቦታ እንደከፋፈለው ይነገራል፡፡ ዛሬ ድረስ የቀጠለውና በየጊዜው የሚያገረሸው የእስራኤልና የፍልስጤም ግጭት በዚህ መንገድ ነው እያደገ የመጣው፡፡

ጋብ ብሎ የማያውቀው የመካከለኛው ምሥራቅ ውጥረት በየጊዜው ወደ ግጭት ባደገ ቁጥር ደግሞ፣ ዓለም አቀፋዊ ቀውስ ይዞ መምጣቱ የተለመደ ይመስላል፡፡ እ.ኤ.አ. የ1956 የስዊዝ ቦይ ቀውስ የዚህ ውጤት ነው፡፡ በ1967 የስድስቱ ቀናት ጦርነት፣ እንዲሁም በ1973 የዮም ኪፖር ወይም የኦክቶበር ጦርነት ወቅት ዓለም ተያያዥ ቀውሶችን አስተናግዳለች፡፡

የመካከለኛው ምሥራቅ እሳት ለመላው ዓለም የሚተርፍ ነው እስኪባል ድረስ፣ የእስራኤሎችና የፍልስጤሞች ወይም የዓረቦች ግጭት በየጊዜው ባገረሸ ቁጥር ሌሎች አገሮች መፈተናቸው የተለመደ ነው፡፡

በክስተታዊነቱና በከባድነቱ እ.ኤ.አ. ከ1973 የዓረብ እስራኤል ጦርነት ጋር እየተነፃፀረ ያለው ቅዳሜ መስከረም 26 ቀን 2015 ዓ.ም. ሐማስ የከፈተው ድንገተኛ የሮኬት ጥቃት፣ በመካከለኛው ምሥራቅ አዲስ ዙር አደገኛ ጦርነት ቀስቅሷል፡፡ ይህ ጦርነት ደግሞ በዙሪያው ያሉ አገሮችን አልፎ በኢትዮጵያና በሌሎች አገሮች ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድር በመሠጋት ላይ ነው፡፡

በአዲሱ የእስራኤልና የሐማስ ጦርነት መዘዝ የዓለም ነዳጅ ዋጋ ስለመጨመሩ እየተነገረ ይገኛል፡፡ ብሬንት የተሰኘው የነዳጅ ገበያ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ 3.44 በመቶ ጭማሪ በማሳየት ወደ 87.49 ዶላር በበርሜል ዋጋው ማሻቀቡ ነው የተነገረው፡፡ በአዲሱ የሐማስና የእስራኤል ጦርነት መዘዝ የበርካታ አገሮች አየር መንገዶች በረራ ስለማቋረጣቸው እየተነገረ ነው፡፡

እስከ ማክሰኞ መስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ድረስ አዲሱ ጦርነት ከእስራኤል ወገን ከ900 በላይ ሰዎች፣ እንዲሁም ከፍልስጤም ወገን ከ500 በላይ ሰዎችን ሰለባ ማድረጉ ታውቋል፡፡ ከእስራኤል ወገን 2,200 ሰዎች፣ እንዲሁም ከፍልስጤም 2,751 ሰዎች መቁሰላቸውም ተረጋግጧል፡፡ ግጭቱ ትኩስ ሆኖ እስከቀጠለ ድረስ ሰለባ የሚያደርጋቸው ሰዎች ቁጥርም በየሰዓቱ እየጨመረ እንደሚሄድ ነው የሚገመተው፡፡

የእስራኤልና የፍልስጤም ግጭት ሁሌም አጃቢ አጥቶ እንደማያውቅ ይነገራል፡፡ ሁለቱ ወገኖች በተጋጩ ቁጥር አንዱን ደግፎ ሌላውን በተቃራኒው መቃወም በዓለም የተለመደ ነው፡፡ ለምሳሌ በሊባኖስ የሸመቀው ሒዝቡላ የተባለው ታጣቂ ቡድን ሐማስን በመደገፍ በእስራኤል ግዛቶች ላይ ተኩስ መክፈቱ እየተዘገበ ነው፡፡ የኢራን መንግሥት ከፍልስጤም ጎን እንደሚቆም አቋሙን የገለጸ ሲሆን፣ በኢራን ፓርላማ አባላት ይኼው ድጋፍ ሲንፀባረቅ ነው የታየው፡፡

በሌላ በኩል ምዕራባዊያኑ ከእስራኤል ጎን እንደሚሠለፉ በተለያዩ መንገዶች አቋማቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ አሜሪካ ይህን በመግለጫ ብቻ ሳይሆን በተግባር ለማሳየት ጭምር ጥረት ጀምራለች ተብሏል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ስለሚገኘው ጦርነት ለማብራራት ማክሰኞ ዕለት መግለጫ የሰጠው በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ፣ በእስራኤል ላይ ሽብርተኞች ያላቸው ኃይሎች ጦርነት ማወጃቸውን ዓለም እንዲገነዘበው እንደሚፈልግ ተናግሯል፡፡ ኤምባሲው አዲስ አበባ በሚገኘው ጽሕፈት ቤቱ በሰጠው በዚሁ መግለጫ በሐማስ ጥቃት ደረሰ ያለውን ውድመት ብቻ ሳይሆን፣ እስራኤል ራሷን ለመከላከል እየወሰደች ስላለው ዕርምጃና ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ኅብረትም ሆነ የዓለም ማኅበረሰብ ሊገነዘቧቸው ስለሚገቡ ጉዳዮች በሰፊው ለማብራራት ሞክሯል፡፡

የእስራኤል ኤምባሲ ቆንስል የሆኑትና በጥቃቱ ወቅት በእስራኤል ቴልአቪቭ አቅራቢያ የነበሩት ያሪቭ ሶሜክ፣ በእንቅልፍ ላይ እንዳሉ በድንገት ጥቃቱ መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡

‹‹በሳይረን ጩኸት ነው የነቃነው፡፡ በአካባቢያችን ምን እየተካሄደ እንዳለ ለመገንዘብ እንኳ ሰዓታት ወስዶብናል፡፡ በሚዲያ የሚነገረውን በቅጡ ለመረዳትም ሆነ የተከፈተብንን ጦርነት ለማወቅ ጊዜ አስፈልጎናል፡፡ ከባድ ጭፍጨፋና ዕልቂት ነው የተካሄደብን፡፡ የሽብርተኞቹ ጥቃት አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ ሕዝቡ አሁንም ቢሆን ከዚህ ጭንቀትና ሥጋት ገና አልተላቀቀም፤›› በማለት የተናገሩት ቆንስሉ፣ እሳቸው ወደ ኢትዮጵያ እስከተመለሱበት ሰኞ ዕለት ድረስ አሰቃቂ ጥቃት በእስራኤል ላይ ስለመድረሱ አብራርተዋል፡፡

በጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡትና የእስራኤልን መንግሥት አቋም ግልጽ ያደረጉት በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ፣ በርካታ አገሮች ከእስራኤል ጎን መቆማቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹ጦርነቱ እንዴትና ለምን ሆነ የሚለው በእኛ በኩል የሚታይ ይሆናል፡፡ ከ46 የአፍሪካ አገሮች ጋር ግንኙነት አለን፡፡ ለሚሰማን ሁሉ የኢትዮጵያ መንግሥትን ጨምሮ ከእስራኤል ጎን እንዲቆሙ ጥሪ እናቀርባለን፤›› ብለዋል፡፡

አለልኝ (አምባሳደር) ሪፖርተር ላነሳቸው በዚህ ጦርነት ኢትዮ አይሁዳዊያን (ቤተ እስራኤላውያን) በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ለሚለው ጥያቄም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

‹‹ቤተ እስራኤላውያን ከሌላው የእስራኤል ማኅበረሰብ አንለይም፡፡ ለአገራችን አብረን እንሠራለን፣ ከሌላው እኩል መስዋዕትነትም እንከፍላለን፡፡ በጦርነቱ የሞቱ፣ የቆሰሉ፣ ታፍነው የተወሰዱ አሉ፡፡ ከእስራኤል ኅብረተሰብ የተለየን አይደለንም፤›› በማለት ነበር የገለጹት፡፡

‹‹ለሚሰማንም ሆነ ለመንግሥትም ጥሪ እናቀርባለን፤›› ያሉት አለልኝ (አምባሳደር)፣ የአሸባሪዎች ያሉትን ይህን ጥቃት ሁሉም ወገን ከእስራኤል ጎን ቆሞ እንዲያወግዘው ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡

የእስራኤል ኤምባሲ ምክትል አምባሳደር ቶመር በር-ላቪ በበኩላቸው፣ የጥቃቱን ሒደትና ያስከተለውን ውጤት በሐማስ የተቀነባበረ ነው ባሉት ቪዲዮ አስደግፈው አቅርበዋል፡፡

‹‹የእስራኤል ዜጎች በሮኬት እሩምታ ነው ከእንቅልፋቸው ሳይነቁ በበዓል ቀን የተጨፈጨፉት፤›› ያሉት ምክትል አምባሳደሩ፣ የሐማስ ኃይሎች የእስራኤል ከተሞችን መውረራቸውንና የእስራኤል ፀጥታ ኃይሎች 90 በመቶውን መልሰው እንዳፀዱት አብራርተዋል፡፡

እስራኤል የአሸባሪዎች ጥቃት እንደተፈጸመባትና ከዚህ ጨካኝ ጥቃትም ራሷን መከላከል እንዳለባት የጠቀሱት ምክትል አምባሳደሩ፣ እስራኤል በአላቅሳ መስጊድ በቅርቡ የወሰደችውን ዕርምጃ ለመበቀል ነው ሐማስ ጦርነት ያወጀው የሚለውን ጉዳይ አስተባብለዋል፡፡

‹‹አላቅሳ መስጊድ ውስጥ ገብታ እስራኤል ገደለች፣ መፀለይ ከለከለች የሚሉ ስሞታዎች የሚቀርቡት የሽብርተኞቹን ጥቃት ለማለባበስ ነው፡፡ ሐማስ እስራኤልን ለማውደም የሚሠራ ድርጅት ነው፡፡ ይህንን ቡድን በመደገፍና በማስታጠቅ ደግሞ እንደ ኢራን ያሉ አገሮች ተሠልፈዋል፡፡ ሒዝቡላ እኮ ጦርነቱን ከወዲሁ ተቀላቅሎ ጥቃት ከፍቶብናል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በቅርብ ዓመታት የተለያዩ የዓረብ አገሮች ከእስራኤል ጋር ግንኙነት የማሻሻል ዕርምጃዎች ስለመውሰዳቸው በመጥቀስ፣ የአሁኑ ጦርነት ይህን መሻሻል ሊቀለብሰው አይችልም ወይ የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸውም ነበር፡፡

‹‹ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ከባህሬንና ከሱዳን ጋር ግንኙነት የማሻሻል ዕርምጃ ተወስዷል፡፡ ከሳዑዲ ጋር ጭምር ንግግሮች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ የአሁኑ ጦርነት ይህን በዓረብ አገሮችና በእስራኤል መካከል የተፈጠረ የግንኙነት መሻሻል ሒደት እንደማያበላሸው ተስፋ አለን፤›› ሲሉ ነው ምክትል አምባሳደር የመለሱት፡፡

ኢየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ ስለመሆኗ ያወሱት አለልኝ (አምባሳደር) በበኩላቸው፣ ጦርነቱ እስከ የት ድረስ እንደሚቀጥል እንደማይታወቅ ገልጸዋል፡፡ እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር ለብዙ ሺሕ ዓመታት የሚቆጠር ግንኙነት ያላት አገር ስለመሆኗ ያወሱት አምባሳደሩ፣ አሁንም ቢሆን ይህ ግንኙነት በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በንግድና በቴክኖሎጂ ትብብሮች በጥሩ መንገድ ተጠናክሮ ስለመቀጠሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹ጦርነቱ ወዴት እንደሚያመራ ባይታወቅም፣ እስራኤል ግን ራሷንና ሕዝቧን የመጠበቅ ግዴታ ስላለባት ለሚመጣው ሁሉ ተዘጋጅታለች፤›› በማለት ነው አምባሳደሩ መግለጫውን ያሳረጉት፡፡

የእስራኤልና የሐማስ ሰሞነኛ ውጊያ የዓለምን ትኩረት ሙሉ ለሙሉ የሳበ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ከኮሮና ወረርሽኝ ገና ሳያገግም በዩክሬንና በሩሲያ ጦርነት መቀስቀስ እየተፈተነ ያለው የዓለም ማኅበረሰብ፣ አሁን ደግሞ በአስራኤልና በሐማስ ጦርነት ከባድ ሥጋት ላይ የወደቀ ይመስላል፡፡

ሐማስ ‹‹ዘመቻ የአላቅሳ ማዕበል›› በሚል ቅዳሜ ዕለት የከፈተው ጥቃት፣ በእስራኤል ‹‹ዘመቻ የብረት ሠይፍ›› የሚል ፈጣን የአፀፋ ዘመቻ ምላሽ ተሰጥቶታል፡፡ አሁን 2.3 ሚሊዮን ሕዝብ ይኖርበታል የሚባለው የጋዛ ሰርጥና ዙሪያውን ያሉ የእስራኤል ከተሞች የጦር አውድማ ሆነዋል፡፡ ሐማስ ሮኬት ሲተኩስ እስራኤል ደግሞ በምላሹ የአየር ድብደባ እያደረገች ነው፡፡

ገለልተኛ ናቸው የሚባሉ እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የአፍሪካ ኅብረት ያሉ ተቋማት ጉዳዩ እጅግ ያሳሰባቸው መሆኑን እየገለጹ ነው፡፡ ከተለያዩ አቅጣጫዎች እስራኤልም ሆነች ሐማስ ግጭቱን እንዲያበርዱ ጥያቄው በርትቷል፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ ያለችው ነገር ባይኖርም፣ በርካታ የዓለም አገሮች ግጭቱ መባባሱ ለዓለም ፀጥታ አሥጊ እንደሆነ በማሳሰብ ላይ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -