በ12 የተለያዩ መሥፈርቶች የተመረጡ 500 ግብር ከፋዮችን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ረቡዕ ጥቅምት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕውቅና ሊያሰጡና ሊያሸልሙ እንደሆነ፣ የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቁ፡፡
ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ለአምስት ዓመታት ከፍተኛ የግብር ከፋዮች የሆኑና በሕግ ተገዥነታቸው የተመረጡ ድርጅቶች ሲሸለሙ የቆዩ ሲሆን፣ ቁጥራቸውም ከ400 በልጦ አያውቅም ነበር፡፡ የገቢዎች ሚኒስቴርም በዚህ ዓመት 100 ያህል ግብር ከፋዮችን በማከል ሊያሸልም መሆኑን ገልጿል፡፡
‹‹በታክስና ቀረጥ የሕግ ተገዥነታቸው የተሻሉ የሆኑ፣ እንዲሁም በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ግብር ከፋዮች ናቸው ዕውቅና የሚሰጣቸው፤›› ሲሉ የገለጹት የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሤ ናቸው፡፡
ማክሰኞ መስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ከጉምሩክ ኮሚሽነሩ አቶ ደበሌ ቃበታ ጋር በመሆን በገቢዎች ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት መግለጫ የሰጡት ወ/ሮ ዓይናለም፣ በ2015 በጀት ዓመት የግብር አሰባሰብ የተሻለ አፈጻጸም የታየበት መሆኑንና የተሸላሚዎች ቁጥርም መጨመሩን አስረድተዋል፡፡
ሽልማትና ዕውቅና ከሚሰጣቸው 500 ግብር ከፋዮች ውስጥ 50 ያህሉ በፕላቲኒየም ደረጃ፣ 150 ያህሉ በወርቅ ደረጃ፣ 300 የሚሆኑት ደግሞ በብር ደረጃ የተደለደሉ መሆናቸው ተነግሯል፡፡
ሚኒስትሯ እንዳስረዱት 14 ያህል ግብር ከፋዮች ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ በተዘጋጁትና የዘንድሮን ጨምሮ በሁሉም ሽልማቶች በተከታታይ በፕላቲኒየም ደረጃ ሲሸለሙ ስለነበር፣ ‹‹ልዩ ዕውቅና›› ይሰጣቸዋል፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር በ2015 በጀት ዓመት 442 ቢሊዮን ብር በማሰባሰብ በ98.2 በመቶ ዕቅዱ አሳክቶ እንደነበር መገለጹ የሚታወስ ነው፡፡ በተያዘው በጀት ዓመት ደግሞ 529 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሠራ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የዕውቅናና የሽልማት መርሐ ግብሩ ጥቅምት 1 ቀን የተደረገበትን ምክንያት በመግለጫቸው ላይ ያስረዱት ሚኒስትሯ፣ በዚህ ወር ከሁሉም ወራት በበለጠ ትልቁ ገቢ ስለሚገኝ ነው ብለዋል፡፡
ከበጀት ዓመቱ 529 ቢሊዮን ብር የመሰብሰብ ዕቅድ ውስጥ በጥቅምት ወር ከአገር ውስጥ ታክስ 68.1 ቢሊዮን ብርና ከወጪ ንግድ ደግሞ 17.9 ቢሊዮን ብር፣ በድምሩ 86 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ እንደታቀደ ገቢዎች ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
ሚኒስቴሩ ካስቀመጣቸው ራዕዮች መካከል በ2022 ዓ.ም. የአገራዊ ወጪን በአገራዊ ገቢ ለመሸፈን የተያዘው ራዕይ አንደኛው እንደሆነ፣ ወ/ሮ ዓይናለም ለሚዲያ አካላት አስረድተዋል፡፡
በሽልማትና በዕውቅና መርሐ ግብሩ ላይ በተደጋጋሚ በከፍተኛ ግብር ከፋይነት የሚመረጡት የሥራ ዘርፎች ውስን መሆናቸውን፣ እነዚህ የሥራ ዘርፎች ላይ የፖሊሲ ለውጥ ቢኖር የመንግሥት ገቢ አስተማማኝነትና ቀጣይነትን በሚመለከት ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ሚኒስትሯ፣ ተቋማቸው ባላቸው መረጃ አብዛኞቹ ግብር ከፋዮች ደረጃቸውን ጠብቀው በሽልማት ውስጥ ያሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
‹‹ግብር ከፋዮች የተሰማሩባቸው ዘርፎች ቢታይ፣ ወደ አንድ ዘርፍ ያጋደለ ሳይሆን፣ ወደ ተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩትንም ያካተተ ነው፤›› ብለው፣ ሚኒስቴሩ በአስመጪና ላኪነት፣ በተለያዩ በአምራችነት የተሰማሩትንና በአገልግሎት ዘርፍ የተሳተፉትንም ያካተተ መሆኑን አስረድተዋል፡፡