ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፣ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የ2016 የጋራ ጉባዔን ሲከፍቱ ያስተጋቡት ኃይለ ቃል፡፡ የሕግ የበላይነትን
ማረጋገጥና የሰላም መንገዶችን አሟጦ በመጠቀም ዘላቂ አገራዊ ሰላምን ለማረጋገጥ መሥራት የዚህ ዓመት የመንግሥት ዋና ተግባር መሆኑን ያስታወቁት ፕሬዚዳንቷ፣ መንግሥት ከማንኛውም ኃይል ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑን ጠቅሰዋል። የሰላምና የእንድነት ጥሪ በማቅረብም በየትኛውም አካባቢ ያሉ ግጭቶች በሰላም እንዲፈቱም ጠይቀዋል። ኢትዮጵያ ጥንታዊት ከመሆኗ ባሻገር ለዓለም በታሪክ፣ በጥበብ፣ በአርበኝነትና በአሰባሳቢነት ጉልህ ድርሻ ያበረከተች ሆና ሳለ በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት ራሷን በሚያቀጭጭና በሚያወድም ችግር ውስጥ መሆኗንም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡