Sunday, December 10, 2023

የድርቅና የረሃብ ዑደት በኢትዮጵያ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የቆዳ ስፋቷ 1.1 ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር የሆነው ኢትዮጵያ ከዓለማችን 27ኛ ደረጃ ላይ የምትቀመጥ ሰፊ አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ለእርሻ ሥራ መዋል የሚችል 38.5 ሚሊዮን ሔክታር መሬት አላት፡፡ ኢትዮጵያ አላት ከሚባለው 120 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ አብላጫው ጠንካራ የሥራ ኃይል መሆን የሚችል ወጣት የኅብረተሰብ ክፍል ነው፡፡

ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ122 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ የዝናብ ውኃም ታገኛለች ይባላል፡፡ አገሪቱ 2.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የከርሰ ምድር ውኃም አላት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በየአቅጣጫው እየፈሰሱ ለጎረቤት አገሮች ጭምር የተረፉ ከ12 ያላነሱ ዋና ዋና ወንዞችና ተፋሰሶችም አሏት፡፡

ኢትዮጵያ ከ22 ያላነሱ ዋና ዋና ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ሐይቆች ሲኖራት፣ በመስኖ ሊለማ የሚችል ከ5.3 እስከ አሥር ሚሊዮን ሔክታር መሬት እንዳላትም ይነገራል፡፡

ራሷን ‹‹የ13 ወር ፀጋ›› እያለች ስትጠራ የኖረችው ኢትዮጵያ ዓመቱን ሙሉ የፀሐይ ብርሃን የምታገኝ አገር ናት፡፡ አገሪቱ በዓመት አንዴ ብቻ ሳይሆን ሁለትም ሆነ ሦስቴ አርሶ ለመብላት የምትቸገር አይደለችም፡፡

ኢትዮጵያ ለመራብና ለመቸገር ብዙ ምክንያት የላትም ነው የሚባለው፡፡ አገሪቱ ለመቸገርና ለመደህየት ራሷን ሆን ብላ ካላመቻቸች በስተቀር ተፈጥሮ ያደላት ባለፀጋ ነች ነው የሚባለው፡፡ ለምሳሌ ለግብርና ከሚሆነው 38 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ውስጥ 16 ሚሊዮን ያህሉ የሚታረስ ሲሆን፣ ቀሪው 20 ሚሊዮን ሔክታር ደግሞ ለእንስሳት ግጦሽ የሚውል መሆኑ ይነገራል፡፡

በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ጥንታዊ መሠረት ያለው ነው፡፡ የአገሪቱን 40 በመቶ ጥቅል ምርት የሚሸፍነው ግብርና 80 በመቶ የወጪ ንግድ ምርቶች መሠረት ነው፡፡ ግብርና ከአገሪቱ የሥራ ኃይል ውስጥ 75 በመቶውን ያሰማራ መስክ ሲሆን፣ በአጠቃላይ የአገር ‹ዋልታና ማገር› የሚል ስም የወጣለት የእያንዳንዱን ሰው ሕይወት የሚነካ የኢኮኖሚ መስክ ነው፡፡ 

ይሁን እንጂ የአገሪቱ የግብርና ዘርፍ የቱንም ያህል ቢተልቅም ሆነ ቢዘመርለት አገሪቱን በቅጡ መቀለብ ያልቻለ ዘርፍ መሆኑ አይካድም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አገሩ ሰፊ የግብርና መስክ ቢኖራትም፣ የተመጣጠነ ጤናማ የምግብ ሥርዓት ማግኘት እንኳ አልቻለም ነው የሚባለው፡፡ የሕዝብ ቁጥር ዕድገትን፣ የከተሞች መስፋፋትንም ሆነ የኢንዱስትሪና የኤክስፖርት ዕድገቶችን የተስተካከለ የግብርና ዘርፍ ምርታማነት ዕድገት በአገሪቱ አለመኖሩ ነው በሰፊው የሚነገረው፡፡

ኢትዮጵያ ከእጅ ወደ አፍ ከሆነ የግብርና አመራረት ተላቃ ወደ ትርፍ አምራችነት የምትሸጋገርበት ጊዜ መቼ ነው? የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀን ሦስቴ ጎርሶ ማደር የሚችለው መቼ ነው? የሚለው ጉዳይም ለረዥም ጊዜ ሲጠየቅ ነው የኖረው፡፡

ኢትዮጵያ ሕዝቧ በቀን ሦስቴ እንዲበላ እናደርጋለን የሚሉ መሪዎች አጥታ እንደማታውቅ ይነገራል፡፡ በየጊዜው ከረሃብና ከችግር ኢትዮጵያን እናላቅቃለን የሚለው ቃል ቢደጋገምም ልክ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም ድርቅ፣ ረሃብና ችግርን መጋፈጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግዴታው የሆነ ይመስላል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት (UNOCHA) መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ 28.6 ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ አገሪቱ 4.6 ሚሊዮን ከቤት ቀዬአቸው የተፈናቀሉ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች እንዳላት ያመለከተው ኦቻ፣ ወደ 942 ሺሕ የውጭ ስደተኞችና ተገን ጠያቂዎችን ማስጠጋቷንም ይገልጻል፡፡

የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) በበኩሉ ረሃብ የዓለም ችግር መሆኑን ይገልጻል፡፡ በዋናነት አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች 783 ሚሊዮን ሰዎች በምግብ እጥረት ክፉኛ እንደሚቀጡ ይጠቁማል፡፡ ይህ ችግር ከሚቀጣቸው አብላጫዎቹ ወይም 60 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ሴቶችና ሕፃናት መሆናቸውን ነው ፋኦ በቅርብ ሰሞን ሪፖርቱ የጠቀሰው፡፡

የድርቅ አደጋ የፈጠረው የምግብ እጥረት ችግር ዓለም አቀፍ ችግር ቢሆንም በምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ የተፈጠረው ቀውስ ግን ከሁሉ እንደሚሰፋ ይገለጻል፡፡ ኢትዮጵያ በምትገኝበት በዚህ ቀጣና ወደ 32 ሚሊዮን ሕዝቦችን ከረሃብ አደጋ ለማትረፍ 2.4 ቢሊዮን ዶላር አስቸኳይ ዕርዳታ ያስፈልጋልም ይባላል፡፡ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር በቀረበው ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ጥሪ ለዓመታት በዘለቀ ተደጋጋሚ ድርቅ፣ ግጭት፣ ጎርፍ፣ ጦርነትና መፈናቀል በኢትዮጵያ፣ በሶማሊያ፣ በኬንያ፣ በደቡብ ሱዳንና በሌሎች የቀጣናው አገሮች አስከፊ የሚባል የሰብዓዊ ቀውስ መፈጠሩ ተነግሯል፡፡

በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የሰብዓዊ ቀውስ ባለበት በዚህ ወቅት ግን ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ድርጅቶችና ለጋሾች የሰብዓዊ ዕርዳታ አቋርጠው ቆይተዋል፡፡

የዕርዳታ ድርጅቶቹና ለጋሾቹ ሰብዓዊ ረድዔቱን ለማቆም የተገደዱት፣ በአገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የዕርዳታ እህል ስርቆትና ሽያጭ በማጋጠሙ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ከአንድ ወር ቀደም ብሎ ኦቻ ይፋ እንዳደረገው 20.1 ሚሊዮን ሰብዓዊ ረድዔት ፈላጊ ኢትዮጵያዊያንን ለመርዳት 4.4 ቢሊዮን ዶላር የረድዔት አቅርቦት ያስፈልጋል ይላል፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ ፍላጎት ውስጥ ማሳካት የተቻለው 30 በመቶውን ወይም 1.2 ቢሊዮን ዶላሩን ብቻ ነው ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ የረድዔት አቅርቦት አቋርጠው የቆዩ የዕርዳታ ድርጅቶችና ለጋሾች ቀስ በቀስ የዕርዳታ አቅርቦታቸውን መጀመራቸው ቢነገርም፣ ነገር ግን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለዕርዳታ አቅርቦቱ የሚያደርገው ድጋፍ በቂ አለመሆኑ ነው እየተነገረ የሚኘው፡፡

ይህ ሁሉ እየገጠማት ባለችው ኢትዮጵያ አሁን ላይ ደግሞ ሌላ ዙር የድርቅ አደጋ እንዳጋጠማት እየተነገረ ነው፡፡

በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በቅርቡ የከፋ የድርቅ አደጋ መከሰቱ ታውቋል፡፡ በዞኑ በትንሹ ሦስት ወረዳዎችን ድርቁ ማጥቃቱን የገለጹት የበየዳ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረሕይወት በላይነህ፣ በየዳ ወረዳ ውስጥ ድርቁ ያደረሰው ጉዳት ከባድ ነው ቀላሉ፡፡

‹‹በበየዳ ወረዳ 35 ሺሕ ሕዝብ በድርቁ ተጎጂ ሆኗል፡፡ በአካባቢያችን እስካሁን ባገኘነው ሪፖርት ከ17 ሺሕ በላይ እንስሳት ሞተዋል፡፡ ድርቁ ገና ያልበቀሉ ሰብሎችን፣ በመብቀል ላይ የነበሩና በቅለው ፍሬ ለመስጠት የተቃረቡ ማሳዎችን አውድሟል፤›› በማለት ነው አቶ ገብረሕይወት የተናገሩት፡፡ በወረዳቸው በመደበኛነት የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች እንደሚሠሩ ያመለከቱት ኃላፊው የድርቁ አደጋ ሊፈጠር የሚችል እንደሆነ አስቀድሞ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የመረጃ ልውውጥ እንደነበርም አመልክተዋል፡፡

አካባቢያቸው ዝናብ አጠር እንደ መሆኑ በመደበኛነት ድርቅ ሊያጠቃው እንደሚችል እንደሚታወቅ አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ከነበረው የቅድመ ዝግጅት ሥራ በመነሳት አሁን ላይ ለ2100 ሰዎች ዕርዳታ እያቀረብን ነው፡፡ ተጨማሪ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች የመለየት ሥራም እየሠራን እንገኛለን፤›› በማለት አቶ ገብረሕይወት ገልጸዋል፡፡

በአፋር ክልል ደረሰ ስለተባለው የድርቅ አደጋ ገለጻ ያደረጉት የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ መሐመድ ዓሊ በበኩላቸው አደጋው የሚባለውን ያህል አለመሆኑን አመልክተዋል፡፡ የአንበጣም ሆነ የግሪሳ ወፍ ችግር አለመኖሩን በመጥቀስ ድርቁ ጥቂት አካባቢዎችን የሸፈነ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹በአማራና በትግራይ አዋሳኝ አካባቢዎች ድርቁ ታይቷል፡፡ አንበጣውን በሚመለከት ግን በፌዴራል መንግሥት ዕገዛ አስቀድሞ የኬሚካል ርጭት ሥራ በመሠራቱ ችግሩ ሳይባባስ መከላከል ተችሏል፤›› ሲሉ ነው አቶ መሐመድ የተናገሩት፡፡

‹‹የድርቁ አደጋ እንደሚባለው አይደለም፡፡ በዋናነት የጦርነት ቀጣና የነበሩ፣ ቆላማና እርጥበት አጠር አካባቢዎችን ነው ያጠቃው፡፡ በተለይ በዞን አራት አካባቢ አርብቶ አደርና ቆላማ የሆኑ ወደ አራት ወረዳዎችን ያዳረሰ ድርቅ ነው የደረሰው፤›› ብለዋል፡፡

በአፋር ክልል አሁን ከትግራይና ከአማራ ክልሎች ጋር የሚዋሰኑ አካባቢዎች ለድርቅ መጋለጣቸው እንደታወቀ ያስረዱት አቶ መሐመድ፣ እነዚህን በድርቅ የተጠቁ አካባቢዎችን የሚሸፍን የዕርዳታ አቅርቦት ሥራ ክልሉ እንደሚሠራ አመልክተዋል፡፡ ‹‹የጦር ቀጣና የነበሩና ዝናብ አጠር የሆኑ ቆላማ አካባቢዎች ናቸው ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑት፡፡ ነገር ግን ጉዳቱ ያን ያህል የሰፋና አሥጊ አይደለም፤›› በማለት አቶ መሐመድ አስተያየታቸውን አጠቃለዋል፡፡

በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር ብቻ ሳይሆን በሌሎች አካባቢዎችም ከበድ ያለ ድርቅ ማጋጠሙ እየተሰማ ነው፡፡ ለምሳሌ በዋግ ህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በአራት ወረዳዎች ሥር የሚገኙ 40 ቀበሌዎችን ለጉዳት የዳረገ ድርቅ ተከስቷል ተብሏል፡፡ የዞኑ አደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምሕረት መላኩ እንደተናገሩት፣ ከ123 ሺሕ በላይ ዜጎች በዞኑ አስቸኳይ ዕርዳታ ፈላጊ ሆነዋል፡፡

የአማራ ክልል አዲሱ አስተዳደር ክልሉ የገጠመውን የድርቅ አደጋ በተመለከተ ምላሽ የሰጠ መሆኑን፣ አጣዳፊ የዕርዳታ ማቅረብ ርብርብ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ የክልሉ መንግሥት 430 ሚሊዮን ብር መመደቡን የተናገረ ሲሆን፣ እህል ገዝቶ FAO) jj/m/sics

ለድርቁ ተጎጂዎች የማቅረብ ሥራ እንደሚሠራ ገልጿል፡፡ የዕርዳታ ማቅረቡ ሥራም በጥናት የተደገፈ እንደሚሆን ያመለከተው ክልሉ የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸው አካባቢዎችን በመለየት ዕርዳታ እንደሚያቀርብ ነው ያመለከተው፡፡

ዓምና በደቡብ፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ከበድ ያለ የድርቅ አደጋ መድረሱ አይዘነጋም፡፡ ለተከታታይ ዓመታት በድርቁ ሲጠቁ የቆዩት የቦረናና የሶማሌ ቆላማ አካባቢዎች ደግሞ በተለየ ሁኔታ የእንስሳት ሞት ማጋጠሙ፣ እንዲሁም ብዙ ሕዝብ ማፈናቀሉ ነው የሚነገረው፡፡ ከመንግሥትና ከዕርዳታ ድርጅቶች ርብርብ ባለፈ በማኅበራዊ የትስስር ገጾችና በግለሰቦች ጭምር ሰፊ የዕርዳታ ማስባሰብ ጥረቶች ሲደረጉ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ እያከታተለ ድርቅ ሲያጠቃት ለልመናና ዕርዳታ ከመሮጥ ይልቅ፣ አስቀድሞ የቅድመ ማስጠንቀቅ ሥራዎች ማከናወን ለምን አይቻልም የሚለው ጉዳይ በብዙዎች ተደጋግሞ ይነሳል፡፡

ይህን በሚመለከት ምላሽ የሰጡት የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ አታለል አቦሃይ በዚህ ረገድ በቋሚነት ሥራዎች እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

‹‹በየሳምንቱና በየወሩ መደበኛ ስብሰባ በፌዴራልና በክልል አደጋ ሥጋት አመራሮች መካከል ቋሚ ስብሰባዎች ይደረጋሉ፡፡ ከክልሎች ጋር በጋራ የተዋቀረ የጋራ ግብረ ኃይል አለን፡፡ የሚያስተሳስረን የጋራ ዕቅድም አለን፡፡ የፌዴራል መንግሥት የራሱን ኃላፊነት የሚወጣ ሲሆን ክልሎች በባለቤትነት የራሳቸውን ኃላፊነት ይወጣሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ድርቅም ሆነ ጎርፍ በብዙ ቦታዎች ጉዳት አድርሰዋል፡፡ ክልሎች ለእነዚህ አደጋዎች ምላሽ ለመስጠት ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

በአማራ ክልል ለምሳሌ ዝናብ አጠር በሆኑት እንደ ጃናሞራና ዋግ ህምራ በመሳሰሉት አካባቢዎች ለድርቅ ተጋላጭ መሆናቸው እንደሚታወቅ የጠቀሱት አቶ አታለል፣ እንዲህ ላሉ አካባቢዎች የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራ መሥራት ወይም አለመሥራት ጉዳይ የሚፈጥረው ልዩነት አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡

ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ እንደ አገር በተደጋጋሚ ለድርቅ መዳረጓ የሚጠበቅ ነው፡፡ የዓለም ሜቲዮሮሎጂ ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ኢትዮጵያን ጨምሮ መደበኛ የዝናብ ሥርጭት በዓለም አየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የተነሳ እያሽቆለቆለ መጥቷል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የወጡ መረጃዎች እንዳመለከቱት በምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ ቀጣና ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ 20 ሚሊዮን ሕዝቦች እ.ኤ.አ በ2022 ለዕርዳታ ጠባቂነት ተዳርገዋል፡፡ በዓለም አየር ንብረት ለውጥ የተነሳ በአፍሪካ ለግብርና ሥራ ተስማሚ ከነበረው 874 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ውስጥ 83 በመቶው ለምነቱን ወይም ምርታማነቱን እያጣ መምጣቱ ተመላክቷል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ተጋላጭ የሆኑ የአፍሪካ አገሮች እንደከዚህ ቀደሙ በመዘናጋት ወይም በተዝናና ሁኔታ የሚያልፉት የግብርና ሥራ ዝግጅት ወይም የምርት ወቅት አለመኖሩ በተደጋጋሚ ይወሳል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በአሁኑ ጊዜ ለአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ቅድሚያ መስጠቱ ይነገራል፡፡ የችግኝ ተከላ ዘመቻዎችን ለተከታታይ ዓመታት ከማካሄድ ባለፈ፣ አገሪቱን የስንዴ ኤክስፖርተር ለማድረግ ትልቅ ግብ አስቀምጦ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ አገሪቱን ከተረጂነት ማላቀቅ አልቻለም፡፡ በየጊዜው ለሚፈጠሩ የድርቅ አደጋዎች ከጊዜያዊ መፍትሔ ባለፈ የሚጨበጥ ለውጥ የሚያመጣ የፖሊሲ መፍትሔ መንግሥት መተግበር አለመቻሉ አደጋውን አጉልቶታል ይባላል፡፡ ስለብልፅግና፣ ስለስንዴ ኤክስፖርትና ስለሙዝ በዳቦ እየተወራ በተቃራኒው ጤፍ በኩንታል 15 ሺሕ ብር መሸጡ፣ እንዲሁም ሽንኩርት በኪሎ 150 ብር መሸጡ አገሪቱ ባለህበት እርገጥ ሁኔታ ውስጥ ወድቃለች የሚለው ብዙዎችን የሚያነጋግር ጉዳይ መሆኑ ነው የሚነገረው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -