በመካከለኛው ምሥራቅ በእስራኤልና ጋዛ (ሀማስ) መካከል የተቀሰቀሰው አዲስ ጦርነት በዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ ላይ መፍጠር የጀመረው የዋጋ ጭማሪ ተጠናክሮ የሚቀጥል ከሆነ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣው የነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ የበለጠ ሰማይ ሊነካ ይችላል የሚል ሥጋት ፈጥሯል።
ከጦርነቱ መቀስቀስ በፊትም ቢሆን የዓለም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ እያሳየ ነው። ለዓብነትም ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ሁለት ጊዜ ጭማሪ የታየበት ሲሆን በእስራኤልና ጋዛ ታጣቂ ቡድን ሀማስ መካከል ካለፈው ቅዳሜ ዕለት አንስቶ የተቀሰቀሰው ከፍተኛ ጦርነት በዓለም የነዳጅ ዋጋ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖውን ከወዲሁ ማሳደር ጀምሯል። በዚህ ጦርነት ምክንያት መታየት የጀመረው ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ተባብሶ የሚቀጥል ከሆነ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የነዳጅ ሀብት የሌላቸው አገሮች ፍዳ ሊያይል እንደሚችል ተሠግቷል።
ይህ ሁኔታ የሚከሰት ከሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት አሁን ተግባራዊ እያደረገ የሚገኘውን የዓለም የነዳጅ ዋጋን ወደ ማኅበረሱቡ የማስተላለፍ ሒደት ቆም ብሎ ማጤን እንደሚገባው ባለሙያዎች ማሳሰብ ጀምረዋል።
መንግሥት በቅርቡ ባደረጋቸው ሁለት የነዳጅ ችርቻሮ ዋጋ ማስተካከያዎች አዲስ አበባ ላይ የአንድ ሊትር የቤንዚን ዋጋ ወደ 77.65 ብር እየተሸጠ ሲሆን፣ የአንድ ሊትር ናፍጣ ዋጋም በሁለት ጊዜ በተደረገው ጭማሪ ወደ 79.75 ብር ከፍ ብሏል፡፡
መንግሥት ይህንን ጭማሪ ያደረገው ባልተጠበቀ ሁኔታ የነዳጅ ዋጋ በመጨመሩ እንደሆነና እየተሸጠበት ያለውም ዋጋ የጭማሪውን 50 በመቶውን በመሸፈኑ ነው፡፡ መንግሥት ከመስከረም 18 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ያደረገውን አዲስ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ይፋ ባደረገበት ወቅት እንዳስታወቀው የዓለም የነዳጅ ዋጋ ከሰኔ ወር መጨረሻ ጀምሮ ጭማሪዎች እያሳየ በመምጣቱ ከነሐሴ መጨረሻ ጀምሮ ከፊል ነዋጋ ማሻሻያ ማደረጉን ጠቅሷል፡፡ አያይዞም አሁንም የዓለም ገበያው ላይ የሚስተዋለው ጭማሪ በመቀጠሉ የችርቻሮ ዋጋ ላይ ክለሳ ማድረጉን አስታውቋል።
ይህም ጭማሪ ቢሆን የኅብረተሰቡን ጫና ለመቀነስ እንዲቻል ከጭማሪው አሁንም 50 በመቶውን ብቻ ወደ ተጠቃሚው በማውረድ ቀሪው በመንግሥት እንዲሸፈን መደረጉንም አስታውቋል፡፡
ከሰሞኑ የተቀሰቀሰው ጦርነት ግን አሁንም የነዳጅ የችርቻሮ ዋጋ ላይ ጭማሪ ሊያስከትል እንደሚችል ሥጋት ፈጥሯል። በመሆኑም መንግሥት እስካሁን ድረስ የነዳጅ ዋጋን ወደ ተጠቃሚው ለማስተላለፍ በወሰነው መሠረት እስሁን ድረስ በአማካይ ከአሥር በመቶ በላይ የዋጋ ጭማሪ እያደረገ የመጣ በመሆኑ በእስራኤልና ጋዛ (ሀማስ) መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ሊፈጥር የሚችለው የዓለም የነዳጅ ዋጋ በቀጥታ ወደ ተጠቃሚው ማኅበረሰብ ከማስተላለፍ ሊቆጠብ ይገባል ሲሉ ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች ይመክራሉ።
የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ አወት ተክኤ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚከሰት ጦርነትና አለመረጋጋት በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያሳድር ነው። በቀዳሚነትም የዓለም የነዳጅ አቅርቦትና ገበያ የሚታወክ በመሆኑ፣ ይህ ሁኔታ የሚከሰት ከሆነ አሉታዊ ተፅዕኖው ለኢትዮጵያም እንደሚተርፍና እንደሚያሠጋ ገልጸዋል።
‹‹የዓለም የነዳጅ ምርትና ገበያ ሰላምን ይፈልጋል›› ያሉት አቶ አወት እንዲህ ያሉ ትልልቅ ጦርነቶች በተለይ አገሮች በፖለቲካ አመለካከታቸው ወገንተኝነታቸውን በግልጽ በሚያሳዩበት ወቅት የነዳጅ ግብይት ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡ በተለይ አሁን በተቀሰቀሰው የእስራኤልና ጋዛ (ሀማስ) ጦርነት ምክንያት በአካባቢው የሚገኙ የመካከለኛው ምሥራቅ ነዳጅ ባለፀጎች ለአንደኛው ወገን የሚያደላ የፖለቲካ አቋም ለመያዝ ከተገደዱ ይህንን የፖለቲካ አቋማቸውን የሚገልጹት የነዳጅ ምርትና አቅርቦታቸውን በመገደብ እንደሚሆን ቀደም ሲል የነበራቸውን ተሞክሮ ዋቢ በማድረግ አስረድተዋል።
ከዛሬ 50 ዓመታት በፊት በነዚሁ ወገኖች መካከል በተቀሰቀሰ ጦርነት ነዳጅ አምራች አገሮች በሁለቱ ተፋላሚዎች መካከል ጎራ ለይተው በመሠለፋቸው በዓለም የነዳጅ ምርትና አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ዕክል ፈጥረው እንደነበር አስታውሰዋል። አሁንም እነዚሁ ተመሳሳይ አገሮች የሚፋለሙበት ጦርነት በመከሰቱ በነዳጅ ሀብት የታደሉት የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች በዋናነትም፣ ኢራንና ሳዑዲ ዓረቢያ ያሉ አገሮች አንደኛውን ተፋላሚ ወገን ደግፈው ምዕራባዊያኑ ደግሞ ሌላኛውን ወገን ደግፈው የሚቆሙ ከሆነ የዓለም የነዳጅ ምርትና አቅርቦትን ሊያስተጓጉልና ዋጋውም ጣሪያ ሊነካ እንደሚችል ሥጋታቸውን ገልጸዋል።
ይህ ሁኔታ ከተከሰተ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ትልቅ ፈተና እንደሚሆን እኝሁ የኢኮኖሚ ባለሙያ አመልክተዋል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግሥት ቀስ በቀስ ከነዳጅ ድጎማ ለመውጣት ቀስ በቀስ የሚያደርገውን የዓለም የነዳጅ ዋጋን መሠረት ያደረገ ወርኃዊ የችርቻሮ ዋጋ ማስተካከያ ቆም ብሎ ሊፈትሸው ይገባል ብለዋል።
ያልጠበቀውን ጦርነት ተከትሎ ሊመጣ የሚችለውን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ እንዳለ ኅብረተሰቡ ላይ መጫን የሚያዋጣ እንዳልሆነ ገልጸዋል። መንግሥት ከነዳጅ ድጎማ ለመውጣት በገበያ ዋጋ እየሠራ ቢሆንም እንዲህ ባሉ ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ግን ሊያስከትል የሚችለውን ተፅዕኖ ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖው ግልጽ ከመሆኑ አንፃር በተለይም በአሁኑ ወቅት የሚታየው የዋጋ ንረት ጦርነቱ ሊያስከትል የሚችለውን የዋጋ ጭማሪ ኅብረተሰቡ ላይ እንዲጫን ማድረግ ተገቢ አይሆንም ብለዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የዋጋ ንረቱን በማባባስ ማኅበረሰብን ብሎም ኢኮኖሚውን ይጎዳል ብለዋል።
በሌላ በኩል ግን የእስራኤልና የፍልስጤም ጦርነት ከተፋላሚ አገሮች ባሻገር አገሮችን ጎራ ለይተው ወገንተኝነታቸውን እየገለጹ መሆን ምናልባት ትላልቆቹ የነዳጅ አቅራቢዎች ነዳጅ ባያቀርቡ ዓለም ላይ ችግር እንዳይኖር በተቃራኒ ያሉ አገሮች ተጨማሪ ነዳጅ በማቅረብ ገበያውን ለማረጋጋት ሊሞክሩ የሚችሉበት ዕድል እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለበት ዕድል ጠባብ ቢሆንም አሁን ካለው ሁኔታ አንፃር ሲታይ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው አይቀመስም ብዙ አገሮችን ተጎጂ ያደርጋቸዋል፡፡ በተለይ ከፍተኛ የገቢ ንግድ ያለቸው አገሮች የዋጋ ጭማሪ ሊያስከትልባቸው እንደሚችል የኢኮኖሚ ባለሙያው ማብራሪያ ያመለክታል፡፡ ስለዚህ በተለይ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው ሊያስከትል የሚችለው ተፅዕኖ በማሰብ መንግሥትም ጊዜውን የዋጀ አሠራር ሊያስፈልገው እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
በአጠቃላይ ግን የመካከለኛው ምሥራቅ ጦርነት ዓለም አቀፉን ኢኮኖሚ ይፈትናል፡፡ ጦርነቱ ዛሬ ያቆማል ቢባል እንኳን በብዙ መልኩ ተፅዕኖው ቀላል እንደማይሆን ያስረዱት የኢኮኖሚ ባለሙያው በተለይ ዕቃን የሚያጓጉዙ የትራንስፖርት ዘርፎች በሚፈጠርባቸው ሥጋት እንቅስቃሴያቸው ይገደባል፡፡ ከዚህም ሌላ መንቀሳቀስ ከቻሉም ከፍተኛ የኢንሹራንስ ሽፋን የሚጠይቁ መሆኑንና ተያያዥ ጉዳዮች የአቅርቦት ዋጋን ስለሚያስወድዱ የጦርነቱ ግልጽ የሆነ ተፅዕኖ አለው ይላሉ፡፡