Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለልዩ ፍላጎት ተማሪዎችና ለማዕከላቱ የተደረገው ረድዔት

ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎችና ለማዕከላቱ የተደረገው ረድዔት

ቀን:

የ‹‹ልዩ የትምህርት ፍላጎት›› የሚለው ቃል ከአካል ጉዳተኝነትም ሆነ ከሌላ ጋር ተያይዞ ለመማር የሚቸገሩ ተማሪዎችን ይመለከታል፡፡ ልዩ የትምህርት ፍላጎት ያላቸው ልጆች ለዕድሜ አቻዎቻቸው ከሚሰጠው ትምህርት በተጨማሪ ወይም የተለየ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የአካቶ ትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት፣ እንዲሁም በዘርፉ ላይ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት መንግሥት ፖሊሲዎችን እንደ አዲስ በመከለስ እየሠራ መሆኑ በተደጋጋሚ ይገለጻል፡፡

በተለይ የትምህርት ሥልጠና ፖሊሲውን መሠረት በማድረግ የትምህርት ሚኒስቴር ለትምህርት ልዩ ፍላጎት ላላቸው ሕፃናትና የማኅበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ እንዲሆን፣ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ፕሮግራም ስትራቴጂ በ1988 ዓ.ም. ቀርፆ እስከ 2003 ዓ.ም. ድረስ ተግባራዊ አድርጓል፡፡

ስትራቴጂው በሥራ ላይ ባዋላቸው አምስት ተከታታይ ዓመታት ከተገኙ ውጤቶች መካከል፣ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ፕሮግራሞች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መጀመራቸው ይገኝበታል፡፡

ከሁሉም በላይ የልዩ ፍላጎት ትምህርት የሚወስዱ ተማሪዎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ፣ መንግሥት በከተማ ደረጃ ማዕከላትን በመገንባት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት ይገኛል፡፡

በዚህም መሠረት የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ተገቢ የሆነ ትምህርት እንዲያገኙ፣ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ‹‹ተደራሽና አካታች ፍትሐዊ የትምህርት አገልግሎት ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች›› በሚል መሪ ቃል፣ መስከረም 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ግብዓቶችን ድጋፍ አድርጓል፡፡  

ለተማሪዎቹና ለማዕከላቱ ከተደረጉ ድጋፎች መካከል ብሬል፣ የብሬል ወረቀት፣ መቅረፀ ድምፅ፣ ቴሌቪዥንና መቀመጫዎች ይገኙበታል፡፡ ድጋፉ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችና ለነሱ ድጋፍ እንዲሰጡ የተቋቋሙ የድጋፍ መስጫ ማዕከላትን በቁሳቁስ ለማደራጀት ታስቦ የተደረገ ሲሆን፣ ቁሳቁሶቹን ከየክፍለ ከተማው የተውጣጡ የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) ተረክበዋል፡፡

ድጋፉም ሲደረግ ንግግር ያደረጉት የቢሮው ኃላፊ ዘለዓለም ሙላቱ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የልዩ ፍላጎት ትምህርት የራሱ የሆነ ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲኖረው ቢሮው ትኩረት አድርጎ እየሠራ ነው፡፡

ድጋፉም የተደረገላቸው የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ከመዋለ ሕፃናት እስከ 12ኛ ክፍል ደረጃ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን የተናገሩት ኃላፊው፣ ድጋፉም በዓይነት 28 መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ 10.8 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ግብዓቶችን በመግዛት ለተማሪዎች ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው፣ ድጋፉም የተደረገው በከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ሥር ለሚገኙ አሥራ ስምንት የድጋፍ መስጫ ማዕከላት ለሚገኙ ተማሪዎች መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ፣ የአካቶ ትምህርት ድጋፍ መስጫ ማዕከላትን በየዓመቱ እንዲዋቀር በማድረግ በዘርፉ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል ያሉት የቢሮው የልዩ ፍላጎትና አካቶ ትምህርት ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል አሥራት ናቸው፡፡

ቢሮው በ2015 ዓ.ም. 18 የአካቶ ትምህርት ድጋፍ መስጫ ማዕከላት ማዋቀር መቻሉን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ እነዚህም ድጋፍ መስጫ ማዕከላት የሚገኙ የልዩ ፍላጎት ትምህርት የሚማሩ ተማሪዎችን ድጋፍ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሠረት ዓይነ ሥውራን፣ መስማት የተሳናቸውን፣ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸውንም ጨምሮ፣ ሌሎች አካል ጉዳተኞችን መሠረት በማድረግ ድጋፉ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በ2016 ዓ.ም. ቢሮው አሥራ አራት የልዩ ፍላጎት ማዕከሎችን ማዋቀሩን፣ እንደ አጠቃላይ በከተማዋ 92 የሚሆኑ የአካቶ ትምህርት ድጋፍ መስጫ ማዕከላት እንዳሉ አቶ ዳንኤል ተናግረዋል፡፡

የልዩ ፍላጎት ትምህርት የሚማሩ ተማሪዎች ሩቅ መንገድ ተጉዘው ከመማር ይልቅ፣ በየአካባቢው ባሉ ማዕከሎች እንዲማሩ ቢሮው የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በቅርቡ የተቋቋሙ የልዩ ፍላጎት ማዕከሎች ላይ ተደራሽ ለመሆን ቢሮው የግብዓት ግዥ እያከናወነ መሆኑን ገልጸው፣ በቀጣይም ዓይነ ሥውር ለሆኑ ተማሪዎች በተለየ ሁኔታ ድጋፍ የሚደረግ ይሆናል ብለዋል፡፡

በተለይ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ለልዩ ፍላጎት ተማሪዎች የተለየ ትኩረት እንደሚሰጥ ጠቅሰው፣ ለዓይነ ሥውር ተማሪዎች የብሬል የመጽሐፍ ኅትመት ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህ መሠረት በአማርኛና በኦሮሚኛ መጽሐፎችን ለማሳተም እንቅስቃሴ መጀመሩን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ ይህንን ተፈጻሚ ለማድረግ ረዥም ጊዜ እንደሚጠይቅ አልሸሸጉም፡፡

የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን ተገቢ የሆነ ክትትል እንዲያገኙ በክፍለ ከተማ ደረጃ አሥራ አንድ የቡድን መሪዎች መኖራቸውን፣ በዚህም ዘርፍ ላይ የተሻለ ሥራ እየተሠራ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች የመማር ማስተማር ሁኔታ ምን ይመስላል የሚለውን ለመለየት፣ በቢሮ ደረጃ እየተሠራ መሆኑንና ይህንን ተደራሽ ለማድረግ በዘርፉ ልምድ ያላቸውን በርካታ አስተማሪዎችን እንዲሠሩ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችም የተሻለ እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ፣ አስተማሪዎችን ለማብቃት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሚገኝና ሥልጠና እየተሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም መንግሥት ለአካቶ ትምህርት አግባብነት ያላቸውንና ልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች፣ ኮንቬንሽኖችና ደንቦች፣ በተለይም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትኩረት የሰጠውን የአካል ጉዳተኞች መብት ጥበቃ ኮንቬንሽንን ተከትሎ እ.ኤ.አ. በ2006 በማፅደቅ የኢትዮጵያ የሕግ አካል እንዲሆን አድርጓል፡፡

በተመሳሳይ በ1986 ዓ.ም. ፀድቆ በተግባር ላይ የዋለው የትምህርት ሥልጠና ፖሊሲ፣ ጥራት ያለው የመጀመርያ ደረጃ ትምህርትን ለሁሉም ዜጎች ማዳረስ የመብት ጥያቄ ብቻ ሳይሆን፣ ልማትን የማረጋገጫ ዋስትና መሆኑን ያስቀምጣል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...