በጣፋጭ ጣዕሙ የሚታወቀው አገር በቀል የአሶሳ ማንጎ ከውጭ አገር በገባ ተባይ ምክንያት የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠበት፣ የአሶሳ የግብርና ምርምር ማዕከል አስታወቀ፡፡
እ.ኤ.አ. በ2010 በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ኩኬ እርሻ የነበሩ የህንድ ኢንቨስተሮች ባስገቡት ችግኝ ሳቢያ፣ ተባዩ መምጣቱንና በንፋስ አማካይነት በአጭር ጊዜ ውስጥ መስፋፋቱን፣ የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋው መልካሙ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
‹‹ዋይት ማንጎ ስኬል›› በመባል የሚታወቀው ተባይ ጣፋጩን የማንጎ ምርት ከአሶሳ አካባቢ ማጥፋቱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይሁን እንጂ ምርቱ የማንጎ ዛፎችን፣ ቅጠሎችንና ፍሬውን የሚያበላሽ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ተባዩ አገር በቀል የማንጎ ዝርያው እንዳያፈራ የሚያደርግ መሆኑን፣ ነገር ግን በምርምር የተገኙ ወይም የተዳቀሉ የማንጎ ዝርያዎች የመቋቋም አቅማቸው የተሻለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው የማንጎ ዝርያ ተባዩን መቋቋም ስላቃተው፣ ፍሬ ማፍራት አለመቻሉንና ፍሬ ቢሰጥም እንኳን ሳይደርስ እንደሚበላሽ አስረድተዋል፡፡
አገር በቀል ማንጎው በድጋሚ እንዲያፈራ ለማድረግ የባዮሎጂካልና የኬሚካል ዘዴዎችን በመጠቀም ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፣ ከተባዩ ሥርጭት አኳያ እዚህ ግባ የሚባል ሥራ አልተሠራም ያሉት የማዕከሉ የሰብል ጥበቃ ሥራ ሒደት ኃላፊ አቶ ምን ያህል ከበደ ናቸው፡፡
በምርምር ማዕከሉ ተባዩን ለማጥፋት የኬሚካል ርጭት ቢሞከርም፣ አመርቂ ውጤት እንዳላመጣና ማንጎ በሚያፈሩ አካባቢዎች መዳረሱን ገልጸዋል፡፡
ተባዩ የማንጎ ዛፍ ውኃን እንደሚመጥና በዓመት ሁለት ጊዜ ራሱን የሚያበዛበት ወቅት ስላለው፣ እስካሁን በሚደረገው ጥረት ማጥፋት አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡
በአገር ደረጃ በተባዩ ላይ የሚደረጉ ምርምሮች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ምንያህል፣ ተባዩን ለማጥፋት የኬሚካል ርጭት መሞከሩንና ጥሩ መሻሻል መታየቱን ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ የኬሚካል ርጭት ለማድረግ በተለይ አሶሳና ወለጋ አካባቢ የሚገኘው የማንጎ ዝርያ ቁመቱ እስከ ሰባት ሜትር ከፍ ያለ በመሆኑ፣ ለርጭት አመቺ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
የማንጎ ዛፍ ቅርንጫፎችን በመቁረጥ በማሳሳት ተባዩን የመቆጣጠሪያ መንገድ ተደርጎ ለመተግበር መሞከሩን፣ የተባዩ ፍጥነቱ ከበረሃማና ከሞቃታማ አካባቢዎች ውጪ ያሉትን ሥፍራዎች ማዳረሱን አስረድተዋል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ ጋምቤላ፣ መተከል፣ አማራ ክልልና ሌሎችም የማንጎ ምርት በሚገኝባቸው አካባቢዎች ተባዩ መዳረሱንና የማንጎ ምርት ከገበያ የጠፋበት ምክንያት ከዚህ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል አክለዋል፡፡
ላርጎና የምግብ ዘይት አቀላቅሎ በመርጨት ተባዩን የማጥፋት ተሞክሮ በአማራ ክልል ሲተገበር መቆየቱን፣ የዚህ ትግበራ ውጤታማነት ታይቶ በአሶሳም ለመተግበር ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡
የማንጎ ተባይን ለማጥፋት በአገር ደረጃ የተጨበጠ ነገር የለም የሚሉት አቶ ምንያህል፣ የሚደረጉ ምርምሮችም ቢሆኑ በሙከራ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው ብለዋል፡፡
ለግብርናና ለሌሎች ኢንቨስትመንት የሚገቡ ማናቸውም ድርጅቶች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ‹‹ኳራታይን›› ላይ ክፍተት በመኖሩ ምክንያት ችግሩ ማጋጠሙን ገልጸዋል፡፡
የአምቦ የግብርና ምርምር ማዕከል የግብርና ኢንቶሞሎጂ ምርምር ፕሮግራም ብሔራዊ አስተባባሪ አቶ በላይ አባተ፣ ‹‹ዋይት ማንጎ ስኬል›› የተባለው ተባይ በምሥራቅ ወለጋ ቡኬ እርሻ ውስጥ በምርምር ማዕከሉ መገኘቱን ያስታውሳሉ፡፡
የአምቦ ግብርና ምርምር ማዕከል ናሙውን ወደ አሜሪካ በመላክ ተባዩ ‹‹ዋይት ማንጎ ስኬል›› መሆኑን መረጋገጡን፣ ከዚያ በኋላ ተባዩን መቆጣጠር የሚያስችል ምርምር በአገር ውስጥ ሲረግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
ተባዩ የዕፅዋቱን ግንድ፣ ቅጠልና ፍሬ የሚበላ መሆኑንና በተለይም የክረምት ወቅት የሚራባበትና በቀላሉ የሚዛመትበት ስለሆነ ለቁጥጥር አስቸጋሪ ነው ይላሉ፡፡
ማንጎን የሚያጠፋው ተባይ ለኢትዮጵያ አዲስ በመሆኑ ለዚህ የሚሆን አገር በቀል የተፈጥሮ ጠላት አለመኖሩ ትልቅ ችግር ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
በአገር በቀል ዕውቀት በመጠቀም የተከናወኑ ሥራዎች መኖራቸውንና ይሁን እንጂ እስካሁን የተሠሩት የረዥም ጊዜ መፍትሔ አለመሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የረዥም ጊዜ መፍትሔ ተብለው ከተለያዩ አገሮች ተሞክሮዎች መታየታቸውንና ከእነዚህ መካከል የደቡብ አፍሪካና የግብፅ ልምዶች ይገኙበታል ብለዋል፡፡
በተለይም በደቡብ አፍሪካ ተባዩን ለመቀነስ የተጠቀሙትን ዘዴ የተፈጥሮ ጠላት መሆኑና ስኬታማ በመሆናቸው፣ በኢትዮጵያ ለመተግበር ጥረት ቢደረግም በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ እስካሁን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡
የተባዩን የተፈጥሮ ጠላት ከደቡብ አፍሪካ ለማስመጣት እ.ኤ.አ. በ2017 ብቻ 20,000 ዶላር የጠየቁ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ ማስገባት እንዳልተቻለ ጠቁመዋል፡፡
በአገር ምርመር ሥራ ሙሉ በሙሉ ማጥፋት እንደማይቻል ነገር ግን የማንጎ ቅርንጫፉን በመግረዝና ሌሎች ዘዴዎችን በመጠቀም ተባዩን መቀነስ እንደሚቻል አስታውቀዋል፡፡
እንደ አቶ በላይ ገለጻ፣ አገር በቀል ምርቶች በበሽታ እንዳይጠፉ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ኢንቨስተሮች የሚያመጧቸውን ምርቶች በዕፅዋት ኳሪታይን፣ በቴክኖሎጂና ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ማስገባት ይገባል ብለዋል፡፡