Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

ጥራትና ምርታማነትን በካይዘን ለማስመር

ኢትዮጵያ ውስጥ ጥራት ያለው ምርትን ለማሳደግ፣ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን፣ ኢንዱስትሪውን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሳደግ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ በተለይ ተዋናዮቹን ለማብቃትና በቴክኖሎጂ የታገዙ ምርቶችን ለማምረት ዘርፉ በሠለጠነ የሰው ኃይል እንዲመራ ማድረግ የመንግሥት ሥራ ብቻ እንዳልሆነ ብዙዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ በዚህ መሠረት እንደ አገር የአምራች ኢንዱስትሪውን ለማነቃት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ዕውን ለማድረግ እየሠራ ይገኛል፡፡ ይህንን ንቅናቄ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግና አምራች ኢንዱስትሪዎች የነበረባቸውን ማነቆ ለመፍታት በኢትዮጵያና በጃፓን መካከል በተደረገ ስምምነት በ1.9 ሚሊዮን ብር ወጪ የካይዘን ልህቀት ማዕከል ተቋቁሞ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡ አቶ ምንዳዬ ይርጋ የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ የማዕከሉን ተግባር በተመለከተ ተመስገን ተጋፋው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የካይዘን ልህቀት ማዕከል ዓላማው ምንድነው?

አቶ ምንዳዬ፡- የካይዘን ልህቀት ማዕከል ዋና ዓላማው ከመንግሥት የተቀበለውን ተልዕኮ መሠረት በማድረግ፣ ጥራትና ምርታማነት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል፡፡ ማዕከሉም በኢትዮጵያ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅማቸውን አንድ ደረጃ ከፍ እንዲል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለማበርከት እየሠራ ይገኛል፡፡ የካይዘን ፍልስፍና በኢትዮጵያ ሊተዋወቅ የቻለበት ዋናው መነሻ በጃፓን በሐምሌ 2000 ዓ.ም. በተካሄደው አራተኛ የቶኪዮ ዓለም አቀፍ የአፍሪካ ልማት ጉባዔ ነው፡፡ በመድረኩ በታዋቂ ፕሮፌሰሮች በሌሎች የአፍሪካ አገሮች የተቀመረ የካይዘን ትግበራ ተሞክሮና ውጤታማነቱ ለአገሮች መሪዎች የቀረበበት ነበር፡፡ ወቅቱም አገራችን ለውጭ አገሮች ኢንቨስትመንት ተመራጭ እየሆነች የመጣችበት ስለሆነ፣ ይህንን ማዕከል ለማቋቋም ተችሏል፡፡ በተለይም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እያደገ የመጣበት አጋጣሚ ስለነበር፣ ካይዘንን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ አምራች ኢንዱስትሪዎች ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ በመንግሥት በኩል ስለታመነበት ካይዘን በፕሮጀክት ደረጃ በተመረጡ የአምራች ተቋማት ትግበራ እንዲጀመር ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት በጥቅምት 2002 ዓ.ም. ‹‹የጥራትና የምርታማነት ማሻሻያ ጥናት በኢትዮጵያ›› የሚል ፕሮጀክት ለአንድ ዓመት ከአምስት ወራት ሲተገበር ቆይቷል፡፡ በነዚህ ጊዜያትም 30 አምራች ኩባንያዎች ተመርጠው ፍልስፍናውን የማስተዋወቅና ተግባራዊ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል፡፡ በተለይ የፕሮጀክቱ ግምገማ የሚያሳየው የጥራትና ምርታማነት ትግበራ ስኬታማ ሆኖ ስለተገኘ፣ የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ በደንብ ቁጥር 256/2004 ሊቋቋም ችሏል፡፡

ሪፖርተር፡- ማዕከሉ ምን ዓይነት አገልግሎቶችን ይሰጣል?

አቶ ምንዳዬ፡- ማዕከሉ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለመስጠት፣ እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከመንግሥት በኩል ተልዕኮዎችን ተቀብሎ እየሠራ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዓላማዎችና በሒደቱ የተገኙ አበረታች ውጤቶችን ከማስቀጠል አኳያ ሰፊ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ይሆናል፡፡ በተለይም ትልቁና መጀመርያ የተመሠረተበትን ዋነኛ ምክንያት የሥልጠና፣ የማማከር፣ የጥናትና ምርምርና የብቃት ማረጋገጥ አገልግሎቶችን ለመስጠት ታስቦ መሆኑ ለየት ያደርገዋል፡፡ ማዕከሉም ከ1,500 ለሚበልጡ የአምራችና አገልግሎት ኢንዱስትሪዎች የሥልጠና አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ከሁሉም በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማዕከሉ የበኩሉን ድርሻ ይወጣል፡፡ በዚህ መሠረት የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ተልዕኮን ተግባራዊ ለማድረግ ማዕከሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ የካይዘን ፍልስፍናን ሥርፀት ለማሳደግ የሚያስችል ስትራቴጂን ለመተግበር፣ ብሔራዊ የጥራትና ምርታማነት አቅም የሚያድግበትን ሥልት መቀየስና ውጤማነቱን ማረጋገጡ ላይ ማዕከሉ ሰፊ እንቅስቃሴ ያደርጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በሥራችሁ ችግር ገጥሟችኋል?

አቶ ምንዳዬ፡- በኢትዮጵያ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች በሥልጠና የታገዙ እንዲሆኑ ማዕከሉ ኃላፊነቱን የሚወጣ ይሆናል፡፡ በተለይ አብዛኛዎቹ ኢንዱስትሪዎች የምርታማነት ዕድገታቸውን እንዲያሻሽሉ ቢሠራም፣ በብዙዎቹ ከፍተኛ ክፍተት ይታያል፡፡ አምራች ኢንዱስትሪዎች የካይዘን ፍልስፍናን ባህል አድርገው ከመቀጠል አኳያ፣ እንዲሁም በባለቤትነት ከመውሰድ አንፃር ሰፊ ልዩነት ይታይባቸዋል፡፡ ከሁሉም በላይ አብዛኛዎቹ ኢንዱስትሪዎች ‹‹ካይዘን ምንድን ነው?›› የሚለውን ከማወቅ ይልቅ፣ ሌላ አማራጮችን ስለሚወስዱ ሥራችን ላይ ክፍተት እንዲኖርብን አድርጎብናል፡፡ በሌላ በኩል ከተደራሽነት አንፃር ሰፊ ክፍተቶች ነበሩብን፡፡ በአሁኑ ወቅት እነዚህንም ክፍተቶች ሙሉ ለሙሉ በማስወገድ የዘርፉ ተዋናይ የሆኑ ሰዎች ችግራቸውን እየቀረፍን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- በዘርፉ የተሰማሩ ተዋናዮች ያሉባቸውን ክፍተቶች ምንድን ናቸው? ማዕከሉስ ይህንን ችግር በምን መልኩ ይፈታዋል?

አቶ ምንዳዬ፡- በዘርፉ የተሰማሩ መሪ ተዋናዮች ላይ ሰፊ የሆነ ክፍተት አለ፡፡ በተለይ አምራች ኢንዱስትሪዎች ጥራት ያለው ምርትን ለገበያ ከማቅረብ አኳያ ክፍተቶች ይታዩባቸዋል፡፡ አምራች ኢንዱስትሪዎች በጥራትና በምርታማነት ላይ ያለባቸው ክፍተቶች ከፍተኛ መሆኑ ችግሩን ይበልጥ አጉልቶታል፡፡ ከሁሉም በላይ እያንዳንዱ ሠራተኛ ወደ ኢንዱስትሪ ዘርፉ ሲሰማራ በቂ የሆኑ ሥልጠናዎችን ባለማግኘቱ ጥራት ያለው ምርት ለማግኘት ችግር ሆኖብናል፡፡ አብዛኛው ሠራተኛ ቀጥታ ወደ ኢንዱስትሪ የሥራ ዘርፍ ከመግባቱ በፊት ሥልጠናዎችን ቢያገኝ ምርቶቻችንን ማሳደግ ይቻላል፡፡ እንደ አገር ምርቶቻችንን ከሌሎች አገሮች ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆኑ፣ መንግሥት የተለያዩ ፖሊሲዎችን ቀርፆ እየሠራ ይገኛል፡፡ ይህንን ማድረግ ከተቻለ ምርቶቻችንን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሳደግ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- በክልል ደረጃ ተደራሽነታችሁ ምን ይመስላል?

አቶ ምንዳዬ፡- የክልል የካይዘን ንቅናቄ መድረኮችን በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በደቡብና በሐረሪ ክልሎች በማዘጋጀትና ፋይዳውን በማስገንዘባችን የጠራ ምልከታ እንዲያዝ ለማድረግ ተችሏል፡፡ ለክልሎች የካይዘን ምሥረታ ድሬዳዋ፣ ሐረሪና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ድጋፍ በመስጠትና ቴክኒካዊ ዕገዛዎች እንዲያገኙ በማድረግ፣ በክልሎች በራስ አቅም የካይዘን ትግበራዎችን ማከናወን እንዲችሉ አቅም ተፈጥሯል፡፡ በቀጣይም ወደ ተለያዩ ክልሎች በመሄድ የካይዘን ልህቀት ማዕከልን ማስፋፋት የግድ ይላል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለ ልህቀት ማዕከሉ ግንባታ ቢገልጹልን?

አቶ ምንዳዬ፡- የማዕከሉ ሕንፃ ግንባታ አጠቃላይ ወጪ 1.9 ቢሊዮን ብር የፈጀ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥም 1.4 ቢሊዮን ብር በጃፓን መንግሥት ተሸፍኗል፡፡ ቀሪው በኢትዮጵያ መንግሥት መሸፈን ችሏል፡፡ ኢትዮጵያ የቀድሞ የላቀ የካይዘን አፈጻጸም ውጤት ከሌሎች አፍሪካ አገሮች የተሻለች ስለነበር ማዕከሉ በጃፓን ድጋፍ ሊቋቋም ችሏል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ሠራተኛ ስቀጥር ካለመሠልጠናቸውም በላይ ስንት ይከፈለኛል ብለው ሲጠይቁ እደነግጥ ነበር›› ወ/ሮ ቅድስት ጌታቸው፣ የሶጋ ትሬዲንግና ፖላር ፕላስ ኤክሰለንስ ሀብ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ

በኢትዮጵያ የሚገኙ ቀጣሪ ድርጅቶች የሚፈልጉት የሠለጠነ የሰው ኃይልና የሥራ ፈላጊው ብቃት በብዛት አይጣጣምም፡፡ በዚህም ቀጣሪዎች ብቁ የሰው ኃይል አለማግኘታቸውን፣ ሠራተኞችም የሚፈልጉትን የሥራ ዓይነት አጥተው...

‹‹የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል›› አቶ ያዕቆብ ወልደ ሥላሴ፣ የሮያል ፎም ስፕሪንግ ፍራሽና የፕላስቲክ ውጤቶች ማምረቻ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል በኢንቨስትመንት ዘርፉ የተሰማሩ ተቋሞችን መደገፍ የግድ እንደሚል ይታመናል፡፡ መንግሥት ሊያደርግ ከሚችለው ድጋፍ አንዱ ደግሞ የውጭ...

‹‹የግንባታ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን ክህሎት እንዲያሟሉ ትምህርታቸው በሥራ ላይ ልምምድ የታገዘ መሆን አለበት›› አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ፣ የናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት መሥራች

ናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታትም በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ለደንበኞቹ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢንጆይ ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል...