የአዕምሮ ጤና እጅግ ትኩረት ካልተሰጣቸው የማኅበረሰብ ጤና አገልግሎቶች አንዱ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በዓለም አንድ ቢሊዮን የሚጠጉ ሰዎች የአዕምሮ መቃወስ ችግር ያጋጠማቸው ሲሆን፣ ሦስት ሚሊዮኖቹ ደግም አልኮልን አብዝቶ በመጠቀም ምክንያት በየዓመቱ ሕይወታቸውን ያጣሉ፣ እንዲሁም በእንዳንዷ 40 ሰከንድ ውስጥ ራስን በራስ በማጥፋት አንድ ሰው ሕይወቱን ያጣል፡፡
በአሁኑ ወቅት በምድሪቱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በተለያዩ ወረርሽኞች፣ ሌሎች ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጫናዎች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ይህ ሁኔታ በሰዎች የአዕምሮ ጤና ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ በአንፃራዊነት በዓለም ጥቂት ሰዎች ብቻ ጥራት ላለው የአዕምሮ ጤና አገልግሎት ተደራሽ ሲሆኑ፣ በዝቅተኛና በመካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ደግሞ ከ75 በመቶ በላይ የአዕምሮ ሕመምና የሱስ አስያዥ ዕፆች ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎች ምንም ዓይነት ሕክምናም ሆነ እንክብካቤ እንደማያገኙ የአዕምሮ ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡
በተጨማሪም እስካሁን ድረስ በአዕምሮ ሕሙማን ላይ የሚደርሰው መገለል፣ አድልኦ፣ የሰብዓዊ መብት ንፍገትና የሕግ ማዕቀፍ መላላት ተባብሰው የቀጠሉ መሆኑንም ጥናቱ ሳይጠቁም አላለፈም፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የአዕምሮ ጤናን ለማልማት የሚደረገው ድጋፍ እጅግ ዝቅተኛ ከመሆኑ የተነሳ፣ በሕክምናና እንክብካቤ አሰጣጡ ላይ ትልቅ ክፍተት ፈጥሮ ቆይቷል፡፡ እንደ ዘርፉ ምሁራን ገለጻ፣ የአዕምሮ ጤና ልማት እንጂ ወጪ አይደለም፡፡ በመሆኑም በዚህ ምክንያት ቀጣይ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀልበስ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል በማለት ይጠይቃሉ፡፡
የአዕምሮ ጤና ድርጅት ሪፖርት የአዕምሮ ጤና ክብካቤ ክፍተቱ ሰፊ መሆኑን ገልጾ፣ 50 በመቶ ሰዎች የአዕምሮ መቃወስ ችግር ያለባቸው ሰዎች የሚገኙት በከፍተኛ ገቢ፣ 85 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በዝቅተኛና በመካከለኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ባላቸው አገሮች ውስጥ ነው፡፡ ለክብካቤና ለሕክምና ምቹ ሁኔታ እንደሌለም ጭምር ያመለክታል፡፡
በየዓመቱ የሚታሰበው የዓለም የአዕምሮ ጤና ቀን፣ ሁነት ብቻ ሳይሆን በአዕምሮ ጤና ልማት ሒደት ውስጥ የሚከናወነውን ተግባር ዕውን መሆን ለማረጋገጥ የሚያስችል የመንግሥትን፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን፣ የተባባሪ አካላትን፣ የፖሊሲ አውጪዎችን ትኩረት ለመሳብና ለመያዝ ምቹ ሁኔታና ጠቀሜታ የሚያበረክት ዕለት ጭምር እንደሆነ ምሁራን በአጽንኦት ያትታሉ፡፡
ስለሆነም በአዕምሮ ጤና ላይ ሕዝባዊ ተሳትፎን ለማጠናከር ይቻል ዘንድ የዘንድሮ የዓለም አዕምሮ ቀን ‹‹የአዕምሮ ጤና ዓለም አቀፋዊ ሰብዓዊ መብት ነው›› በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ መስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ተከብሮ ውሏል፡፡
በኤሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል የስብሰባ አዳራሽ በተከናወነው መርሐ ግብር፣ የጤና ሚኒስቴር የአዕምሮ ጤና ፕሮግራም ባለሙያ አቶ ጀማል ተሾመ፣ የአዕምሮ ጤና በኢትዮጵያ ያለውን ገጽታ በተመለከተ ገለጻ ሰጥተዋል፡፡
እንደ ባለሙያው ማብራሪያ የትም ይኑር ሁሉም ሰው የአዕምሮ ጤናው በከፍተኛ ደረጃ የመጠበቅ መብት አለው፡፡ ይህም ማለት የማኅበረሰቡ አባል መሆኑ፣ ነፃና ራስን መቻል፣ ከማንኛውም ጫና ተፅፅኖ ነፃ የመሆን፣ የተሻለ ጥራት ያለው ክብካቤ የማግኘት፣ የመደመጥ፣ የመሳተፍ፣ የመከበርና ተቀባይነትን የማግኘት መብቶች ሊከበርለት ይገባል፡፡
የአዕምሮ ጤና የአገርን ሰላምና መረጋጋትን እንደሚፈልግ፣ ይህ ካልሆነ ግን የአዕምሮ ጤና እክል ያለባቸው የሕክምና አገልግሎት ወደሚሰጥበት ተቋም የመሄድ ፍላጎታቸው እንደሚቀንስ፣ ሰላምና መረጋጋት ከሰፈነ ግን አገልግሎቱ ሊያገግም እንደሚችል ነው የተናገሩት፡፡
እስከ 24 ዓመት ባሉ ወጣቶችና አፍላ ወጣቶች ላይ ተገቢ የጤና ክብካቤ ከተሠራ 75 በመቶ የሚሆነው የአዕምሮ ጤና ችግር ምልክት አሳይቶ ሊጠፋ እንደሚችል፣ ምልክቱ እንደታየ አስፈላጊና ደጋፊ የሆኑ ነገሮች ከተዘጋጀላቸውና ክብካቤም ከተደረገላቸው መዳንና አምራች ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው ባለሙያው የገለጹት፡፡
የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የአዕምሮ ጤና እክል ሲያጋጥም እክሉ ያለበትን ሰው ብቻ ሳይሆን፣ አብረውት ባሉት ቤተሰቡና በማኅበረሰቡ ላይም ትልቅ ተፅዕኖ እንደሚያስከትል ገልጸው፣ ከዚህም አንፃር ትልቅ ትኩረት ሊቸረውም እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
የሚሰጠውም ትኩረት ከሰብዓዊ መብት አንፃር፣ ከጤና ኤክስቴንሽንና ከማኅበረሰብ አገልግሎት ጀምሮ በየደረጃው እስከ ሰብ ስፔሻሊቲ ሕክምና ድረስ ያለውን አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
የአዕምሮ ጤና እክል ያለበት የማኅበረሰብ ክፍል የጤና አገልግሎትን ብቻ ሳይሆን፣ ማንኛውንም አገልግሎት የማግኘት መብት ያለውና አድልኦና መገለል የሌለበት መሆን እንዳለበትም፣ ይህም የሚተገበረው በሴክተርና በተቋማት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዘርፎች ግዴታና ኃላፊነት መሆኑንም ነው ሚኒስትሯ ያመለከቱት፡፡
እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት፣ ከዓለም ሕዝቦች ከአራት ሰዎች አንዱ በሕይወት ዘመናቸው ለተለያዩ የጤና አክሎች ይጋለጣሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2019 ከአዕምሮና ከሱስ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሕመሞች ከሁሉም ሕመሞች ድርሻቸው ሲታይ የሚያሳድሩት ጫና 13 ከመቶ እንደሚደርስም ተናግረዋል፡፡
በአገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከስቶ የነበረው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአሁኑ ጊዜ ትንሽ እየቀነሰ ቢመጣም፣ በአዕምሮ ጤና ላይ ከፍተኛ ጫና እንዳስከተለ፣ በኢትዮጵያ ደረጃ ደግሞ ከግጭቶች ጋር በተያያዘ በርካታ የማኅበረሰብ ክፍል ለአዕምሮ ጤና፣ ለኢኮኖሚና ማኅበራዊ ችግሮች መጋለጡን፣ ይህም ሆኖ ግን ችግሮቹ የጤና ተደራሽነትን የበለጠ ለማስፋት ከፍተኛ ሥራ የሚያስፈልገው መሆኑን አመላክቶ ማለፉን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
በአገር ውስጥ የአዕምሮ ጤና ሕክምና የሚሰጡ የጤና ተቋማት ቁጥር እያደገ መምጣቱን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ ብቁ የአዕምሮ ጤና ባለሙያዎችን ለማፍራት እየተሠራ መሆኑን፣ የጤና ጣቢያዎችን ጨምሮ በተለያዩ የጤና ተቋማት የሕክምና አገልግሎቱን ተደራሽነት ለማስፋት የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል።
በዚህም የአዕምሮ ጤና አገልግሎትን የሚሰጡ በየደረጃው ያሉ ባለሙያዎችን አቅም ከማጎልበት አንፃር ከመጀመርያ ዲግሪ ጀምሮ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ስፔሻላይዜሽንን ጨምሮ ማሠልጠኑ ተጠናክሮ መቀጠሉንም፣ በአሁኑ ወቅት ከ70 በመቶ በላይ የሆኑ ሆስፒታሎች የአዕምሮ ጤና አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
የአዕምሮ ጤና ቀንን አስቦ ከማዋል ባለፈ ዘላቂነት ያለውና የተቀናጀ ግንዛቤን መፍጠር ያስፈልጋል ያሉት፣ በሚኒስቴሩ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሕይወት ሰሎሞን (ዶ/ር) ናቸው። ከመሪ ቃሉ በመነሳትም የአዕምሮ ጤና የሰብዓዊ መብት መሆኑን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገቡ ሥራዎችን እየተከናወኑ መሆናቸውንም መሪ ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል፡፡
የዓለም የአዕምሮ ጤና ቀን እ.ኤ.አ ከ1992 ጀምሮ በየዓመቱ ‹‹ኦክቶበር 10›› (መስከረም 28 ቀን/ በየአራት ዓመቱ መስከረም 29) በመከበር ላይ ይገኛል።