Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገር“ካሳንድራ ሲንድረም” በኢትዮጵያ

“ካሳንድራ ሲንድረም” በኢትዮጵያ

ቀን:

በቶፊቅ ተማም

ዓለማየሁ ዋሴ (ዶ/ር) ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በብዛት ተነባቢ የሆኑ መጻሕፍትን የሰጡን ደራሲ ሲሆኑ፣ በቅርቡ ‹‹ችቦ›› ብለው በሰየሙት መጽሐፍ ላይ ያነሱት አንድ ሐሳብ ለዚህ ጽሑፍ መንደርደርያ ማድረግ ፈለግሁ፡፡ ጸሐፊው በዚህ መጽሐፋቸው ገጽ 165 ላይ ይህን ይላሉ፡፡

‹‹ካሳንድራ በግሪክ አፈ ታሪክ (Mytology) ታሪኳ የተጠቀሰ ንግሥት ናት፡፡ እጅግ ቆንጆ በመሆኗ ከግሪክ አማልክት አንዱ የሆነው ‹አፖሎ› በፍቅሯ ይነደፋል፡፡ እናም እንድታገባው ይጠይቃታል፡፡ እርሷም የምትጠይቀውን ከሰጣት ለማግባት ፈቃደኝነቷን ትገልጽለታለች፡፡ በዚህም ተስማምቶላት የምትፈልገውን እንድትነግረው ይጠይቃታል፡፡ እርሷም ወደፊት የሚሆነውን ነገር በትክክል የማወቅና የመተንበይ ፀጋ እንዲሰጣት ትጠይቀዋለች፡፡

‹‹አፖሎም በፍቅራ ተሸንፎ ስለነበር የጠየቀችውን የትንቢት ፀጋ ሳያቅማማ ሰጣት፡፡ ከሳንድራ ይህ ፀጋ እንደተሰጣት ባወቀች ጊዜ ቃሏን አጥፋ ቃልኪዳኗን ጥሳ የጋብቻውን ጥያቄ ውድቅ አደረገችበት፡፡ በዚህ የተበሳጨው አፖሎ በአማልክት ልምድና ሥርዓት መሠረት የተሰጠውን ፀጋ መልሶ ማንሳት እንደማይቻል ስላወቀ ሊረግማት ፈለገ፡፡ እናም እንዲህ ብሎ ረገማት፣ ‹የወደፊቱን በትክክል መተንበይ የምትችይ ቢሆንም ማንም ቃልሽን አይስማ፣ ተከታዮችሽም አይቀበሉሽ፣ የምትናገሪውን የሚያዳምጥሽ አንድ እንኳ አይኑር፡፡ በአሁኑ ዘመን እንዲህ ያለ የመደመጥ ችግር ሲያጋጥም ምዕራባውያን ‹Casandra Syndrome› በማለት ይጠሩታል፤›› ሲሉ አሥፍረዋል፡፡

ከላይ በመጽሐፉ እንደተነሳው በተለይ እንደ አገር እርስ በርስ ተደማምጦና ተደራድሮ አገርን ማሳደግ፣ ከጦርነትና ከዕልቂት ማዳን ሲቻል አገርን ወደፊት አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ጉዳዮች በተለያዩ አካላት በግልጽ ቢተነበይም፣ ይህንን በአግባቡ አድምጦ የመፍትሔ ዕርምጃ መውሰድ ሲቻል ይህንን ማድረግ ለምን አልተቻለም? እንደ አገር ባሳለፍነው ታሪክ ስለምን ለምክክር ዕድል መስጠት ስለምንስ መደማመጥ አቃተን? በማለት ጥቂት ሐሳብ ለማንሳት ነው፡፡

ዕድሜ ጠገብ የሆነችው ኢትዮጵየ ብዙ የግጭትና የጦርነት ታሪክ ብታሳልፍም፣ ከዚህ ታሪክ ጀርባ ሰላምን ሊያወርድ የሚችል ዕርቅ ለምን ከግጭት በፊት መከወን አልተቻለም? ይህ ለብዙዎች እንቆቅልሸ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡ የበፊቱን ትተን ‹‹ከለውጡ›› በኋላ ባሉ ዓመታት በተከሰቱ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ላይ ይህ ነው የሚባል መደማመጥና ድርድር መካሄድ አልተቻለም፡፡ ለዚህም የተወሰኑ ማሳያዎችን እንመልከት፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት እንደ አገር ተወዶም ባይሆን በግድ የተገባበት የትግራይ ጦርነት ዳፋ እስካሁን አለ፡፡ ከዚህ ሁለት ዓመታትን የፈጀ የወንድማማቾች ጦርነት ከመገባቱ በፊት ዕውን የድርድር፣ በሰከነ መንገድ የመደማመጥ፣ የምክክር አማራጭና ዕድል አልነበረምን?

ለመሆኑ የነበሩ ዕድሎች የትኞቹ ነበሩ በጨረፍታ ጥቂቱን እንመልከት፡፡ ወደ እዚህ ጦርነት ከመገባቱ በፊት በገዥው ፓርቲ ብልፅግናና በሕወሓት መካከል ያለውን ግጭት ለማሸማገልና እርስ በእርስ በወጉ እንዲደማመጡ ጥረት ተደርጎ ነበር፡፡ የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና እናቶች ከጦርነት ይልቅ በፅኑ መደማመጥና ድርድር ይቀድም ዘንድ ሁለቱን ወገኖች ወደ ጠረጴዛ ለመውሰድ ጥረት ቢያደርጉም፣ ጥረታቸው ፍሬ ሳያፈራ መቅረቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡

ሌላው ጦርነቱ የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት የተደረገ የድርድር ጥረት የነበረ ሲሆን፣ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የቀድሞ ፕሬዚዳንቶች በአዳራዳሪነት ለማሸማገል ቢሞከርም አልተሳካም፡፡ በመቀጠል በአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ በቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ግጭት እንዲቆምና የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈረም ወደ መቀሌ አምርተው፣ ሁለቱን ወገኖች የማደራደር ጥረት ቢያደርጉም በሚገባው ልክ ሊሳካ አልቻለም፡፡

መንግሥት አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ውጭ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ አገር ቤት ገብተው በሰላም እንዲንቀሳቀሱ በተሰጠ ዕድል መሠረት ብዙዎች ገቡ፡፡ ወደ አገር ውስጥ ከገቡ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በተለይም ከኦሮሞ ነፃነት ግንባርና ሌሎች መሠረታቸውን በኦሮሚያ ካደረጉ ኃይሎች ጋር ዕርቅን በአግባቡ ፈጽሞና ተመካክሮ ለአገር ሰላም ለመሥራት ጥረት ተደርጓል፡፡ በተለይ በኦሮሞ ብሔር ዘንድ ከፍተኛ ተሰሚነት ባላቸው በአባገዳዎች አማካይነት የድርድር ዕድል ቢሰጥም ይህም ፍሬ ያላፈራ ሲሆን፣ ከዚህ ባለፈ ይህን ለአገር የሚበጅ ድርድር የበለጠ ለመጠቀም ከአገር ውጪ በዛንዚባር ቢቀጥልም ከጥቂት ፍንጭ በስተቀር በሚገባው ልክ ሊሰምር አልቻለም፡፡ በሰሜን የአገሪቱ ክፍል እንደተደረገው ሁሉ በኦሮሚያ ክልል ያለውን አለመግባባት ተመሳሳይ በሆነ ሰላማዊ አካሄድ ለመፍታት ጥረቶች መቀጠል አለባቸው፡፡

ሌላው በአሁኑ ወቅት አሳሳቢ የሆነው ጉዳይ በተለይ ካለፉት ወራት ጀምሮ የተከሰተው የአማራ ክልል የፀጥታ መደፍረስ ሲሆን፣ በክልሉ በተከሰተ የፀጥታ ችግር ሳቢያ ባለፈው ጦርነት ክፉኛ ተጎድቷል፡፡ የአማራ ክልል አሁንም ለሌላ ዙር አስከፊ ችግር ውስጥ በመግባቱ ሳቢያ፣ ይህንን ችግር ያለ የውጭ ጣልቃ ገብነት በድርድር ለመፍታት ቁርጠኝነት ማሳየት ይገባል፡፡ መንግሥት በአፋጣኝ ውይይትና ድርድር በማካሄድ በአገር ላይ እየደረሰ ያለውን የሰው ሕይወት መጥፋት፣ የንብረት ውድመት፣ እንዲሁም እየደረሰ ያለው ከፍተኛ ማኅበራዊ፣ ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመፍታት መነሳት አለበት፡፡ ችግሩን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ትጥቅ ካነገቡ አካላት ጋር የኃይል አማራጭ መፍትሔ አለመሆኑን በመገንዘብ፣ ብሎም ከትግራይ ጦርነት ተገቢውን ትምህርት በመውሰድ አፋጣኝ ድርድር ማድረግ ይጠበቃል፡፡

ከላይ እንዳየነው በተለይ ነፍጥ ያነገቡ አካላትና መንግሥት በመደራደር ግጭት አስወግደው አገርን ከጥፋት ሊያድኑ አልቻሉም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በመሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በወጉ ለመደማመጥ፣ ምክክር ለማድረግና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠርና ሒደቱን የሚመራና የሚያስተባብር አካል ለማቋቋም ከፍተኛ ጥረት መደረጉ ይታወሳል፡፡ የተለየዩ ዓላማዎች ያነገቡ በፖለቲካዊ መድረኩ ላይ ያሉ ኃይሎችንና ልሂቃንን፣ እንዲሁም ሕዝብ ውስጥ ያሉ ጥያቄዎችንና ሐሳቦችን መሠረት በማድረግ ለአገራዊ አንድነት ገንቢ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ በማሰብ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ታኅሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. በወጣ አዋጅ ተቋቁሟል፡፡

አገራዊ ምክክር ያስፈለገውም ለአገራችን አንኳር ችግሮች በመደበኛው የችግር አፈታት ሒደት መፍትሔ ማግኘት በማይቻልበት ደረጃ በመድረሳቸው፣ እንዲሁም የበለጠ እየገዘፉና እየተወሳሰበ ሄደው አገርን የማፍረስ ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት አገር ለማዳን እንዲያስችል ነው፡፡

አገራዊ ምክክር በመደበኛ አሠራሮች ሊፈቱ የማይችሉ መዋቅራዊና ጊዜያዊ ቅራኔዎችን በሰላማዊ መንገድ ተነጋግሮ ለመፍታት የሚያስችል በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው፡፡ አገራዊ ምክክር በአግባቡ ከተጠቀምንበት ልዩነቶች በማስታረቅ አገራዊ የፖለቲካ ቀውስን ለማስቀረት፣ ከፖለቲካዊ አጣብቂኞች ሰብሮ ለመውጣትና ውጥረትን ለማርገብ፣ በትጥቅ የታገዘ አመፅ እንዳይፈጠር አስቀድሞ ለመከላከል ታስቦ ነው፡፡ በተጨማሪም ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር ከዚህ ቀደም ለተፈጸሙ በደሎች፣ ወንጀሎች፣ እንዲሁም የፍትሕ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እንዲረዳ ነው፡፡

የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋሙ ግጭትና አለመግባባትን በጦር መሣርያ ከመፍታት ይልቅ፣ ጊዜውን በዋጀ የምክክርና የመደማመጥ ሥርዓት ውስጥ ሊያስገባን የሚችል መሆኑ በአዎንታዊ ጎኑ ይታያል፡፡ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን አሁን እየሠራቸው ካላቸው ሥራዎች ባሻገር፣ ገለልተኛ በሆነ መንገድ በፍጥነት ነፍጥ ያነገቡ አካላት ከመንግሥት ጋር የሚነጋገሩበትና የሚደራደሩበት ሁኔታ ሊያመቻች ይገባል፡፡

በሌላ በኩል አገራችን ኢትዮጵያ አገር በቀል የሆኑ የግጭት መፍቻ በሁሉም የአገሪቱ  ክፍል በሚባል ደረጃ ይህን ዕምቅ እሴት ተጠቅሞ፣ በተለይ በአሁኑ ወቅት ለሚከሰቱ ግጭቶች መፍቻ እርስ በእርስ መደማመጫ ለአገር ሰላም ግንባታ ለማዋል ጥረት ቢደረግም ፍሬ ሊያፈራ አልቻለም፡፡ እንደ አገር አለመግባባቶች ወይም ግጭቶች የሚፈቱበት ዕምቅ ማኅበራዊና አገር በቀል የግጭት ሥርዓቶች በማጠናከር፣ አለመግባባቶች በሰላማዊ ውይይት በመፍታትና የሽምግልናና የዕርቅ ሥርዓቶችን በማጎልበት፣ የኢትዮጵያን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ መሥራት ከሁላችንም የሚጠበቅ ነው፡፡ ይህንን አገር በቀል የዕርቅ ሥርዓት በመጠቀም አገራችን ከገጠማት ያለ መደማመጥ አዙሪት (Casandra Syndrome) ማውጣት ይጠበቅብናል፡፡

ከላይ ካነሳሁት ዕርቅና መደማመጥን በተመለከተ ተስፋ ሰጪ ሁኔታ ካየንበት ጉዳይ አንዱ በመንግሥትና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነግ ሸኔ) መካከል በዛንዚባር የተጀመረው ድርድር እንደሚቀጥል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ እንዲሁም ድርድሩ ሰምሮ ‹‹ዕርቅ መውረዱ›› አይቀሬ ነው ማለታቸውም አይዘነጋም፡፡ ይህ ዓመት ዕርቅ የሚወርድበትና ያለ መደማመጥ አዙሪት የሚያበቃበት ይሆናል በማለት በአዲስ ዓመት መግለጫቸው መናገራቸውም እንዲሁ፡፡ ይህም በራሱ ተስፋን ሲፈነጥቅ ከቃል ባለፈ ወደ ተግባር ቢለወጥ ያለፉትን ዓመታት በሰላምና በፀጥታ መደፍረስ ዜጎችን ለስደት፣ ለሕልፈት፣ ለንብረት ውድመትና ሌሎች ችግሮች ለተከሰቱበት ኦሮሚያ ክልል ዕፎይታ እንዲሁም ለአገሪቱ የሰላምና የፀጥታ መጎልበት የሚኖረው አዎንታዊ አስተዋጽኦ የጎላ ይሆናል፡፡

አሁንም ቢሆን ከገባንበት የግጭትና የቀውስ አዙሪት (Viscious Circle) ለመውጣት በተለይ በመንግሥት በኩል ሆደ ሰፊ በመሆን ካለፉ ስህተቶች በመማር አሁን እየደረሰ ካለው ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ የባሰ የከፋ አደጋ ከመድረሱ በፊት ያለ ውጭ አካላት ጣልቃ ገብነት በተለይ ትጥቅ ካነገቡ አካላት ጋር በወጉ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ለመደማመጥ፣ ለመደራደርና ዕርቅ ለመፈጸም የቀረበውን ሐሳብ የበለጠ አጠናክሮ መቀጠል የግድ ሊሆን ይገባል፡፡

እንደ አገር ተው ሲሉን የምንሰማቸው፣ አድርጉ ሲሉን የምንታዘዛቸው የፖለቲካ መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ባለሙያዎችና ምሁራን የምናገኝበት ዓመት ይሁንልን፡፡ እንደ አለመነጋገርና አለመደማመመጥ ያለ ክፉ ደዌ የለምና ይህ ሥር የሰደደ የአገራችን ፅኑ ሕመም የሚሽርበት ዓመት ያድርግልን እያልኩ በዚሁ ላብቃ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው tofick1970@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...