ከሽሮሜዳ ወደ ሜክሲኮ ልንጓዝ ነው። የኑሮ ሸክም የከበዳቸው ምንዱባን ፊትና ኋላ ሆነው እየተራመዱ ነው። ‹ሕይወት ፊቷ ወዴት ነው?› ቢሉት አንዱን ሻማ ለኩሶ ‹የዚህ ሻማ ብርሃን ዓይን ወዴት ነው?› ያለውን የጠቢብ ሰው ምላሽ የሚያውቁ ጥቂት መሆናቸው ያስቆጫል። በተረፈ ግን የዓለም ጣጣ ሁሉ እሱና እሱ ላይ ብቻ የተከመረ የሚመስለው ይበዛል። አንዱ ‹የእኔውስ ነገር አይነገር› ሲል ሌላው የፈጣሪን ስም እየጠራ ‹እንደ እኔ የረዳው ማንም የለም› ብሎ በምሥጋና ወደ ሰማዩ ያንጋጥጣል። በመሀል ያ ሰው ሠራሹ ስህተትና መከራ ግን አለ፣ አይወራም። ዘወትር በመፈክርና በፕሮፓጋንዳ ብዛት ናላው እየዞረ እንደሚኖር ምስኪን ሕዝብ፣ ዕንባው ሳይታበስ የዋይታውን ርስት ለተረካቢው እያወረሰ ያልፋል። ያም በዋይታ ዘርቶ በዕንባ አጭዶ ያለ ፍሬ ያልፋል። ‹‹ይኼም ደግሞ ከንቱ ንፋስንም እንደ መከተል ነው…›› ይላል ከሠልፈኞች መሀል አንዱ። ‹‹ምኑ?›› ትለዋለች ከኋላው። ‹‹ሁሉም ነገር…›› ይላታል። ያሰኛል!
‹‹ያደለው እንደ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በፓርኮች፣ በአካፋይ መንገዶች፣ በሪል ስቴቶች፣ ፀዳ ፀዳ ባሉ መኖሪያ ቤቶችና ለዓይን በሚማርኩ ዕይታዎች ይዋባል፡፡ እዚህ ደግሞ የነገር ገመዳቸውን እየጎተቱብን ድህነታችንን የበለጠ ያወሳስቡብናል…›› ይላል ከፊት የተሠለፈ ጎልማሳ። ‹‹ምን ይላል ይኼ ያለፉበትንና ያልደከሙበትን ሀብት እያጋበሱ የሚሞላቀቁት ናቸው እንዴ ለእኛ እንደ ውብ ምሳሌ ሆነው የሚቀርቡልን?›› የሚለው ደግሞ አንድ ሌላ ጎልማሳ ነው። ከፊት የቆመው ጎልማሳ ዘወር ብሎ፣ ‹‹ከሐሳብና ከንፋስ አመጣሽ ገንዘብ የቱ ይበልጣል?›› ከማለቱ፣ ‹‹እሱማ ጥራት ያለው ሐሳብ የሚበልጥ ቢሆንም ትውልዱ ግን ዓይኑም ሆነ ቀልቡ ያለው ገንዘብ ላይ ብቻ ነው…›› ትላለች ሠልፉ መሀል ወገብ ላይ የቆመች ዘንካታ። ‹‹አሁንስ ጎዳናው በሙሉ ለዛ እያጣ ነው…›› ሲል እንሰማዋለን ጎልማሳውን። ምሬት ሳይሆን አይቀርም!
ጉዟችን ተጀምሯል። ‹‹የእኔ ልጅ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት አጠገብ ምስካዬ ሕዙናን መድኃኔዓለም ደጅ ላይ ጣለኝ በሞቴ፡፡ ከአምላኬ ጋር ጥብቅ ቀጠሮ አለኝ…” ብለው አንዲት እናት ተሳፈሩ። ‹‹ኧረ ማዘር በእኔ ይሁንብዎት ግድ የለም…›› ወያላው በልጅነት ስሜት ታዛዥነቱን ያሳያል። ‹‹ተባረክ ይህንንም አንተ ሆነህ አይደል በነፍስ የተለመንክ? አንዱ ይኼውላችሁ በቀደም ዕለት ግዴለም ተሳፈሪ እሸኝሻለሁ ብሎ አሳፍሮኝ ሲያበቃ፣ መሀል መንገድ ሲደርስ የትራፊክ ፖሊስ ይከሰኛል ብሎ አስወረደኝ። ዋ ሰው በደጉ ጊዜ በቅሎ ጭነን፣ ፈረስ ለጉመን ስንቱን ያለ ክፍያ የትናየት እንዳልሸኘን፣ ዛሬ መኪናው ለሚወስደንና ጊዜ ለሚያሳፍረን ሞልቷል ውረዱ የሚሉን በዙ…›› ብለው አዛውንቷ ቆዘሙ። ‹‹ወዴት እየሄዱ ነው?›› ጠየቀቻቸው ከሾፌሩ አጠገብ ጋቢና የተሰየመች ወይዘሮ። አዛውንቷ የመንገዱን ዙሪያ ገባ ቃኝተው፣ ‹‹መድኃኔዓለም ዘንድ ቀጠሮ ስላለኝ እዚያ ነው የምሄደው›› እያሉ ሳቁ። ወይ ቀጠሮ!
አንድ ወጣት ደግሞ፣ ‹‹ምንድነው በፌስታል የያዙት?›› ጠየቃቸው። ‹‹እሱ ደጅ ስሄድ ለምስኪኖች ትንሽ የምትበላ ነገር ቋጥሬ ነው…›› ብለው አሳጥረው መልሰው ረዥም ትካዜ ውስጥ ገቡ። ‹‹እናታችን ለድሆች የሚሰጥ ምግብ ነው…›› ጎልማሳው ሌላ ጥያቄ አመጣ። ‹‹ይኸውልህ ሁላችንም በፈጣሪ ፊት ምስኪኖች ነን፡፡ አንዳችን ከሌላችን ትንሽ ሻል ብንልም የሰው ልጅ ደሃ አይባልም፡፡ አሁንማ ጥጋባችሁ ለከት አጥቶ የደሃ ደሃ እያላችሁ የሰውን ልጅ ስትጠሩ አታፍሩም፡፡ አሁን እኔ ምስኪኗ ለእነዚያ ምስኪኖች የምትሆን ትንሽ ነገር መቋጠሬን ባልናገር ጥሩ ነበር፡፡ ቅዱስ መጽሐፉም የሚለው እንደዚያ ነው…›› አሉትና በትካዜ ውስጥ ሰጠሙ። ዓይኖቻቸው መሀል የዋህና የገራገር እናቶች ሲቃ ጎልቶ ተሰማን መሰል ሁላችንም ለጊዜው ዝም አልን። አሁንማ በሰፊው ፀጥታ የሚያስፈልገን ይመስላል፡፡ በፀጥታ ውስጥ ያለው ሰላም የትም አይገኝምና!
‹‹ቅድም ስለለሚ ኩራ ውበትና አስደሳችነት ያነሳኸው ጉዳይ ሳይጠናቀቅ ወደ ሌላ ነገር ገብተን ተቋረጠብን አይደል…›› ብሎ አንዱ ጎረምሳ መሳይ ወደ ጎልማሳው ሲያንጋጥጥ፣ ‹‹እኛ የጉለሌ፣ የየካ፣ የቂርቆስ፣ የአራዳ፣ የንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ የኮልፌ ቀራኒዮ…›› እያለ አንዱ ከመሀል ወንበር ክፍላተ ከተሞቹን ሲዘረዝር፣ ‹‹ሾፌር እባክህን አንዴ አዲስ አበባ ቤቴ የሚለውን የዓለማየሁ እሸቴን ምርጥ ዘፈን ጋብዘህ ገላግለን…›› ብላ አንዲት የጠይም ቆንጆ ድንገት ዘው ብላ ገባች፡፡ አንድ በዕድሜ ጠና ያሉ ሸበቶ አዛውንት፣ ‹‹አገር ሲያረጅ የጃርት መጫወቻ ይሆናል…›› ብለው ሲያሾምሩ ወያላው ፊቱን በፈገግታ ሞልቶ፣ ‹‹አባታችን ጮሌ ሲያረጅ መጋዣ ይሆናል…›› የሚል ጥቅስ መርካቶ ሻይ ቤት ውስጥ ያነበብኩትን አስታወሱኝ ብሎ ሲያያቸው፣ ‹‹ካመጣኸው አይቀርማ ካልጠፋ ገበያ ጓያ ሸመታ የሚባለውንም እንዳትረሳ…›› ብለው ሲስቁ ታክሲያችን ውስጥ ዘና የሚል ስሜት ተፈጠረ፡፡ ይሻላል!
‹‹አባታችን መቼም ጨዋታ በምሳሌያዊ አነጋገሮችና በአባባሎች ሲታጀብ ያምራል…›› እያለ ጎልማሳው፣ ‹‹የአባያ በሬ ወንድም ይታረስበታል እንጂ አይታረድም የሚል ጥቅስ አንድ ጽሑፍ ላይ አየሁና ትርጉሙ ሳይገባኝ ቀረ…›› ብሎ ወደ አዛውንቱ ጥያቄ ሲወረውር፣ ወያላው ሾፌሩ ታክሲውን እንዲያቆም አስደርጎ፣ ‹‹እናታችን መድኃኔዓለም ደርሰዋል ይውረዱ…›› ብሎ ደግፎ አወረዳቸው፡፡ እሳቸውም ምርቃት በምርቃት አዥጎድጉደውበትና እኛንም አመሥግነው፣ ‹‹አንዱ ቢናገር ሁሉም ይሰማል፣ ሁሉም ቢናገር ማን ይሰማልና ስለሆነ እባካችሁ እየተከባበራችሁ በመነጋገር ተደማመጡ፡፡ ብንከባበር እኮ ኢትዮጵያ ምድራዊ ገነት እንጂ ሲኦል አትሆንም ነበር፡፡ ለማንኛውም መድኃኔዓለም ከሁላችንም ጋር ይሁን…›› ብለውን ተሰናበቱን፡፡ የእናታችንን ምርቃትና ምክር ተቀብለን ወደ ወጋችን ግን እየተመለስን ነበር፡፡ የግድ ነው!
አዛውንቱ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ መስጠት ሊጀምሩ፣ ‹‹እህ… እህ… እህ…›› በማለት ትኩረታችንን ሳቡት፡፡ ‹‹…የእኔ ወንድም…›› ብለው ወደ ጎልማሳው ዞረው፣ ‹‹…ምን መሰለህ ወንድሜ አባያ በሬ በረት በመበጥበጥ፣ ሌሎች ከብቶችን በማመስና ቀንዱን ባገኘው ላይ በማሾል ነው የሚታወቀው፡፡ እሱን አስቸገረ ብለህ ወንድሙን ከማረድ እያረሱበት ሙያ ማስተማር ይሻላል ለማለት ነው፡፡ አሁን በዚህ ዘመን ያስቸገረው እንዲህ ያለውን ጥበብ ለመጎናፀፍ አለመቻል ነው፡፡ አይደለም እንዴ…›› ብለው ሲስቁ፣ ‹‹አሁንማ ዳኛውም ዝንጀሮ መፋረጃው ገደል፣ አሁን እንዴት ሆኖ ይነገራል በደል…›› የሚለውን ማንጎራጎር ነው ልማዳችን የሆነው ብላ ያች የጠይም ቆንጆ አሁንም ድንገት ዘው ስትል ሳቅ በሳቅ ሆንን፡፡ እንሳቀው እንጂ!
አንድ ወጣት አብሮት ከተቀመጠው ጓደኛው ጋር የጀመሩት ወግ ድንገት ጆሮአችን ውስጥ ጥልቅ አለ፡፡ ‹‹አሁንማ በዚህ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ምክንያት ብዙ ነገሮች ቢቀሉም፣ መረጃዎቻችን ግን በሌሎች ቁጥጥር ሥር እየዋሉ አሳር የምንበላበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም…›› ሲለው፣ ‹‹እንዴት ሆኖ ነው አሳራችንን የምንበላው…›› ይላል ያኛው፡፡ ‹‹እስኪ ስልክህን ልብ ብለህ አስተውል፡፡ አንድ የፊልም ወይም የዕቃ ዓይነት ለማየት በላፕቶፕህ ወይም በዴስክቶፕህ ላይ ስታስስ፣ ትንሽ ቆይቶ በስልክህ የማይመጣልህ ነገር የለም፡፡ ዋትስአፕ ወይም ቴሌግራም ላይ ገብተህ የሆነ ነገር ስታስስ በዩቲዩብ ወይም በሌላ ፕላትፎርም ሰተት ብሎ ይመጣልሃል፡፡ ከዚህ የበለጠ ምን ወረራ ሊኖር ነው ታዲያ፡፡ በእነሱ ቁጥጥር ሥር ሆንን ማለትም አይደል…›› ከማለቱ ያኛው ደንግጦ፣ ‹‹በእነ ማን ቁጥጥር ሥር…›› ብሎ ሲያንጠለጥለው፣ ‹‹በማን ልበልህ መንግሥት፣ ድንበር ዘለል ኩባንያዎች፣ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች…›› እያለ ሲዘረዝር ሌላ ራስ ምታት ጨመረብን፡፡ ኤዲያ!
ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ‹‹ኤድያ ምንድነው ይኼን ያህል መንቦቅቦቅ…›› ወይዘሮዋ ከጋቢና በንዴት ተንጫጫች። ‹‹…እንኳን አሁንና ጥሩ ትጥቅ እያለን፣ በጦር በጎራዴ ታንክ እንማርካለን እያሉ ታላላቅ የአርበኝነት ገድሎች ሲፈጸምባት የኖረች አገር ውስጥ ተፈጥረን የምን ፍራቻ፣ የምን ሥጋት ነው የምታወሩት…›› አለች። ‹‹እስኪ አሁን ዓለም አንድ መንደር በሆነችበት በዚህ ዘመን በሌሎች ቁጥጥር ሥር እንውላለን ተብሎ ይህንን ያህል መፍራት ምን የሚሉት በሽታ ነው?›› ብሎ አንዱ በወይዘሮዋ ላይ ተደርቦ ሲናገር ሌላው ቀበል አድርጎ፣ ‹‹አንድ መንደር አብረን ሆነን ነዋ የዴሞክራሲው፣ የመልካም አስተዳደሩ፣ የፍትሕ ጉዳይ አሉባልታና ወሬ ብቻ የሆነብን? አንድ ላይ ሆነን ነዋ እነ አሜሪካ እንደፈለጉ በዚህ ግቡ በዚህ ውጡ ሲሉን እንደ አሽከር የሚያዙን…›› ይለዋል። ታክሲያችን ሜክሲኮ ደርሶ ወያላው ‹‹መጨረሻ!›› ብሎ በሩን ከፈተው። የተጀመረው ርዕሰ ጉዳይ እልህ ውስጥ ከቶን ነው መሰል ስሜታችን ደፍርሶ ለወጉ ያህል ሰላምታ ተሰጣጥተን ወደ ጉዳያችን አመራን፡፡ መልካም ጉዞ!