- ምን… ምንድነው ያሉት?
- ምነው ምን ሆንሽ?
- መንግሥት የጀመረው የማዕድ ማጋራት የዜጎችን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል ረገድ አስተዋጽኦ አድርጓል ነው ያሉት?
- አዎ፣ እንደዚያ ነው ያሉት።
- እንዴት?
- ምን እንዴት አለው?
- ያለነው በመኖሪያ ቤታችን አይደል እንዴ?
- ነው።
- ስለዚህ እንዴት ማለት እንችላለን።
- ምን ለማለት ፈልገሽ ነው?
- ያለነው ፓርላማ አይደለም ማለቴ ነው።
- እንዴት?
- ምን እንዴት አለው?
- አልገባኝም?
- እዚያ እንዴት ተብሎ አይጠይቅማ?
- መንግሥት ማዕድ እያጋራ መሆኑ የሚታወቅ ሀቅ አይደለም እንዴ? ምን ተብሎ ይጠየቃል?
- ማዕድ ስታጋሩማ እኛም እናያለን።
- ታዲያ ምንድነው ያስገረመሽ?
- መንግሥት ዓውደ ዓመት ሲመጣ የሚያጋራው ማዕድ ፓርላማ ላይ ስለተነገረ አይደለም የተገረምኩት።
- ታዲያ ምንድነው ያስገረመሽ?
- መንግሥት ማዕድ ማጋራቱ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል ረገድ አስተዋጽኦ አድርጓል መባሉ ነው።
- እንዴት? ይኼ ምኑ ያስገርማል?
- የዜጎች ኑሮ ደረጃ ተሻሻለ የሚባለው የበዓል ቀን ሲበሉ ነው?
- ለማለት የፈለጉት እንደዛ አይደለም።
- እኔ እሳቸው የተናገሩትን አዳምጫለሁ፣ እናንተ የፈለጋችሁትን ማለት ትችላላችሁ።
- የፈለጋችሁትን ማለት ትችላላችሁ ስትይ ምን ማለትሽ ነው?
- እናንተ እሳቸው የተናገሩትን ሳይሆን ለማለት የፈለጉትን በሉ ማለቴ ነው፣ ቆይ …ቆይ እስኪ … እንዴ…?
- ምንድነው?
- አትሰማም እንዴ የሚሉትን?
- አልሰማሁም ምንድነው ያሉት?
- በመንግሥት የምገባ ፕሮግራም9 ሚሊዮን ተማሪዎች ቁርስና ምሣ እየበሉና ቀጥለው ደግሞ…
- እ… ቀጥለው ምን አሉ?
- የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ድህነትን ከመቀነስ ባሻገር አምራች ዜጋ ለመፍጠርና ትውልድ ለመገንባት የሚያስችል ለውጥ አምጥቷል አሉ፡፡
- እና ምነው ተገረምሽ?
- እንዴት አልገረምም?
- ለምን?
- ድህነት በምገባ ፕሮግራም ይቀንሳል እንዴ?
- ለምን አይቀንስም?
- በምገባ ፕሮግራም ሊቀንስ የሚችለው ድህነት አይመስለኝም።
- እና ምንድነው የሚቀንስ የሚመስልሽ?
- በምገባ የሚቀንስው?
- እ…?
- ረሃብ ነዋ፡፡
- አትሳሳቺ፣ ድህነትንም ለመቀነስ ይጠቅማል።
- እኮ እንዴት?
- የምግባ ፕሮግራሙ የተማሪ ቤተሰቦችን እያገዘ ነዋ፡፡
- እና ድህነት በቁርስና በምሣ ይቀንሳል ልትለኝ ነው?
- ለምን አይቀንስም?
- ኧረ ዛሬ ምንድነው የምሰማው?
- ምን ሰማሽ?
- አትሰማም እንዴ የሚሉትን?
- ምን አሉ?
- በየማዕከላቱ የሚመገበው የሕዝብ ብዛት እንደ አገር ቢቆጠር በአፍሪካ በ35ኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጥ ነው እያሉ እኮ ነው?
- እሱማ እውነት ነው፣ እንዲያውም እሳቸው በደረጃ አስቀመጡት እንጂ ከአገሮች ጋር ቢያነፃፅሩት ይሻል ነበር።
- እንዴት? ምን ማለትህ ነው?
- በማዕከላቱ የሚመገበው የሕዝብ ብዛት የኢኳቶሪያል ጊኒ፣ የጋቦንና የቦትስዋና ሕዝቦች ተደምረው ማለት እኮ ነው።
- አሃ… እንዲህም ማሰቀመጥ ይችሉ ነበር?
- ታዲያስ?
- ይገርማል፡፡
- የሚያስደንቅ ነው እንጂ፡፡
- ሰማሁ እኮ፡፡
- ምን?
- መጨረሻ ላይ ያሉትን።
- ምን አሉ?
- በየምገባ ማዕከላቱ የሚመገበው በሕዝብ ብዛት ደረጃ ቢታይ በአፍሪካ 35 ደረጃ ላይ የሚቀመጥ ነው፣ ይህም የአገራችንን ኢኮኖሚ ጥንካሬ የሚያሳይ ትልቅ ስኬት ነው አሉ።
- ትክክል ነው።
- ይገርማል።
- ምኑ ነው የሚገርመው?
- ይህን የሚያህል ሕዝብ በመንግሥት ምገባ ሥር መሆኑ ለእኔ የሚሰጠኝ ትርጉም ሌላ ነው።
- ምንድነው?
- ያለው ድህነት ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ።
- እኛ ግን እንደዚያ ብለን አንወስድም።
- የገረመኝ በእሳቸው መነገሩ እንጂ፣ እናንተማ የምትኩራሩበት መሆኑን አውቃለሁ።
- መንግሥት እኮ ነው የሚያዘጋጀው፡፡
- ምኑን?
- የእሳቸውን ንግግር።
- እንደዚያ ነው እንዴ?
- አዎ።
- ታዲያ ቀድመህ አትነግረኝም ነበር!
- Advertisment -
- Advertisment -