Sunday, December 10, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

አስተዋይነት በጎደለው ዕርምጃ አገር ለጉዳት እንዳትጋለጥ!

ጥንታውያኑ ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት አስከብረው በአፍሪካ ብቸኛዋ የነፃነት ተምሳሌት ያደረጓት፣ ከማንኛውም ልዩነትና ፍላጎት በላይ አገራቸውን በማስቀደማቸው ነው፡፡ በልዩ ልዩ ምክንያቶች የእርስ በርስ መገፋፋትና ትንቅንቅ በማያጣት ኢትዮጵያ፣ በየዘመናቱ የነበሩ ትውልዶች የአገራቸውን ዳር ድንበር ሳያስደፍሩ በጀግንነት የተዋደቁት ለአገር ክብር በነበራቸው ልዩ ፍቅር ነበር፡፡ አውሮፓውያን አፍሪካን እንደ ቅርጫ ዕጣ ተጣጥለው ሲከፋፈሉ ኢትዮጵያ የተረፈችው፣ በአገር ፍቅር ስሜትና በአርበኝነት ተጋድሎ ነው፡፡ አውሮፓውያን በኢትዮጵያ ዙሪያ ያሉ አገሮችን ጭምር ይዘው ወደ ኢትዮጵያም ሲያማትሩ፣ ልዩነቶቻቸውን በወግና በሥርዓት መያዝ የቻሉበት ጀግኖቹ ኢትዮጵያውያን በታሪክ የማይረሳ ድንቅ ተግባር አከናውነዋል፡፡ ከጦር ግንባሩ ተጋድሎ በተጨማሪ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ከቅኝ ገዥዎች ጋር እየተነጋገሩና እየተደራደሩ፣ እንዲሁም የከፋ ችግር ሲያጋጥም ለሰላም እጃቸውን እየዘረጉ በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ ለማለፋቸው ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ታላቁ የዓድዋ ድል የተመዘገበውም ከእልህ አስጨራሽ ዲፕሎማሲያዊ ትግል በኋላ ነበር፡፡ ይህንን አኩሪ ታሪክ በማስታወስ ለዚህ ዘመን የሚመጥን ተግባር ለማከናወን አርቆ አሳቢ መሆን የግድ ነው፡፡

በመካከለኛው ምሥራቅ በእስራኤልና በሐማስ መካከል የተጀመረው አደገኛ ጦርነት፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአካባቢው ባሉ አገሮች ላይ በሙሉ ከፍተኛ ሥጋት እንደሚፈጥር ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ይህ አደገኛ ጦርነት ከቅርብም ሆነ ከሩቅ ያሉ የውጭ አካላትን በጎራ እያሠለፈ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ጎራዎች መካከል መገኘትም ሆነ ገለልተኝነት በጣም አደገኛ ቢሆኑም፣ ብሔራዊ ደኅንነትንና ጥቅምን ታሳቢ ያደረገና በመርህ የሚታገዝ አቋም መያዝ የግድ ነው፡፡ ይህ አቋም ለሰላምና ለጋራ ጥቅም የሚረዳ፣ በማንም ግፊት የማይነዳ፣ በአርቆ አሳቢነት የሚመራ፣ ታሪካዊ ዳራዎች ላይ የሚመሠረት፣ የአፍሪካ ኅብረትንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ዓላማዎች ያነገበ፣ የኢትዮጵያን ዘመን ተሻጋሪ የዲፕሎማሲ ባህል ያከበረና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን የማያበላሽ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ እስራኤላዊያንም ሆኑ ፍልስጤማውያን ለበርካታ ዓመታት መፍትሔ ያጡለት አለመስማማት ብዙ ጊዜ ደም ያቃባቸው ሲሆን፣ ሐማስ ሰሞኑን በፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት ምክንያት በደረሰው ከፍተኛ ጥፋት የለየለት ጦርነት ተጀምሯል፡፡ ጦርነቱ የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት ሲጋብዝ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ከጥንቃቄዎቹ አንዱ የጦርነቱ አድማስ እየሰፋ ሌሎች ተዋንያን ጎራ ለይተው ለፍልሚያ ሲያቆበቁቡ፣ ከሩቅም ሆነ ከቅርብ የሚሰባሰቡ ኃይሎች የአካባቢውን አገሮች የውክልና ጦርነት ተሳታፊ ለማድረግ ግፊት መፍጠራቸው አይቀሬ ነው፡፡ አሜሪካ መራሹ የምዕራብ ኃይል ባለ በሌለ ኃይሉ ወደ አካባቢው ሲያመራ፣ በተቃራኒ ጎራ ያለው ስብስብ መንቀሳቀሱ አይቀርም፡፡ በተለይ ደግሞ በቀይ ባህርና በህንድ ውቅያኖስ መውጫ ላይ የጦር ሠፈሮቻቸውን የመሠረቱ በርካታ አገሮች፣ በግራና በቀኝ ሆነው በቅርብ ርቀት ጦርነቱን የበለጠ ለማስፋፋት መሥራታቸው ይጠበቃል፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ያሉ ሀብታሞቹ የባህረ ሰላጤው አገሮች ጥቅማቸውን እያሰሉ፣ የተውኔቱ ተሳታፊ እንደሚሆኑም ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ድንገተኛ ጥቃት የተከፈተባት እስራኤል በጋዛ ላይ የጀመረችው ከበባና ጥቃት ሲጠነክር፣ ኢራን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሌሎች ሸሪኮቿ ጋር ሆና እጇን ከማስገባት እንደማትታቀብ ይታሰባል፡፡ በዚህ ጊዜ የአካባቢው አገሮችን በሮች የሚያንኳኩ የድጋፍ ጥሪዎች ስለሚኖሩ፣ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡

ለዚህ ደግሞ ውስጣዊ አንድነትንና አገራዊ ማንነትን እየሸረሸሩ ካሉ የዘውግ ትርክቶች ውስጥ መውጣት ያስፈልጋል፡፡ በአገራዊ ዕሳቤ ላይ እየተፈጠረ ያለው አሳዛኝ ገጽታ ተለውጦ አንድነትን ማጠናከር የግድ ነው፡፡ ችግር ሲመጣ መሰባሰብ ችግሩ ሲወገድ ዓይንህን ለአፈር የሚለው ደዌ ተወግዶ፣ ውስጣዊ ችግሮችን በፍጥነት በመደማመጥና በመከባበር ስሜት ለመፍታት ጥረት ማድረግ ይገባል፡፡ ከአንድ አውዳሚ ጦርነት ወደ ሌላው የተገባበትን ስህተት በማረም፣ ለአገር ሰላምና ህልውና ሲባል ይቅር በመባባል የጋራ መፍትሔ መፈለግ ይተኮርበት፡፡ በተለይ መንግሥት ከሁሉም ያኮረፉ ኃይሎች ጋር በሰላማዊ መንገድ ለመነጋገር ቁርጠኝነቱን በተግባር ያሳይ፡፡ ከመንግሥት በተቃራኒ ያሉ ወገኖችም ለሰላም ያላቸውን አቋም በግልጽ ያሳዩ፡፡ ችግር በተፈጠረ ቁጥር በጦር መሣሪያ ለመፍታት ከመሯሯጥ በፊት ለመነጋገር፣ ለመከራከርና ለመደራደር ቁርጠኝነት ይኑር፡፡ በጦር መሣሪያ የሚደረጉ የእርስ በርስ ትንቅንቆች ኢትዮጵያ ውስጥ ያመጡት አንዳችም በጎ ነገር የለም፡፡ አምባገነኖችን በየተራ ከማፈራረቅ በስተቀር ለኢትዮጵያም ሆነ ለሕዝቡ ያስገኙት ተድላ ወይም ምቾት ሳይሆን፣ ድህነትንና ተመፅዋችነትን እንደሆነ ማንም አይክደውም፡፡

ሰኞ መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ሦስተኛ የሥራ ዘመን የጋራ መክፈቻ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ‹‹…ምንጊዜም ቢሆን ለሰላምና ለንግግር የሚረፍድ ጊዜ የለም…›› ብለው፣ መንግሥት ከማንኛውም ኃይል ጋር ችግሮችን በመወያየትና በንግግር የመፍታት ቁርጠኝነት እንዳለው የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት በሰላም መቋጨቱን በዋቢነት ጠቅሰዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያን አስጨንቀው ከያዟት ዋነኛ ችግሮች መካከል ተጠቃሹ፣ በየቦታው የሚስተዋለው የፀጥታ መደፍረስ ነው፡፡ ከዋና ከተማዋ አዲስ አበባ በአምስቱም በሮች ወጣ ብሎ ጉዳይን በሰላም ፈጽሞ መመለስ አዳጋች በሆነበት በዚህ ጊዜ፣ መንግሥት ከግማሽ መንገድ በላይ ተጉዞ ለሰላም መስፈን የሚጠበቅበትን መወጣት ይኖርበታል፡፡ እንደሚታወቀው በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ አካባቢዎች ሰዎች ይታገታሉ፣ ይዘረፋሉ፣ ይገደላሉ፣ ከመኖሪያ ቀዬአቸው ይፈናቀላሉ፡፡ ምርቶችን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ማንቀሳቀስና ወደ ገበያ ማድረስ ባለመቻሉ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ከመፈጠሩም በላይ፣ አምራቾች በሚያጋጥማቸው ኪሳራ ተስፋ እየቆረጡ ችግሩ ተባብሷል፡፡

ኢትዮጵያ ላለፉት አምስት ዓመታት ያለችበት ከግጭት ውስጥ ያለ መውጣት አዙሪት፣ ወትሮም የጦርነትና የድርቅ ሰለባ የሆነው የአፍሪካ ቀንድ አስተማማኝ አለመሆን፣ በቀይ ባህር አካባቢ የከተሙ የውጭ ኃይሎች የጦር ሠፈሮች መበራከት፣ አሁን ደግሞ ድንገት ሳይታሰብ የፈነዳው የእስራኤልና የሐማስ አስፈሪ ጦርነትና ሌሎች ሥጋቶች ለከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያነሳሱ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጣዊ ሰላሟ ታውኮ በእርስ በርስ ግጭት እየታመሰች የምትቀጥል ከሆነ፣ ከላይ የተጠቃቀሱት ችግሮች እየገዘፉ ከቀጠሉ ለህልውናዋ ጠንቅ መሆናቸው አይቀርም፡፡ በአካባቢው በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በዲፕሎማሲ ብቁና ንቁ ሆኖ መገኘት የሚቻለው ውስጣዊ ሰላም ሲኖር ነው፡፡ ውስጣዊ ሰላም ሲናጋ እጃቸውን አስረዝመው የሚያስገቡ የውጭ ኃይሎች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ኃይሎች ከራሳቸው ጥቅምና ፍላጎት ጋር የሚናበብ ተባባሪ ስለሆነ የሚሹት ማንኛውንም ነገር ከማድረግ አይመለሱም፡፡ ኢትዮጵያ በታላቁ የህዳሴ ግድብና ይኖራታል ተብሎ በሚታሰብ ዕምቅ አቅም ምክንያት ቁልቁል እንድትወርድ የሚፈልጉ ታሪካዊ ጠላቶችም ብቅ ብቅ ይላሉ፡፡ አስተዋይነት የጎደለው የፖለቲካ ዕርምጃ ለከፍተኛ ጉዳት እንደሚዳርግ መገንዘብ ይገባል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...

የስኳር ፋብሪካዎች መከላከያ ሠራዊት ተመድቦላቸው  እያመረቱ መሆኑ ተገለጸ

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ግሩፕ ውስጥ ከተካተቱ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለጥቃት ተጋላጮች አስተማማኝ ከለላ ይሰጥ!

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ምክንያት የተከሰቱ መጠነ ሰፊና አሳሳቢ የሰብዓዊ...

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...