- የትግራይ ክልል የማራቶን ሪሌ ውድድር ያሰናዳል
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስተናጋጅነት የሚከናወኑት የአገር ውስጥ ዓመታዊ ውድድሮች የሚያስተናግዱ ከተሞች ተለይተው ለክልሎች መላካቸው ታውቋል፡፡
በዓለም አቀፍ ውድድሮች አገራቸውን ወክለው የሚሳተፉ አትሌቶችን ለመለየት የሚዘጋጁት ውድድሮችን እንዲያስተናግዱ ሰባት ከተሞች ተለይተዋል፡፡ የሩጫና የሜዳ ተግባራትን ያካተቱ ውድድሮች ለማከናወን ቢሾፍቱ፣ መቀለ፣ አዲስ አበባ፣ ሰመራ፣ ደብረ ብርሃን፣ አሰላና ሐዋሳ ከተሞች መመረጣቸው ታውቋል፡፡
ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ውድድሩን ለማስተናገድ የተመረጡ ከተሞች ለክልሎች የተላኩ ሲሆን፣ በቅርቡ በሥራ አስፈጻሚ ውሳኔ ያገኛሉ፡፡

በዚህም መሠረት የ2016 ዓ.ም. የአትሌቲክስ ውድድር ዘመን ጥቅምት 25 ቀን በቢሾፍቱ በሚከናወነው 10ኛው የኢትዮጵያ የ30 ኪሎ ሜትር የጎዳና ውድድር ይጀመራል፡፡
በሌላ በኩል ከሁለት ዓመታት በላይ ከውድድር ተሳትፎ ርቆ በቆየው የትግራይ ክልል፣ ኅዳር 8 ቀን 2016 ዓ.ም. 19ኛው የማራቶን ሪሌ ውድድር በመቀለ እንደሚከናወን የወጣው መርሐ ግብር ያመለክታል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ይፋ ባደረገው መርሐ ግብር መሠረት፣ ከታኅሣሥ 3 እስከ 7 ቀን የኢትዮጵያ አቋም መለኪያ ውድድር የአጭር፣ የመካከለኛና የ3000 ሜትር መሰናክል፣ እንዲሁም የሜዳ ተግባራትና የዕርምጃ ውድድሮችን በአዲስ አበባ ይከናወናሉ፡፡
ከዚህም ባሻገር 41ኛው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ውድድር ለጥር 19 ቀን በአዲስ አበባ ለማካሄድ ቀጠሮ ተይዟል፡፡
በአትሌቲክሱ ተተኪዎችን ለማፍራት ታቅዶ ዓምና መከናወን የጀመረው የኢትዮጵያ ፕሮጀክቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለሁለተኛ ጊዜ ከየካቲት 13 እስከ 17 በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ እንደሚከናወን ታውቋል፡፡
እንደ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ መረጃ ከሆነ 17ኛው የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ውድድርና የ5 ኪሎ ሜትር ሕዝባዊ ሩጫ መጋቢት 15 ቀን 2016 ዓ.ም. በደብረ ብርሃን ከተማ ይከናወናል፡፡
በርካታ አትሌቶች የተለያዩ ክለቦችን ወክለው የሚተፉበት ዓመታዊው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአዲስ አበባ እንደሚከናወን መርሐ ግብር ወጥቶለታል፡፡
ለ53ኛ ጊዜ የሚከናወነው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከሚያዝያ 8 እስከ 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ይከናወናል፡፡
በሌላው የፌዴሬሽኑ መርሐ ግብር መሠረት ለአራተኛ ጊዜ የሚከናወነው የኢትዮጵያ ማሠልጠኛ ማዕከላት አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከግንቦት 15 እስከ 18 ቀን በአሰላ ካተማ ለማከናወን መርሐ ግብር ወጥቶለታል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በየዓመቱ ይፋ ከሚያደርጋቸውና ውድድር ከሚያከናውንባቸው ከተሞች መካከል አሰላ የተለየ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ ይህም ከተማው በርካታ የአትሌቲክስ ተመልካቾች በአረንጓዴ ስታዲየም ስለሚታደሙና የማያቋርጥ ድጋፍ ስለሚያደርጉ እንደሆነ ይነገርላቸዋል፡፡
በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከሚከናወኑት ዓመታዊ ውድድሮች መካከል ዕድሜ ጠገብ የሆነው የሻምበል አበበ ቢቂላ ኢንተርናሽናል ማራቶንና የ10 ኪሎ ሜትር ሕዝባዊ ሩጫ ሰኔ 2 ቀን በአዲስ አበባ ይሄዳል፡፡ ውድድሩ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የጎዳና ውድድሮች ላይ ለሚካፈሉ አትሌቶች ራሳቸውን እንዲገመግሙ የሚረዳና የውድድር ዕድል የሚፈጥር ይሆናል ተብሏል፡፡
የዓመቱ የመዝጊያ ውድድር የሚሆነው 12ኛው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ሲሆን፣ ከሰኔ 26 እስከ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. በሐዋሳ ከተማ ይከናወናል፡፡
እንደ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ማሳሰቢያ የውድድር መርሐ ግብሩ እንደ አስፈላጊነቱ ሊሻሻል ወይም ሊስተካከል ይችላል፡፡
በአገር ውስጥ የሚከናወኑ ውድድሮች አትሌቶች ብቃታቸውን የሚገመግሙበት ብቸኛ አማራጭ ሲሆን፣ ተተኪ የሚሆኑ አትሌቶችም የሚገኙበት ነው፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞም ክለቦች ከተለያዩ የዞንና የወረዳ፣ እንዲሁም በትምህርት ቤት ውድድሮች ላይ ያገኟቸውን አትሌቶች የሚፈትኑት በእነዚህ ውድድሮች ነው፡፡ ሆኖም በአገሪቱ በትራክ ላይ ውድድር ማድረግ አዳጋች መሆኑን ተከትሎ ዓመታዊ ውድድሩ ስኬታማ መሆኑ አጠራጣሪ ያደርገዋል፡፡ በተለይ ወቅታዊ የአገሪቱ ሁኔታ ያልተረጋጋ መሆኑ ውድድሮችን ለማከናወን በእርግጠኝነት ለመናገር እንደማያስችል እየተገለጸ ይገኛል፡፡
በተለይ በአማራ ክልል እንደሚከናወኑ መርሐ ግብር የወጣላቸው ውድድሮች የማድረጋቸው ጉዳይ አጠራጣሪ መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡
በአንፃሩ አብዛኛዎቹ ውድድሮችን በአዲስ አበባ የመደረጋቸው ዕድል ሰፊ ቢሆንም፣ በከተማዋ የመሮጫ ትራክ ያለው ስታዲየም ባለመኖሩ የመከናወኑ ዕድል ጠባብ መሆኑ ይገለጻል፡፡