Monday, December 11, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የመንግሥት አካላትና ተቋማት የኮንትሮባንድ ንግድን እንደሚያባብሱ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ባለፈው በጀት ዓመት 80 ቢሊዮን ብር የሚገመት ኮንትሮባንድ ተይዟል ተብሏል

የመንግሥት ሆኑ ሌሎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ተቋማት ለኮንትሮባንድ ንግድ መቆም መፍትሔ ከመሆን ይልቅ፣ ሕገወጥ ንግድን የሚያባብሱ ሆነው አግኝተናቸዋል ሲሉ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ኃላፊዎች ገለጹ፡፡

በየአካባቢው ያሉ ተቋማት በኮንትሮባንድ ዙሪያ የሚያከናውኑትን በሚመለከት ሲያስረዱ፣ ድርጊቱን በመቃወም አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የመንግሥትና ሌሎች አካላት እንዳሉ ሁሉ፣ ‹‹ከችግሩ ጋር አብረው የሚኖሩና የሚተገብሩም›› እንዳሉ የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ተናግረዋል፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን 500 ለሚሆኑ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች የዕውቅናና የሽልማት መርሐ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ያዘጋጀ ሲሆን፣ ስለመርሐ ግብሩ ማክሰኞ መስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው አቶ ደበሌ ከሪፖርተር ለተነሳላቸው ጥያቄ ማብራሪያ ሲሰጡ ስለተቋማቱ የገለጹት፡፡

የተቋማቱን ስምና አድራሻ ሳይገልጹ እነዚህ ተቋማት ምንም እንኳን ዕርምጃ እየተወሰደባቸው ቢሆንም፣ የኮንትሮባንዲስቶቹ አካልና ተባባሪ ሆነው እየሠሩ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

‹‹ሁኔታ የሚያመቻቹ፣ የሚያሳልፉ፣ መረጃ የሚሰጡ፣ ሕገወጦችን የሚከላከሉላቸው፣ የሚደብቁ፣ እንዳይያዙና እንዳይመረመሩ የሚያደርጉ፣ ዕቃዎቻቸውን በሽፋን የሚያሳልፉ፣ ሐሰተኛ ሰነድ በመሥራት የሚተባበሩ…›› ሲሉ አቶ ደበሌ በሕገወጥ ንግድ ላይ፣ ‹‹ቀላል ቁጥር የሌላቸው›› ተቋማት እንዴት እንደሚሳተፉ አብራርተዋል፡፡

ስለኮንትሮባንድና ሕገወጥ ንግድ ሲነገር እነዚህ ችግሮች በበርካታ ተቋማት እንደሚፈጸሙ፣ ወደታችኛው የአስተዳደር አካል ሲወረድ ደግሞ ችግሮቹ ‹‹በጣም በከፍተኛ ደረጃ እየሰፉ ነው›› ሲሉ ኮሚሽነሩ ይገልጻሉ፡፡

ችግሩን በመቃወም አስተዋጽኦ እያበረከቱ ካሉ ተቋማት መካከል፣ ከጉምሩክ ኮሚሽንና ከገቢዎች ሚኒስቴር በተጨማሪ የፌዴራል ፖሊስ፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ ዓቃቢያነ ሕጎች፣ የክልል የፀጥታ አካላትና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንደሚገኝበት አስረድተዋል፡፡

ኮንትሮባንዲስቶች ሊጠቀሙባቸው የሚችሏቸው በርካታ መንገዶች እንዳሉ ሁሉ፣ ከሁለት ሺሕ ኪሎ ሜትር በላይ የሚረዝመውን ከምሥራቅ ኢትዮጵያ ክፍል እስከ ኬንያ ድንበር ድረስ ያለውን ሥፍራም ለዝውውር እንደሚጠቀሙበት ተገልጿል፡፡

በችግሮቹ ግዝፈትና አስከፊነት ልክ አቅም ያላቸው ተቋማትን መገንባት አንደኛው ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ፣ እንደ ሕግ አስከባሪ ዓይነት ተቋማትንም በሚገባ ማደራጀት እንደሚያስፈልግ ኮሚሽነሩ አውስተዋል፡፡

አቅምን ከመገንባት ባለፈም የሚወሰደው ዕርምጃ ትልቅ ሊሆን እንደሚገባና ከዚህ በፊት የተወዱት ዕርምጃዎችም ጥሩ እንደሆኑ ሲገልጹ፣ በተጠናቀቀው ዓመት ብቻ እስከ 80 ቢሊዮን ብር የተገመቱ የተለያዩ የኮንትሮባንድ ቁሳቁሶች እንደተያዙ ገልጸዋል፡፡

‹‹ይህ ቁጥር የሕገወጥነትን ጉልበት በልኩ የሚናገር፣ የተወሰደውን ዕርምጃ በልኩ የሚናገር፣ ቀጣይ ምን መሥራት እንደሚገባንም የሚናገር ነው፤›› ሲሉ አቶ ደበሌ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች