Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልአዲስ ወቅት አብሳሪው ኢሬቻ

አዲስ ወቅት አብሳሪው ኢሬቻ

ቀን:

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ከክረምት በኋላ የሚመጣው የመፀው ወቅት ሲሆን ጥቢን ተከትሎ ይመጣል፡፡ ኅብረተሰቡ አዲስ ዓመት ሲመጣ፣ ወቅት ሲለወጥ እንደየባህሉ፣ ትውፊቱና ወጉ ክብረ በዓል ያደርጋል፡፡ ከክረምት ወደ ብራ የሚደረገውን ታላቅ የወቅት ሽግግር ‹ኢሬቻ› በማለት በመስከረም ሦስተኛ ሳምንት ላይ በሚገኙት ቅዳሜና እሑድ ላይ የሚያከብረው የኦሮሞ ብሔር ነው፡፡

ዘንድሮ በዓሉ ወደ አራተኛው ሳምንት ተሻግሮ ቅዳሜ መስከረም 26 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ‹‹ሆራ ፊንፊኔ›› በሚል መጠርያ የተከበረ ሲሆን፣ ዛሬ እሑድ መስከረም 27 ደግሞ በቢሾፍቱ ‹‹ሆራ አርሰዲ›› ተብሎ እየተከበረ ነው፡፡

አዲስ ወቅት አብሳሪው ኢሬቻ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የኢሬቻ በዓል አከባበር ገጽታ በቀደሙት ዓመታት

ኢሬቻ ከጥንታውያኑ የኦሮሞ አባቶች ሲወርድ ሲዋረድ እንደመጣ ይነገራል፡፡ ሪፖርተር ከዚህ ቀደም ያነጋገራቸው አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ እንዳብራሩት፣ ኢሬቻ እርጥብ ሣር፣ ቅጠል ቄጠማ አበባ ማለት ነው፡፡  ‹‹ኢሬቻው ለእግዚአብሔር ምስጋና የምናቀርብበት ሥርዓት ነው፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡

‹‹ዓምና በሰላም በጤና 13ቱን ወር አስጨርሰኸናል፡፡ መጪውን ዓመት ደግሞ በሰላም እንድታደርሰን ይሁን፡፡ ይኸንን ለሰው ልጅ ለሁሉም ፍጥረት ብለህ የፈጠርከውን ንፁህ ውኃ በአንተ ኃይል አጣርተህ ያስቀመጥከውን በሐይቅህ ላይ ምስጋናህን እናቀርባለን፡፡ ውኃ ንፁህ ነውና፡፡››

የመመረቂያው ቦታ አድባር ‹‹ድሬ›› ይባላል፤ የተስተካከለ ቦታ ማለት ነው፡፡ ከዚህ ካልተመረቀ ወደታች ወደ ሐይቁ አይኬድም፡፡  ምርቃቱም የሚከወነው መራቂው በባህላዊው የኦሮሞ አልባሳት ተውበው ነው፡፡

ምርቃቱም ‹‹እንኳን በሰላም ከክረምቱ ወደ ብርሃኑ አወጣኸን፡፡ ዘመኑን በሰላም ያድርግልን፡፡ የእኛን ሕዝብና አገሪቷን ይባርክልን›› ይባልበታል፡፡

‹‹ኢሬቻ ሣሩን አበባውን እግዚአብሔር ነው ያበቀለው፡፡ ይኸንን አበባውን አብቅለህ ለከብቶች ሣር አብቅለህ፣ ለሰው ልጅ ደግሞ ዘር ሰጥተህ፣ ፍሬ አሰጥተህ ስላደረስከን ለአንተ ኢሬቻ እናቀርባለን፡፡ በክረምቱ መልካው ወንዙ ሞልቶ ዘመድ ከዘመድ ተለያይቶ አሁን ስለተገናኘ እግዚአብሔር ለአንተ ኢሬቻ እናቀርባለን፡፡››

ሆራ አርሴዲ የክብረ በዓሉ ዋነኛ ስፍራ ነው፡፡ ሰፊና ክብ ነው፡፡ አካባቢው ዙርያው በዛፎች ተሸፍኗል፡፡ ለበዓሉ አክባሪዎችና ሥነ ሥርዓቱ ተከታዮች ምቹ ስፍራ ነው፡፡ ታዳሚዎቹ ለምለም ቅጠል ቀጤማ ርጥብ ሳር አደይ አበባ ይዘው ሐይቁ ውስጥ እየነከሩ ይረጫሉ፤ ወደራሳቸውም ያስነካሉ፡፡ ከሐይቁ ዳርቻም ያስቀምጣሉ፡፡

የባህል ባለሙያው አቶ ገዛኸኝ ግርማ በድርሳናቸው እንደጻፉት፣ የኦሮሞ የገዳ ሥርዓት ልዩ ልዩ ቁሳዊ መገለጫዎች አሉት፡፡ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት የቅርሱ ቁሳዊ መገለጫዎች መካከል ኦዳ (ዋርካ) አንዱ ነው፡፡ በኦሮሞ ባህል የኦዳ ዛፍ የእምነትና የፖለቲካ ማዕከል ሲሆን፣ ዛሬም ድረስ ለብሔሩ አባላት የተለየ ተምሳሌታዊ ፋይዳ አለው፡፡ ኦዳ ለጉባዔ ማስኬጃነት የተመረጠው በግርማ ሞገሱና በጥላው ስፋት ብቻ አይደለም፡፡

የኦሮሞ ሽማግሌዎች እንደሚናገሩት፣ ኦዳን ከሌሎች ዛፎች ይበልጥ ተመራጭ ያደረገው ከክረምት እስከ በጋ ሳይደርቅ (ቅጠሉን ሳያራገፍ) መቆየት የሚችልና የሕዝቡን ተስፋና የአገሩን ልምላሜ የሚጠቁም ምልክት በመሆኑ ጭምር ነው፡፡

ውኃ እና ሕይወት

በካፑቺን ፍራንቸስካና የፍልስፍና እና የንባበ መለኮት ተቋም የአፍሪካ ፍልስፍና መምህሩ ዮሴፍ ሙሉጌታ ባባ (ዶ/ር) ስለኢሬቻ ፍልስፍናዊ፣ ሃይማኖታዊና ባህላዊ አንድምታ በጻፉት መጣጥፍ እንደገለጹት፣ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ለምለም ሳር የሰላምና የልዕልና ምልክት ነው፡፡ በበዓሉ ላይ የሚሳተፈው እያንዳንዱ ግለሰብ፣ ይህንን ለምለም ሳር በሁለት እጆቹ በመያዝ አምላኩን ያመሰግናል። ከሁሉም በላይ ክረምቱን ከበረዶ፣ ከከባድ ነፋስ፣ ከጎርፍና ከውርጭ የታደጋቸውን ታላቅና ቅዱስ አምላካቸውን አንድ ላይ ሆነው ያመሰግናሉ። መኸሩንና አዝመራውን ደግሞ እንዲባርክላቸው ወደ ፈጣሪ ይጸልያሉ። ስለዚህ የኢሬቻ በዓል ከጨለማ ወደ ብርሃን ላሻገረ አምላክ የሚሰጥ የክብር ዋጋ ነው።

‹‹በአንፃሩም ውኃ የሕይወት ምልክት ነው። ለዚህም ነው ውኃና ልምላሜ እንደ ዋቃዮ ስጦታ የሚታዩት። ያለ ውኃ ሕይወት ቀጣይነት የለውም። ውኃ ዋቃዮ ለፈጠራቸው ልጆቹ የሰጠው ፀጋ ነው፤›› ሲሉም ያክሉበታል፡፡

ድሪቢ ደምሴ ቦኩ በOromo Wisdom In Black Civilization መጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ ‹‹ኦሮሞ ወንዝ፣ ጫካና ተራራ ይወዳል፡፡ የተፈጠረበትና ፍቅር ያገኘበት ስለሆነ በየዓመቱ ለምለም ሳርና የአደይ አበባ ይዞ ለኢሬቻ ከወንዝ ውኃ ዳርቻ በመሄድ፣ ተራራ ላይ በመውጣት፣ ለፈጣሪው ምስጋና ያቀርባል። በጤና፣ በሰላም፣ ለሰውና ለከብት ዕርባታ እንዲሰጠውም ይጸልያል።››

በቢሾፍቱ ከተማ ሆራ አርሰዲ (ሐይቅ) ዳርቻ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በአዲስ አበባ በተዘጋጀ ኩሬ (በሆራ ፊንፊኔ)፣  የሚከበረው ኢሬቻ በእንስቶች ‹‹መሬ ሆ…›› ዜማ የሚታጀብ ነው፡፡

ሁሉም ነገር የተፈጥሮ ሥርዓቱን ጠብቆ እንደሚመጣ ለመግለጽ ከፊት ለፊት ልጃገረዶች ቀጥሎ ሴቶች ‹‹ማሬዎ ማሬዎ›› እያሉና ባህላዊ ጭፈራዎችን እያሰሙ ሲጓዙ፣ አባ ገዳዎች፣ አዛውንቶች እንዲሁም ወጣቶች (ፎሌዎችና ቄሮዎች) ይከተላሉ፡፡

የአፍሪካ ፍልስፍና መምህሩ ዮሴፍ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በኢሬቻ ከሚስተጋባው ጸሎት ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፡፡

‹‹ሀዬ! ሀዬ! ሀዬ! (አሜን አሜን አሜን)

ሀዬ! የእውነትና የሰላም አምላክ!

ሀዬ! ጥቁሩና ሆደ ሰፊው ቻይ አምላክ!

በሰላም ያሳደርከን በሰላም አውለን!

ከስህተትና ከክፉ ነገሮች ጠብቀን!

ለምድራችን ሰላም ስጥ!

ለወንዞቻችን ሰላም ስጥ!

ከጎረቤቶቻችን ጋር ሰላም ስጠን!

ለሰውም ለእንስሳቱም ሰላም ስጥ!››

‹‹ኢሬቻ ሰላም ነው፣ ሰላም ጥልቅ ትርጉም አለው፣ ሰው ከሰው ጋር፣ ሰው ከራሱ ጋር፣ ሰው ከተፈጥሮ ጋርና ሰው ከፈጣሪው ጋር ሰላም ሊኖረው ይገባል፤›› የሚለው ጽንሰ ሐሳብ የክብረ በዓሉ ጭብጥ ነው፡፡

በዕለተ ቀኑ ክብረ በዓሉ ሲከበር ልጃገረዶች ‹‹ማሬዎ ማሬዎ›› እያሉ የሚዘምሩት፣ ይኼም ማለት ሁሉም ነገር የተፈጥሮ ሥርዓትን ጠብቆ ዞሮ መምጣቱን ለመግለጽ እንደሆነ ጥናቶቹ ያስረዳሉ፡፡ በዚህ በዓል በፈጣሪና ፍጥረት መሀል ያለው ሥርዓት ሳይቋረጥ ሒደቱን ጠብቆ በመካሄዱ የሚከበር የምስጋናና የምልጃ በዓል እንደሆነ ለማስረዳት ነው፡፡

ምልጃውና ምስጋናው ክረምትና በጋ፣ ቀን ሌሊት፣ ብርሃንና ጨለማ፣ ልጅነትና እርጅና እንዲሁም ሕይወትና ሞት የማያቋርጡ ሒደቶች እንደሆኑ ለማሳየት ነው፡፡

ከዚህ ቀደም በበዓሉ ላይ ከአባ ገዳዎች ጋር ሲመርቁ ያገኘናቸው አንድ አባት፣ ስለ ኢሬቻ እንዲህ ያብራራሉ፡፡ ‹‹ኢሬቻ ትርጉሙ እርቅ ማለት ነው፡፡ ሰዎችና ሰዎች የሚታረቁበት እግዜርና ሰው የሚታረቁበት ሰላም፣ ስምምነት አንድነት ምቾት ማለት ነው፡፡ በክረምት ወንዞች ሄደው ሳያልቁ ሳይደርቁ እዚህ ያለውና እዚያ ሳይገናኝ ይቆያል፡፡ ስለዚህ ወደ ወንዙ ይሄድና ከወዲህና ማዶ ያለው ‹አላችሁ ደርሳችኋል እኛ ደርሰናል› እያለ እርስ በርስ ሰላምታ ይለዋወጣል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ኢሬቻውን ፈጽሞ ይሄዳል፡፡››

ኢሬቻ የገዳ ሥርዓትን ልዩ ከሚያደርጉ አንዱ በመሆኑ የመንግሥታቱ ድርጅት የባህል ተቋም ዩኔስኮ፣ የገዳ ሥርዓትን  በማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ወካይ መዝገብ ለመካተቱም አንዱ ምክንያት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...